>

ወይሐረር፣ ወይ ሐረር . . . ወይ ጊዜ፣ ወይ ጊዜ! (አሠፋ ሀይሉ)

ወይሐረር፣ ወይ ሐረር . . . ወይ ጊዜ፣ ወይ ጊዜ!

አሠፋ ሀይሉ

አንዳንዶች ጊዜ ሁሉን የሚያሳይ መስታወት ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ጊዜ የሚያነሳና የሚጥል አድራጊ ፈጣሪ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ጊዜ ነገሮችን መዝግቦ የሚይዝ ትልቅ የህይወት ማኅደር ነው ይላሉ፡፡ ምናልባት ጊዜ ታዛቢም ይሆናል፡፡ ሁሉን እየታዘበ የሚያሳልፍ የሰዎች አኗኗሪ ይሆናል ጊዜ፡፡ ለመነሳትም ጊዜ አለው፡፡ ለመውደቅም ጊዜ አለው፡፡ ለመታወስም ጊዜ አለው፡፡ ለመረሳትም ጊዜ አለው፡፡ ለመክበርም ጊዜ አለው፡፡ ለመዋረድም ጊዜ አለው፡፡ ለመኖርም ለመሞትም ጊዜ አለው፡፡ ለጨለማም ለንጋትም ጊዜ አለው፡፡ ጊዜ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ እንዳለው ጠቢቡ ሠሎሞን፡፡ ለሁሉም ግን የየራሱ ጊዜ አለው፡፡
ስለ ጊዜ ያመራመረኝ ምንድነው? ይህ በ70ዎቹ መጨረሻ ላይ የተነሣ የሐረር በር (ዱክ በር) ፎቶግራፍ ነው፡፡ በስተቀኝ በኩል ወደ ሸዋበር፣ በስተግራ ወደ በርበሬ በር፣ ፊት ለፊቱን በአንደኛ መንገድ ሲዘልቁ ደሞ መድኃኔዓለምን ወረድ ብሎ ወዳለው ፈላና በር ያወጣል፡፡ በዚህ ዱክ በር ገብተን በመቶዎቹ ኮሪደሮች፣ በሰባቱም በሮች ተሸለክልከን አድገንበታል በልጅነት፡፡ ከበሩ ገባ እንዳልክ በግራ በኩል የነበረውን ሐራምቤ ሆቴል አስታውሰዋለሁ፡፡ ከእርሱ ወረድ ብሎ የእስላም የግመል ሥጋ ቤት፣ የእስላም የበሬ ሥጋ ቤት፣ እና ቸሩ የክርስትያን ሥጋ ቤቶች አይረሱኝም፡፡ በጠዋት 12፡00 ላይ ተነስቼ እየበረርኩ በስተቀኝ በኩል እታጠፍና መናኸሪያ ፊት ለፊት ተደርድረው ከባቢሌ እና ከኮምቦልቻ ያስመጡትን የተፈለፈለ ለውዝ በሺሪሚሪ ጣሳ እየሰፈሩ ከሚሸጡ የሐረር ሴቶች ላይ ሁለት ሶስት ጣሳ ለውዝ ገዝቼ በመጣሁበት ፍጥነት እፈተለካለሁ፡፡ ወደየት?
