>

ንጉሠ  ነገሥቱ - ጥቁር ሰው (ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ)

ጉሠ  ነገሥቱ – ጥቁር ሰው

ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ

በዓለም ላይ ዝናቸው የታወቀው አጤ ምኒልክ ዝናቸውን ያገነኑት በሥራቸው እንጂ በዘራቸው አልነበረም። ሹመት በዘር እንጂ በሥራ ባልነበረበት ዘመን የተገኙት ምኒልክ የሚሾሙት የተገላቢጦሽ ነበር። ሹመት በሥራ ብለውም ያወጁት ምኒልክ ናቸው።
ለዚህ ማስረጃ የሚሆን አንድ ምሳሌ… 
የንጉሥ ወልደጊዮርጊስ እናት ወይዘሮ አያህሉሽ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ልጅ ናቸው። በዚህ ምክንያት ምኒልክ እና ወልደጊዮርጊስ የታናሽና የታላቅ ልጆች ናቸው። ምኒልክ ንጉሥ ሸዋ ሲባሉ የደጃች ጎበና አሽከር ነበሩ። ምኒልክ ጎበናን ጠርተው “ወልደጊዮርጊስን ሥራና ውጊያ እንድታስተምረው አሽከር አድርጌ ሰጥቼሃለሁ” አሏቸው።
አቶ ወልደጊዮርጊስም በጎበና ቤት እያገለገሉ ብዙ የጀግንነት ሥራ ከሠሩ በኋላ ፊታውራሪ ተባሉ። ሀገር በማቅናት ተግባር የጎበና ተካፋይ ሆነው በመገኘታቸው ደጃዝማች ተባሉ።
በኋላም ራስ ተባሉ። እንዲህ እያሉ በሥራቸው አደጉ እንጂ ምኒልክ ወንድሜ ነው ብለው እንዲያው በዋልፈሰስ አልሾሟቸውም። ወንድማቸው ወልደጊዮርጊስ የሰው ቤት አሽከር በነበሩበት ጊዜ በጦርነት ተማርከው ቤተመንግሥት የሰለጠኑት የተለያዩ ብሔረሰብ የሆኑት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርስ፣ ደጃዝማች ባልቻ፣ ወህኒ አዛዥ ወልደጻዲቅና ሌሎችም የቤተመንግሥት ታላላቅ መኳንንትና አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ። ምኒልክ ሰውን በሥራው እንጂ በዘርና በጎሳው የማይሾሙ ነበሩ።
* ማንኛውም መኳንንት በየሀገሩ ላይ ከሚያገኛቸው የእጅ ሥራ አዋቂዎች መሀል የምኒልክን ድርሻ ወደ አዲስ አበባ እንዲልክ አዘዋል። ምኒልክም ለእነኚህ ከየሀገሩ ለሚመጡላቸው የእጅ ሥራ አዋቂዎች ከቤተመንግሥት ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለማረፊያ ሰጥተዋቸዋል። ምኒልክ እነዚህን ሠራተኞች ከሰበሰቡ በኋላ የእጅ ሥራ አዋቂዎች በኅብረተሰቡ ጥላቻ ከኅብረተሰቡ የተገለሉ ሆኑ። በዚህ የሚናደዱትም ምኒልክ አስደንጋጭ የሆነ ብርቱ አዋጅ አወጁ።
ሠራተኞን በሥራው የምትሰድበኝ ተወኝ። 
“ከዚህ ቀደም ብረት ቢሠራ ጠይብ፣ ሸማ ቢሠራ ሸማኔ፣ ቢጽፍ ጠንቋይ፣ ቤተክርስቲያን ቢያገለግል ደብተራ እያላችሁ አርሶ ነጩን ከጥቁሩ አምርቶ የሚያገባውን አራሽ ከዘውድ ይበልጣል የሚባለውን ገበሬ እያላችሁ፣ ነጋዴን ነግዶ ወርቁን ግምጃውን ይዞ ቢገባ አንተ ነጋዴ ገጣባ አጣቢ እያላችሁ፣ በየሥራው ሁሉ ትሰድባላችሁ፤ ልጁ ምናምን ሥራ የማያውቀው ሰነፉ ብልሁን እየተሳደበ አስቸገረ። ቀድሞም ይህ ሁሉ ፍጥረት የተገኘው ከአዳምና ሔዋን ነው እንጂ ሌላ ፍጥረት የለም።
ይህ ሁሉ ካለመማር የተነሳ ነው። አዳምንም ብላ በአፍ ገጽከ ብሎታል። ይህ ከቀረ፣ ሁሉ ቦዘንተኛ ከሆነ፣ መንግሥት የለ፣ ሀገር የለ።  በወዲያ ሀገር ግን በኤሮፓ ሁሉ አዲስ ሥራ አውጥቶ መድፍ፣ ነፍጥ፣ ባቡር ቢሠራ ሌላውንም እግዚአብሔር የገለጠለትን ሥራ ሁሉ ቢሠራ መሐንዲስ እየተባለ እየተመሰገነ ሠራተኛውም ብዙ ይጨመርለታል እንጂ በሥራው አይሰደብበትም። እናንተ ግን እንዲህ እየተሳደባችሁ ሀገሬን ባዶ ልታደርጉትና ልታጠፉት ነው።
እንግዲህ ግን እንዲህ ብሎ የተሳደበ እኔን የሰደበ ነው እንጂ ሌላውን መስደብ አይደለም። ዳግመኛ ግን ሲሳደብ የተገኘ ሰው መቀጫውን አንድ አንድ ዓመት ይታሰራል። ሹማምንትም አስረህ ዓመት ለማስቀመጥ የሚቸግርህ የሆነ እንደሁ አስረህ ወዲህ ስደድልኝ።”
ጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም
የንጉሠ ነገሥቱ እና የእቴጌ ዝክረ ልደት
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic