>

የምድራችን እውነት ይህ ነው...!!!   [በብርሃኑ ተክለ ያሬድ] 

የምድራችን እውነት ይህ ነው…!!!

    [በብርሃኑ ተክለ ያሬድ] 

•••
በመጀመሪያ የውሸት ትርክት በምድርህ ላይ ይዘራል ታዲያ የተዘራው የሚያበቅለው እህል አይደለም ሀውልት ነው፤ የጥላቻ ሃውልት… ሀገሩን እየመራን ነው የሚሉ ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት የሀሰት ትርክትና የጥላቻ ተረክ አረመኔዎችን ይወልዳል። ከዚያ ሰውነትህ ይረሳል በአረመኔዎቹ ህሊና ውስጥ አንተ ከዚህ ጥፋ ብለው የሚያባርሩህ ወንድምህን ፊት ለፊት በጀርባው እንደ በሬ የሚያርዱብህ አስከሬንህን እየጎተቱ ፎቶ የሚነሱብህ ሌላ አካል ትሆናለህ።
•••
ያየኋቸው ሰቆቃዎች ምናልባት እስከሞቴ ድረስ ከህሊናዬ አይጠፉም። በአንድ በኩል ከልጅነቴ ጀምሮ ሳነብና ስሰማ ያደኩት ስንክሳርና ገድለ ቅዱሳን ግዘፍ ነስቶ ለመሞት የተዘጋጁ ከማተባችን ይልቅ አንገታችንን በጥሱት የሚሉ አካላቸው ተቆራርጦ ለእሳት የተጣሉ በእንስሳ የተበሉ በድንጋይ የተወገሩ  በጦር የተወጉ እጅና እግራቸው ተቆርጦ እንደ ዋንጫ ተይዞ የተጨፈረባቸው ደማቸውን ውሻ የላሰው… በመመልከቴ የሰማእታቱን በረከት የታደልኩም በመሆኔ አምላኬን አመስግኛለሁ።
•••
በሌላ በኩል ደግሞ ባቀኑትና በገነቡት ሀገር ወገን አልባ ሆነው ሞት ታውጆባቸው የተጨፈጨፉና ንብረታቸው የወደመባቸው በየእለቱ እየተዛተባቸውና አሁንም ይገሉናል እያሉ እየነገሩን ህፃናቱ ብዛት ያለው ሰው ወደነሱ ሲሄድ ገዳዮቹ መጡብን ብለው የያዙትን እየጣሉ ሲሮጡ መመልከት ደግሞ ሞትን የሚያስመኝ ነው።
•••
አጋርፋ ላይ “ለምን እንታረዳለን?” እያለ እያለቀሰ ንግግር ያደረገው ልጅ ሲናገር ህፃናቱ ለብቻቸው ክብ ሰርተው እንደትልቅ ሰው ራሳቸውን ይዘው ያለቅሱ ነበር። ምሳ ሲበሉ እዚያው ነበርን አንዲት የ10 ዓመት ህፃን ምግቡን እየጎረሰች እምባዋ ይወርዳል፤ ሰው እንዳያይባት ታቀረቅራለች፤ እናም ከወዳጄ ጋር ወደእርሷ ሔጄ ለምን እንደምታለቅስ ጠየኳት። “አባቴ ትዝ አለኝ” ነበር መልሷ “አባትሽ ምን ሆነ?” አልኳት መልሷ አሰቃቂ ነበር “ጨፍጭፈው ገደሉት ቤታችንንም አቃጠሉት” አለችኝ እምባዋ እየወረደ ፊት ለፊቷ ላለማልቀስ ፊቴን አዞርኩ ከጀርባዬ የነበረው ፌዴራል ፖሊስ እምባው እየወረደ ነበር።
•••