የምፈተለከው የሥላሴ ቤተክርስትያንን ደጃፍ ከጥይት በፈጠነ ማማተብ ተሳልሜ፣ ከወልዴ ጠጅ ቤት አለፍ ብሎ፣ ከሎዝ ጊቢ ተጎራብቶ ወደሚገኘው ወደ ቀበሌ አስር (የአደሬ ጢቆ) ዳቦ ቤት ነው፡፡ የዳቦ ሠልፍ ከመያዜ በፊት ፈጠን ብዬ ለውዜን ከነፌስታሉ ለዳቦ ጋጋሪዎቹ መስጠት ይጠበቅብኛል፡፡ ዳቦ ቤቱ ለቀበሌው ህዝብ አዳራሽ በሚያህል ምጣድቤቱ (ኦቨኑ) ዳቦ ጋግሮ ሲጨርስ – 50 ሣንቲም ይሁን ወይ ስሙኒ ይቀበልና በበረደው የዳቦ ምጣድ ላይ ለውዝ ይቆላልሀል፡፡ ለውዝ እሳት ሲበዛበት አይወድም፡፡ በበረደ የቀበሌው የዳቦ መጋገሪያ ምጣድ ላይ ሲዘረር – አቤት የለውዙ ጣዕም፡፡ ከዚያ በብርሃን ፍጥነት ከዳቦ ቤቱ በቤተሰብ ቁጥር ልክ እያንዳንዱን በ0.10 ሣንቲም ሂሳብ የሚሸጥልንን ግብዴ ባለ ሁለት ጡት ዳቦ ከይርጋዬ ወይ ከፍቅርተ ወይ ከጋሽ መርሻ ላይ በአንደኛው የዳቦ ቤት መስኮት በኩል ሰልፌን ጠብቄ እረከባለሁ፡፡
የቤተሰባችን ቁጥር 6 ነበር፡፡ እኔ፣ ሶስቱ እህቶቼ፣ እናትና አባቴ፡፡ ሌላ ሰው ቤት ውስጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የቀበሌ የዳቦ ካርድህ ላይ የቤተሰብ ቁጥርህ የሚናገረው በቤትህ 6 ሰዎች እንዳሉ ስለሆነ የሚሸጥልህ 6 ዳቦ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘመድ መጥቶ ካነሳችሁስ ዳቦ? ወንድሜ! መላ ትፈጥራለሃ! ለምሳሌ እናቴ እንጀራ ፍርፍር ታፈረፍርና ዳቦ በዙሪያው እየተቆረሰ ማባያ ይሆናል፡፡ ልብ በል፡፡ አንድ ዳቦ ሁለት ቦታ ሲከፈል – በቤቱ 12 ግብብዴ ጡቶች ያሉት የዳቦ ክፋይ ተገኘ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ በሰልፍ ዳቦ ገዝተው እዚያው ትርፍ ለሚፈልግ 0.10 ሣንቲም ጨምረው ከሚሸጡልህ ተርብ የአየር ባየር አትራፊ ልጆች ላይ ማሟያ ዳቦህን ገዝተህ ወደቤትህ መመለስ ግድ ይልሃል፡፡
የዳቦ ሰልፍ ዋዛ አልነበረም፡፡ ዳቦዬን ከዳቦ ቤቱ ፊት ለፊት መስኮት ተረክቤ፣ ለውዜን ደሞ ከዳቦ ቤቱ ጓሮ በር ሹልክ ብዬ ተረክቤ – ወደ ትምህርት ቤቴ ከመሄዴ በፊት የሚጠበቅብኝን የጧቱን ሐረራዊ ግዳጄን ተወጥቼ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ፡፡ ልብ በል፡፡ አንዳንዴ ተሰልፈህ፣ ተሰልፈህ ዳቦ አለቀ ልትባል ትችላለህ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ከሎዝ ጊቢ፣ ወይ ደሞ ከእማማ ማሚቴ ቤት አንዱን በስሙኒ ‹‹ጢቢኛ›› ገዝተህ ቤትህ ለሚጠባበቁህ በላተኛ ቤተሰቦችህ ማድረስ አለብህ፡፡ ከቀበሌ በ0.10 ሣንቲም ከሚሸጠው ዳቦ ወደ 0.25 ሣንቲም ወደሚሸጠው ጢቢኛ ስትገባ – ቤተሰብህን በያንዳንዱ ጢቢኛ 0.15 ሣንቲም እያከሰርክ መሆኑን ሳትዘነጋ ነው ታዲያ፡፡ አንዳንዴም ሰልፉ በዳቦ ቸርቻሪ ነጋዴዎች የተጨናነቀ ስለሆነ ለልጅ አይሆንም እንጂ – ወደ ቀበሌ 14 (ማለትም ወደ ቦቴ ሠፈር) የምወርበትም ጊዜ አለ፡፡ ቆስጣ የሚባል ዳቦ ቤት ነበር፡፡ ቆስጣ ዳቦ፡፡ ባይኔ ላይ መጣብኝ!
