>
9:23 am - Friday June 2, 2023

አስመራ የትናንቴ ከተማ  - አደይ! (ታምሩ ተመስገን)

አስመራ የትናንቴ ከተማ  – አደይ!

ታምሩ ተመስገን
ከህይወት አንድ ጥግ ላይ በአርምሞ ተቀምጬ በዘመን ፊት ሁሉም እንዲሁ አንደአመጣጡ  ተራውን ጠብቆ ሲያልፍ አየሁ። ክረምትና በጋ አለፉ። ቁርና ሀሩርም እንዲያ። ካፊያና ብራ ቀንም እንደሌሎቹ። ዘመን ያመጣውን ሁሉ  ይዞ እብስ አለ።
ቦታ ብቻ ከንፋሱ ጋር ዘመም ቀና እንዳለ በረገጡት ዳናዎችን ታሪክ እንደተደመመ ቀረ።
ቦታ ግን በዘመን እንዳያልፍ ምንድን ነው?
የኮሮኮንቹ መንገድ ከሚያርገፈግፋት አሮጌ ፊያት ቺኳንታ ውስጥ  ኬኔዲ
“እኔ ልሁን ደህና
አምላክ ይስጠኝ ጤና…” እያለ ያቀነቅናል።
ከ16 አመታት በኋላ ወደ አስመራ እየተመለስኩ ነው።  የመጨረሻው ወንበር ላይ በመስኮቱ በኩል ጥግ ላይ ተቀምጬ ሁሉን አያለሁ።
የማለዳው ቅዝቃዜና የተሳፋሪው ትኩስ ትንፋሽ ተባብረው የቺኳንታውን መስታዎቶች ሁሉ ጉም አልበሰዋቸዋል። በ40ዎቹ መካከል የሚመስለው ጋቢ ነገር የተከናነበው ሹፌራችን ድምፁን ዝቅ አድርጎ ከኬኔዲ እኩል እየዘፈነ ወዝወዝ ይላል።
ተሳፋሪው ገሚሱ አንቀላፍቷል ገሚሱ ወግ ይዟል። እኔ ግን አደየ ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በህይወት ትቆየኝ ይሆን አይሆን ሳስብ እንቅልፍ ከአይኔ ሸሸ።
ከ8 ዓመታት በፊት ጎረቤታችን አለቃ ኪሮስ ወለደየሱስ ለዲማ ንግስ የመጡ ጊዜ “አይኔ ሳይታወር ጉልበቴ ሳይደክም መጠህ ካላመለኮስከኝ ከመቃብሬ ላይ እንዳትቆም። እረግምሃለሁ። እናት አለችኝ እንዳትል።”  በማለት የሰደደችልኝ መልዕክት ትዝ አለኝ።
ከዚያ በኋላ ስለአለቃም ስለእርሷም ሰምቼ ሰለማላውቅ ደህንነቷ ሀሳብ ገባኝ። ድጋሚ ትካዜ። አደየ ኖራ ይሆን?
መስኮቱን በሹራቤ አሸት አሸት አደረኩት
አገር ምድሩን የሰኔ ደመና ወሮታል። ራቅ ብሎ ከሚታየው በትላልቅ ዛፎች ከተከበበው ደብር ሸማ የለበሱ እመቤቶችና መኳንንቶች ይወጣሉ ይገባሉ። ሰንበት ነበር። የአቡየ ድርብ። ከወንበሬ ሳለሁ አሻግሬ ተሳለምኩ። ስለ አደየም ፀልይኩ።
ማንጁሶች በደቃቃ እግሮቻቸው ጤዛ የወረረውን መንገድ ሁሉ እየሮጡና እየተጯጯሁ ሩቅ ድረስ ይከተሉናል። ቅኔ ለመማር ከላስታ የመጡት ዲያቆናት ቁራሽ ዳቤ በመስኮቱ በኩል ይጥሉላቸዋል። ያቺን ይናጠቁና ደግመው ይከተሉናል።
ድክም ሲላቸው ደግሞ ጎንበስ ብለው በእጃቸው ጉልበታቸውን ተደግፈው እያለከለኩ ይቆማሉ።
የኋላውን መስታወት የሸፈነውን ከማርጀቱ የተነሳ ደርዙ አካባቢ ክሩ መበዝበዝ የጀመረውን መጋረጃ ገለጥ አደረኩት፣
ማንጁሶቹ ከሩቆ ቆመው የልጅነት ደማቅ ፈገግታቸውን አስቀድመው እጆቻቸውን በደህና ግቡ እያውለበለቡ ከኋላ ሲቀሩ ይታዩኛል። የኔታ ትዝ አሉኝ።
ልጅ ሳለን የኔታ ሀብተጊዮርጊስ የሚባሉ አንድ ቸር ሰው ነበሩ። ታዲያ የኔታ ሰፈራችን የመጡ እንደሁ ምድረ ማንጁሶች ግር ብለን እንከተላቸዋለን። ደብር ድረስ።
“እስኪ አቡጊዳ በሉ” ይሉናል
ሰባብረን እንልልላቸዋለን