ሌላ እናት (እናቴን ይመስላሉ) “ከወራት በፊት ልጄ ሞተችብኝ ጎረቤቶቼና የልጄ አብሮ አደጎች ለለቅሶዬ ቀሩ። ምን አጠፋሁ ብዬ ከልጄ ሀዘን በላይ አለቀስኩ ለካስ ሊያርዱኝ እያመቻቹኝ ነበር። በ23 ማታ ቤቴ መጡ ባሌ ‘የታለች ሚስትህን አምጣ’ ተባለ ለሽንት ቤት አስቆፍሬው የነበረ ጉድጓድ ውስጥ ዘልዬ ገባሁ። ከልጆቼ ጋር አዝዬ ያሳደግኩትን ልጅ ድምፅ ሰማሁ እሰይ እሱ ካለ ያተርፈኛል አልኩ። “ቤቷን እንዳትነኩ እንሰግድበታለን እሷን ፈልጉና ግደሉ” ሲል ሰማሁት። ባሌ እያለቀሰ ለምኖና ገንዘብ ሰጥቶ  የለችም ሮቤ ናት ብሎ መለሳቸው ንብረቴን ሁሉ ዘርፈው ሄዱ። 3 ቀን ሙሉ ሽንት ቤት ጉድጓድ ውስጥ ሆኜ አለቀስኩ። የት ነው ሀገሬ? ምን አጠፋሁ?” አሉኝ
•••
ህፃን ያዘለች በእጆቿም ህፃናት የያዘች ልጅ “ወደቤትሽ ተመለሽ ይሉኛል እንዴት ልመለስ? እኔም ባሌም ኦሮሞ ነን ኦሮሞ ብሎ ኦርቶዶክስ የለም ብለው ባሌን በሩ ላይ እኔና ልጆቹ ፊት እየጨፈሩና እየወጋጉ ከትክተው ገደሉት በመሬታችን ክርስቲያን አይቀበርም ብለውን 3 ቀን ሙሉ ህፃናቱ እያዩት ውሻና ጅብ በላው አሁን ህፃናቱ አእምሮአቸው ልክ አይደለም መልሼ እዚያው ቤት ይዣቸው ገብቼ ለይቶላቸው ሲያብዱ ልይ? በመኪናችሁ ውሰዱኝና ሌላ ሀገር ጣሉኝ ለምኜ ልብላ”አለችኝ ራሴ ሊፈነዳ ነው። አቅመ ቢስነት እየተሰማኝ ጥያት መጣሁ።
•••
በአሳሳ አንዲት ወጣት ጥበቃ ይሰሩ የነበሩ አያቷ አቶ ተፈሪ ከሚሠሩበት ቦታ ተጠርተው ከባለቤታቸው ጋር በድንጋይ ተደብድበው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እያለቀሰች ስትናገር ቆሜ ተመለከትኩ። እነዚህ ቀላሎቹ ናቸው ሌላው ከአእምሮ በላይ ነው ለታሪክ ይቀመጥ አምላከ ንፁሀን መድኃኔዓለም ይፍረድ
•••
ይህን በመናገራችን ልታስፈራሩን የምትሞክሩ አራጆች እንኳን እውነተኛውን ሰቆቃ ተመልክተን ቀርቶ ሌላውንም የምንፈራ አይደለንምና ራሳችሁን አስፈራሩ።
•••
ይህን ሁሉ ግፍ eotc ና ማህበረ ቅዱሳንን ጨምሮ ሁሉም ሚዲያዎች በካሜራቸው አስቀርተውታል። ይህን ድምፅ ማፈን ከገዳይነት አይለይም። እውነቱን እንነጋገርና መፍትሄ እናምጣ፤ ንፁሀኑ ዛሬም ማስፈራሪያ እየደረሰባቸውና ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸው ውጡ እየተባሉ ነው። የንፁሀኑ ደም ይጮሃል።
••• በማለት የአይን ምስርክነቱን ሰጥቶ ሃሳቡን ቋጭቷል።
-አማራ
-ተዋሕዶኦርቶዶክስክርስቲያን
-የኢትዮጵያተዋሕዶኦርቶዶክስቤተክርስቲያን
Filed in: Amharic