ቆስጣ ዳቦ በዘይት የተለበለበ አንጀት አርስ ዳቦ ነው፡፡ መልኩ ኢጣልያዊ፣ ሁለነገሩ ኢትዮጵያዊ እና ሐረሬ የሆነው ክልስ የሐረር ሰው የእነ ሪኮ እና ቤተሰቦቹ ዳቦ ቤት ነበር መሰለኝ ቆስጣ፡፡ ምናልባትም የመጀመሪያው አጠራር ‹‹ኮስታ›› ይሆናል፡፡ ከዚያ ሰዉ ‹‹ቆስጣ›› ብሎት ቀርቶ ይሆናል፡፡ አበሻ ሲባል ለምን ‹‹ቀ››ን ፊደል እንደሚወድ አይገባኝም፡፡ ኮንስታንቲን የሆነው ወደ ሀበሻ ሲመጣ – ቆስጠንጢኖስ ይሆናል፡፡ ሳይፕረስ የሆነው ወደ ሀበሻ ሲመጣ ቆጵሮስ ይሆናል፡፡ ሶክራተስ ወደ ሀበሻ ሲመጣ ሶቅራጠስ ይሆናል፡፡ በዚህ አያያዛችን ለምን የምድር የኬክሮስና የኬንትሮስ መስመሮች ወደ ሀበሻ ሲመጡ ቄቅሮስና ቄንጥሮስ ተብለው እንዳልተሰየሙ ግራ ይገባኛል፡፡ ምናልባት ቆስጣ ዳቦ ብቻ ሳይሆን ይሄ ሠላጣ የምንለው ተክል ወደ ሀገራችን ሲመጣ ስሙ ‹‹ሶላታ›› ይሆንስ ይሆን? ቆስጣስ ቅድመ ስሙ ኮስታ ይሆን? ወንድሜ ለፍልስፍና ጊዜ የለም፡፡ አሁን ነፍስ-ግቢ ነፍስ-ውጪ የዳቦ ሰልፍ ተጋድሎ ላይ ነኝ፡፡
የሆነ ሆኖ ቆስጣ ዳቦ ቤት የቀበሌ መታወቂያ አያድንህም፡፡ ጥሩ ሰልፍን ፈልቅቆ የመግባትና ሰልፈኛው ቢገፋህም ግድግዳው ላይ ተጣብቆ የመቅረት ሸረሪታዊ ችሎታም ያስፈልግሃል፡፡ ከ‹‹ስግብግብ ነጋዴዎች›› ጋር እየተጋፋህ መሆኑን አትርሳ፡፡ ቶሎ ከቆስጣ ዳቦ ገዝተው ሸዋበር ወይ በየሰፈራቸው ባለ ሱቅ ወስደው በእያንዳንዱ ዳቦ 0.10 ሣንቲም ወይም 0.20 ሣንቲም አትርፈው ቶሎ ለቁርስ በላተኛ ለመቸብቸብ ይጣደፋሉ፡፡ ጊዜ የላቸውም፡፡ እና ባለ በሌለ ኃይላቸው ይገፈትሩሃል፡፡ ሲገፈትሩህ – እመነኝ መልሰህ የመገፋተር ጉልበት አይኖርህም፡፡ ስለዚህ እንደ ሸረሪት ወይ እንደ እንሽላሊት ወይ እንደ ፈለግከው ዓይነት ነፍሳት ግድግዳው ላይ ሙጭጭ ብለህ ከሰልፍህ ላለመፈናቀል መጋደል አለብህ፡፡ ለዳቦ፡፡ ይህ ለውቡ የቆስጣ ዳቦ በማለዳ የሚከፈል መስዋዕትነት ነው፡፡ ቤተሰብህ ይሄንን አለማወቁ በጀው፡፡ ምናለባቸው፡፡ ከተጋድሎህ መልስ የዕለቱን ቆስጣ እያደነቁ – ከማብላላት ወዲያ ምናለባቸው እቴ!