“ሸጋ! አሁን ደግሞ መልዕክተን ውጡት” ይሉናል
እንዲህ እንዲያ እያልን ደብር እንደርሳለን።
“ልጆች እዚህ ቁጭ በሉና ጠብቁኝ” ይሉንና እኛን ዋርካው ጥላ ስር ተተውን መቃብር ቤታቸው ይገባሉ። ወዲያው ሰፌድ ላይ የተነጠፈ ሳለነክ ይዘው ይወጡና እየቆረሱ ማከፋፈል ይጀምራሉ።
“የኔታ ከመቃብር ቤት ሲኖሩ ግን ሬሳው አይበላዎትም?” ይላቸዋል ኪሮስ
“እዝጌር ያጠብቀኛል” ይመልሳሉ የኔታ
“እዝጌር መጠበቅ ቢደክመውስ” ሌላ ጥያቄ ያስከትላል ደስታ
“ሂዱ ከዚህ ስራ ፈት ሁላ” ይላሉ የኔታ ዱላ ፍለጋ ዞርዞር እያሉ።
ሳለነካችንን እየገመጥን እየተሳሳቅን ወደ መቃብሮቹ እንሮጣለን።
በመቃብሮች መካከል ስንዘዋወር “አንድ ፎቶ አወጣሁ” ይላል ደስታ ከሟቾቹ ሀውልት ላይ ያለውን መስታወት በድንጋይ አርግፎ
“የኔ ፎቶ እንኳን የሽማግሌ ነው” ይላል በረከት እርሱም እንደደስታ አንዱ መቃብር ላይ ያለ ፎቶ በድንጋይ መስታወቱን አንኮታኩቶ።
በዛው ወደ ወንዝ እንወርዳለን። የዱር ፍሬ ስንለቅም እንውላለን። አሁን እነደስታ እነበረከት ምናምን የት ሆነው ይሆን?
የጡሩንባ ድምፅ ሰምቼ አሻግሬ ስመለከት በነጠላ የተከለለችውን ሙሽራውን በበቅሎ ጭኖ የሚሄድ ሙሽራን በርካቶች አጅበውት ጡሩንባ እየነፉ ሞሰብ ወርቅ ታቅፈው
“የሆም አበባየ
የሆም
የሆም አየበባ የሆም እኛም ፈቅደናል ይሁን” እያሉ አታሞ እየመቱ ሲሄዱ አለፍናቸው።
እንዳንድ እመቤቶች ደግሞ ሳቃቸውን በነጠላ ሸሽገው የቺኳንታውን ጎማ እያዩ ይሱቁና ዳግሞ ወደ አጀባቸው ይመለሳሉ። ደግመው ይዞሩና ጎማው ላይ አይናቸውን ተክለው ይደነቃሉ።
ብርኽቲ ትዝ አለችኝ። የልጅነት ፍቅሬ ብርኽቲ! ሙሽራየ ብርኽቲ! ንግስተ ሳባየ ብርኽቲ!
አንገቴ ላይ ያሰርኩትን የብር መስቀል ዳሰስ አደረኩት።
ከቀናት በአንደኛው አመሻሽ “ከእንግዲህ ወዲያስ ላንገናኝ ነው አለችኝ!” እንባዋ እየቀደማት።
“አትርሳኝ አልረሳህም” ብላ የብር ማተቧን በጥሳ አንገቴ ላይ አሰረችልኝ
አንዳች መብረቅ እንደመታው ሁሉ ክው ብየ ቀረሁ። ለምን? የሚለውን ጥያቄ ሳልጠይቃት እንባዋን እያዘራች በደነዘዝኩበት ጥላኝ ሄደች።
በሳምንቱ ላንዱ ባላጠጋ መዳሯን ሰማሁ። እንግዲህ ምን ቀረኝ?
 አደየን ብርኽቲንም ትቼ ተሰደድኩ። ለ16 ዓመታት በስደት ባዕቴን ዘጋሁ።
ከ7 ሰዓታት አድካሚ ጉዞ በኋላ ማለዳ ላይ አስመራ ደረስኩ።
ቀስ እያልኩ ተጉዤ ቤታችን ስደርስ እጥሩ ፈርሶ ጣራው ተነቃቅሎ ቤታችንም ዘሞ እንደመቃብር ቤት ያለ ዘግናኝ ጭርታም ወርሶት ነበር። አንዳች ፍርሃት በልቤ ላይ ሲሰፍር ታወቀኝ።
አደይ አልኩ። ከውጭ ቆሜ።
መልስ የለም
አንቺ አደይ። አልኩ ደግሜ። ድምጼ ደከመብኝ መሰል።
ጎረቤታችን እማማ ምንታምር ብቅ አሉ። ምንም ያክል ዘመኑ ቢከንፍ፣ የልጅነት ወዜ ከፊቴ ቢጠፋ ገብስማ ፂሜ ቢንዠረገግም ማንነቴን ከማወቅ ግን እንዳላገዳቸው ከድንጋጤአቸው ተረዳሁ።
እንዴት አሉ እማማ? አደየ የት ሄዳ ነው? አልኳቸው።
እንባቸው በጉንጮቻቸው ደረቶች ቁልቁል መውረድ ጀመረ…
Filed in: Amharic