>
1:32 pm - Monday June 5, 2023

የወላይታ ህዝብ ደም ይጮሃል (ደረጄ ከበደ)

የወላይታ ህዝብ ደም ይጮሃል

ደረጄ ከበደ

* የጉራጌውን ድምፅ አፈናውም ተጠናክሮ ቀጥሏል
 
የወላይታ ህዝብ ህገመንግስቱ እንደሚፈቅደው ክልል እንሁን ብሎ መብቱን በጠየቀ የአቢይ አስተዳደር ምላሹን በጥይትና  
እስከ 21 በሚደርስ የእሬሳ ክምር አስታቅፎታል!!!
 
መለስ ዜናዊ የወለደውን የዘርና የቁዋንቁዋ ክልል ዶ/ር አቢይ አህመድ አቅፎ እያሳደገለት ነው። ያላወቀው ነገር ቢኖር ግን ይህ እሽሩሩ የሚለው አውሬ አድጎና ገዝፎ አንድ ቀን ራሱን መልሶ እንደሚበላው ነው።
የወላይታ ህዝብ ህገመንግስቱ እንደሚፈቅደው ክልል እንሁን ብሎ መብቱን በጠየቀ የአቢይ አስተዳደር ምላሹን በጥይትና
እስከ 21 በሚደርስ የእሬሳ ክምር ሰጥቶታል።
ጥፋታቸው ምን ነበር? ህገመንግስቱ ባሰፈረው አሰራር መሰረት የክልልነት መብታቸውን ስለጠየቁ አምባገነናዊው መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱን በቅፅበት ልኮ አመራሮቹና ሽማግሌዎች  በወላይታ ባህል አዳራሽ በስብሰባ ላይ ካሉበት አፍሶ ሲወስዳቸው በተፈጠረው ብጥብጥ በውል ያልታወቀ ቁጥር ያላቸው በርካታ ሰዎች የጥይት እራት ሰለባ ሆነዋል። የፓርላማ አባላቱ ርእሰ መተዳደሩን ጨምሮ ዛሬ በእስር ላይ ይገኛሉ። ይህን ምን እንበለው ከግፍና ከምን ያመጣሉ ሌላ ???
በአቢይ መንግስት የተወሰደባቸውን አላስፈላጊ እርምጃ ስሰማ አንድአንድ ጥያቄዎች ወአእምሮዬ መጡ፣ምነው ቄሮ ባለፉት ሳምንታት ቤት ለቤት እየዞረ ህዝብ ሲያርድ ወንጀሉን ለማስቆም መከላከያው  እንዲህ አልፈጠነ??? አቢይ ባለፈው ሶስትና አራት  ሳምንታት ያልነበረውን አቅም ዛሬ ለወላይታ ወረራ ከየት አመጣው? ሰራዊቱንስ በምን ፍጥነት ማስማራት ቻለ? ትዝ ቢለን በዚሁ አመት ፋኖን ለማፈን ላደረገው ዘመቻ አስተዳደሩ በአማራ ክልል ላይ ታንኩን ረጭቶ ነበር። ነገሩን ለታዘበው ከትግሬውና ከኦሮሞው ክልል ውጭ በሌሎች ክልሎችና ብሄሮች ላይ ዶ/ር አቢይ ጡንቻውን ከማሳየት ዘግይቶ አያቅም። የትግሬ ክልልም የታጠቀ ባይሆን ኖሮ አይቀርለትም ነበር። የደብረፅዮን ታላቁዋ ትግራይ (የአማራውን እርስቶች ወደራሱ አካሎ የገነባት ትግራይ) በቁጥር ከፌዴራል ሰራዊቱ ባልተናነሰ ብዛት ያለው ልዩ ሃይል አላት። ይህንን ጠንቅቆ የሚያውቀው አቢይ ወንጀለኞች የታጨቁባትን ትግራይን አይደፍርም።