በሌሊት ተሰልፈህም ያን ዳቦ ላታገኘው ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም በጧት ገዝተህ፣ በጧት ወደ ትምህርት ቤትህ የመሄድ ተደራቢ ግዴታም አለብህና ከተወሰነ ሰዓት በላይ ለቆስጣ ዳቦ የምትቸረው ጊዜ የለህም፡፡ ስለዚህ አንተም እንደ ነጋዴዎቹ ባለ በሌለ ኃይልህ ለዳቦ መሟሟት አለብህ፡፡ አሊያ ደሞ እንደማይሆንልህ ስታውቅ አንገትህን ደፍተህ ሹልክ ብለህ ከሰልፉ ትወጣና በቦቴ ወደ ህይወት ፋና፣ ወደ ፖሊስ ሆስፒታል በሚወስው አቋራጭ መንገድ እንደ ንፋስ ሽው ብለህ ወደ ሸዋበር ትወርድና – ከሸዋበር የችርቻሮ ዳቦ ወይ የችርቻሮ ጢቢኛህን ገዝተህ ወደ ቤትህ በተሸነፈ ልብ ታዘግማለህ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ብዙ ቤተሰቦች የሸዋበርን ዳቦ፣ የሸዋበርን እንጀራ፣ የሸዋበርን በርበሬ፣ የሸዋበርን ሽሮ መግዛት አይወዱም፡፡ አለሌነት ይመስላቸዋል፡፡
ወንድሜ አንድ የረሳሁት ነገር… ድንገት ሳትታዘዝ ለቤተብህ ቁርስ አስበህ… የቆስጣን ዳቦ ለሚጠብቀው ቤተሰብህ… የሸዋበርን ወፍ ዳቦዎች ገዝተህ ቤትህ ሰከም ሰከም እያልክ ከገባህ ምስጋናን አትጠብቅ፡፡ እንደ ቀኑ ምርቃትም እርግማንም ሊወርድብህ ይችላል፡፡ ቀንህ ነው የሚያወጣህ፡፡ ወይ ‹‹ወፍ›› ነው የሚሉት? በቃ ወፍህ ነው የሚያወጣህ፡፡ በቀኝህ ተነስ ያላለህ ዕለት… ‹‹ዓይንህ እያየ አቧራ እየቦነነበት የሚውልን ዳቦ እንዴት ዳቦ ብለህ ከሸዋበር ገዝተህ ትመጣለህ? ትተኸው አትመጣም? ዳቦ ካልበላህ ትሞታለህ? ከርሣም!›› የሚል የማለዳ እርግማንም ይጠብቅሃል፡፡ እንዲህ ያሉ የጧት በረከቶችን ያስተናገድኩባቸው ቀናት ቀላል አይመስሉኝም፡፡ ወንድሜ – ረጋሚም እኮ ሲገኝ ነው፡፡ ያሁኑን አላውቅም! በኛ ዘመን የልጅ አስተዳደግ እርግማን እንደ ምርቃት ነበር፡፡
ወገኛ እና ወገኝነት የለም በኛ ጊዜ የልጅ አስተዳደግ! ወይም እንደዚያ ይመስለኛል ሳስበው፡፡ ታዲያ ቤተሰብህ ‹‹አይ ላቭ ዩ እሺ የኔ ማር!›› እያሉ እንደሚሞላቀቁት የዘመኑ ወላጆች ‹‹የኔ ማር፣ ሆድዬ፣ እያሉ…፣ ኤሎሄም፣ ኤልቤቴል፣ ኖኤል፣ ምናምን የሚል ስም እያወጡ…፣›› እንዲያሳድጉህ ጠብቀህ ነበር?! አታስቀኝ ወንድሜ! ያውም በሐረር?! እውነቱን ነው የምነግርህ፡፡ ፍቅሩ አልጠፋም፡፡ ነገር ግን ነገር ማካበድ የለም እኛጋ! ልክ ልክህ እስኪበቃህ ይነገርሃል! እና እንደ ቻንስህ ኮምበርህን ጥለህም፣ ጨርቅህን ጥለህም፣ ወይም የሆነ ነገርህን ጥለህ ብቻ ታድጋለህ! ከላስ! ይሄ ነው የሐረር ልጅ አስተዳደግ፡፡ ሐረር እንደዚያ ነው! (በነገራችን ላይ ለሰው ሁሉ የምመክረው ሀቀኛው አስተዳደግም ያ ይመስለኛል! አንዳንዴኮ ማስመሰልና መሸነጋገል ምን ያህል እንደሚመረኝ! ኡዉዉዉዉይ….!! ሀቅ ሀቅህን፣ መሸጫ መሸጫህን እየተነገረህ ማደግማ – ምርቃት ነው! በእውነት?!!)