ጨዋታን ጨዋታ ያመጣዋልና የኦሮሞ ክልል ለ 31ኛ ጊዜ የታጠቁ ልዩ ሃይሎችን አስመርቆአል። የአቢይና የትግራይ አመራሮች የጋራ ጠላት ያደረጉት አማራ ግን በጀግናው ጄነራል አሳምነው ፅጌ አማካኘነት አንድ ዙር ልዩ ሃይል ቢያስመርቅ፣ ወሎ ላይ ጠ/ሚኒትር አቢይ አይኑን በጨው አጥቦ ለልማት የተሰጣችሁን በጀት ልዩ ሃይል እያሰለጠናችሁበት ታባክኑታላችሁ ብሎ በአማራው ክልል ላይ ነቀፌታ ያቀረበው ትዝ ይለናል። በዛን ጊዜ የኦሮሞ ክልል ከአማራው ሲነፃፀር በአስር እጥፍ በሚበልጥ ቁጥር የራሱን ልዩ ሃይል አስመርቆ ነበር። አማራን ቀጥቅጦ ለመግዛት ባላቸው እቅድ መሰረት አማራው የራሱ ሃይልና አቅም እንዳይኖረው ታስቦ ጠ/ሚኒስትሩ እነ ዶ/ር አማባቸውንና እነጀነራል አሳምነው ፅጌን ወሎ ላይ በነቀፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ከሌሎች ባልደረባዎቻቸው ጭምር ተገደሉ። የእነሱም ደም ይጮሃል።
ባለፈው ሲዳማ ክልል ሲሆን በፃፍኩት አርቲክል ላይ ህዝቡ ክልል የመሆን መብቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ክልል መጥፋት ሲገባው እየጨመረ መሄዱ እንዳሳዘነኝ ገልጬ ነበር። ዛሬም የችግራችን መንስኤ የሆነው ኤትኒክ ፌዴራሊዝም የሚወድመው ክልሎች በሙሉ ፈርሰው ሀገራችን በሌላ ምንገድ ስትዋቀር ብቻ ነው።  ያን ካልኩ በሁዋላ ግን የወላይታ ህዝብ እንደአማራው፣ እንደኦሮሞው፣ እንደሲዳማው፣ እንደአፋሩ፣ እንደቤኒሻንጉሉ፣ እንደ ትግራዩ፣ እንደሶማሌው ወዘተ ክልል የመሆን መብቱን ማንም ሊከለክለው አይችልም/አይገባም።
ሌላው በአደጋ ላይ ያለ ብሄር የጉራጌ ብሄር ነው። ክልል የመሆን ጥያቄ በይፋ ያቀርባል ተብሎ ይጤበቃል። ጥያቄው ግን እንዳይነሳ የአቢይ መንግስት ለማፈን እስርና እንግልት እያካሄደበት ነው። የጉራጌ ህዝብ መብት ይጠበቅ እንላለን።
ደጋግሜና አስረግጨ መናገር የምፈልገው ግን ሃገራችን እዚህ ማጥ ውስጥ የገባቸው፣ ህዝባችንም ከኑሮው መፈናቀልና ህይወቱን ማጣት የጀመረው  በዘርና በቁዋንቁዋ ላይ የተመሰረተ ክልል ከተገበረበት ሰእትና ደቂቃ ጀምሮ መሆኑን ነው። ስለዚህ ይህንን ስርአት ከአንቀፅ 39 ጋር በአንድ ሳጥን ወደጥልቁ ልንቀብረው ይገባል።
እስከዛው ግን፣ ስርአቱ እስካለ ድረስ ግን፣ አንዱን ብሄር ክልል አድርጎ ሌላውን ብሄር መከልከል ፍፁም አይቻልም። ስለዚህ የአራዊቱ ህገመንግስት ያስቀመጠውን  መመሪያ ተከትሎ የክልልነት ጥያቄ ላቀረበ ብሄር ሁሉ ለጥያቄው ተገቢውን መልስ መስጠት እንጅ በነዋሪዎቹ ላይ የጥይት ናዳ ማውረድ በፋሺሽታዊ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ማወቅ ያስፈልጋል።
የክልልነት ጥያቄ ገና በገፍ ይቀርባል።ቁጥር ስፍር የሌለው ብሄረሰብ መብቱን መጠየቁ አይቀርም፣ የጫካው ህገመንግስት እስካለ ድረስ ደሞ አንዱ ብሄር ክልል ሆኖ ሌላው እይከለከልም። ስንቱን በጠመንጃ ዝም ማሰኘት ይቻል ይሆን?
በወላይታ በአቢይ የመከላከያ ጦር ጥይት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ነፍስ ይማርልን !!!!!
Filed in: Amharic