አሁን ይህን ሁሉ ትዝታ የጎለጎለብኝ ይሄ የሐረር በር ምስል ነው፡፡ የሐረር በር፡፡ ለእኔ ደግሞ ለሰፈሬ በጣም ቅርብ እና ከሁሉ ነገሬ ጋር የተያያዘ የልጅነት ጎዳናዬ ነበር፡፡ ከልጅነት ዘመኔ ብዙ ጊዜ የተመላለስኩበት በር – ከቤታችን በር እና ከትምህርት ቤቶቼ በሮች ቀጥሎ ምናልባት ይሄ የሐረር በር ከፍተኛውን ምልልስ ያስተናገድኩበት በር ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ብዙ እጅግ ብዙ ነገር ነው የሚያጭርብኝና አንዱ ነገር አንዱን ትዝታ እየጎለጎለ ማለቂያ የለውም፡፡ እና በዚሁ ላቁመው፡፡ የሐረር ልጅ ተሆኖ ይቅርና የሐረርን መሬት የረገጠ ማንኛውም አላፊ መንገደኛ ይህን ወደ ጀጎል የሚያስገባ ዋና በር ሳያስተውለው ካለፈ በትክክል ተኝቶ (ወይም ክፉኛ መርቅኖ) ነበር ማለት ነው፡፡
እንደ መታደል ሆኖ በዐዋቂነት ዘመን ፍለጋዎቼ ያገኘኋቸው የዚህን በር ጥንታዊ ገጽታዎች የሚያስቃኙ፣ የበሩን ሊፈራርስ የደረሰ ጥንታዊ ገጽታ የሚያሳዩ ጥቂት ፎቶግራፎች በእጄ ላይ አሉኝ፡፡ በ1500-1550 ዓመተ ምህረት እንደተገነባ እንሚነገርለት ልክ እንደ ጀጎል ግንብ ታሪክ ሁሉ፣ የዚህ ዋና ቅፅሩ አገነባብ ታሪክም ጥንታዊ ነው፡፡ ቢያንስ 450 ዓመት ይሆነዋል ማለት ነው፡፡ የጥንታዊው በር ከዚህኛው ጋር ይመሳሰል እንጂ ፈጽሞ የተለየ ነበር፡፡ ያኛው ሲፈርስ ይህንን በር በዚህ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስገነቡት ልዑል ራስ መኮንን ናቸው፡፡ እርሳቸው ያስገነቡት ደግሞ ሲያረጅና ተሰነጣጥቆ ሲፈራርስ ደግሞ ልጃቸው ግርማዊ ጃንሆይ (ቀኃሥ) ደግመው አሠሩት በሩን፡፡ እርሱም ደግሞ እንዲሁ አርጅቶ በጎንና በጎን በኩል መፈራረስ ሲጀምር፣ የመንጌ ወታደራዊው መንግሥት በበኩሉ የራሱን አሻራ አሳረፈበት፡፡ ከጎንና ከጎን በኩል ያሉትን ከመሬት ሽቅብ ወደ ላይ የተዘረጉትን ተደራራቢ ሆሪዞንታል ቅርጾች ጨምሮ በግሩም ሁኔታ አድሶ አስገነባው፡፡
አንዳንዴ ሳስበው – እንዲህ እንዳሁኑ ታሪክን ማጥፋት የኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ሳይሆን በፊት – ይሄ የጀጎል መግቢያ ዱክ በር ራሱ ትልቅ የታሪክ ቅብብሎሽ ምስክር ሆኖ ፊታችን ቆሞ የሚከሰን ይመስለኛል፡፡ በጥንት ዘመን ኢሚር ኑር አሰሩት፡፡ ከዚያ ልዑል ራስ መኮንን አሰሩት፡፡ ከዚያ ግርማዊ ጃንሆይ አሰሩት፡፡ ከዚያ መንግሥቱ ኃይለማርያም አሰራው፡፡ አልገባንም እንጂ – ይሄ – ጥፋትና መጠፋፋት የሌለበት ትልቅ የታሪክ ቅብብሎሽ አኩሪ ታሪካችን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው?
እና ታዲያ እሺ ይሁን – ጓድ መንግሥቱ የታሪክ አደራውን ተቀብሎ ይህን በር በልዩ ሁኔታ አሰርቶታል፡፡ ግን እዚህ የጀጎል ግንብ ላይ ምን ፊጥ አደረገው? የራስ መኮንን ኃውልት ፊት ለፊት፣ በልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ጎን፣ በሐረር የጦር አካዳሚ መማሪያ ክፍሎች ጎን በተገነባው በኢሠፓ ጽ/ቤት በር ላይ በትልቁ የተሰቀለ የኮሎኔል መንግሥቱ ሰማያዊ የኢሠፓ ኮት ቀይ መስመሮች ካሉት ጠቆር ያለ ክራቫት ጋር አስረው የሚታዩበት ስዕላቸው ነበረ፡፡ ወያኔ ገብቶ ራሱ በነጭ ቀለም አልጠፋ ብሏቸው ደብዝዞም ይታይ ነበር ለብዙ ዓመት፡፡ እና አባባሌ ያኔስ በመንጌ ጊዜ ራሱ – መንጌ በሁሉ ሥፍራ ፎቶው ነበር – እና ቢቀርበትስ በጀጎሉ ግንብ ላይ መንጦልጦሉ?! …. ወይ ጉድ… ወንድሜ! ነገሩ እኮ ቂብ ማለትን የማፍቀር ጉዳይ አይመስለኝም! ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት ጉዳይ ነው! ብሔራዊ ስሜት እስካፍንጫቸው የሞላባቸው የወቅቱ የሐረር ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች ናቸው የቆራጡን መሪ የጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ምስል አምጥተው የሐረር በር ላይ የገደገዱት፡፡
እሺ የመንጌስ ይሁን! እነዚህንስ ከመንጌ ግራና ቀኝ ያሉትን ሁለት ፀጉረ ልውጥ ሰዎች ምስልስ ምን አመጣው? ወንድሜ! አሁንም አትሸወድ፡፡ ማሽቃበጥም አይምሰልህ፡፡ የዚአድባሬዋ ሶማሊያ በሐርጌሣና በኦጋዴን በኩል ወርራን ሐረርን በመድፍ ስታስጨንቅ – አለሁ ብለው፣ ወገን ሆነው፣ እኛን ከሶማሌ ጥቃት ሊመክቱ ባህር ተሻግረው የደረሱልን ባለውለታዎቻችን ናቸው እነዚህ ፀጉረ ልውጥ መሪዎች፡፡ በነገራችን ላይ እስከእኔ ዕድሜ ድረስ በሐረር የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ላይ የዚአድባሬ ሶማሊዎች የተኮሱት መድፍ ጥይት ሳይፈነዳ በሰማዕቱ ጊዮርጊስ ተዓምር በሩ ላይ ተቸክሎ የቀረውን በያመቱ የጊዮርጊስን ዓመታዊ ክብረበዓል ልናከብር ተራራውን በወጣን ቁጥር እንደጉድ እየተደመምን እናየው ነበር!
እውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተዓምር ነበር ወይ የሶማሌውን መድፍ ያከሸፈው? ወይስ የተኳሹ የማነጣጠር ብቃት ጉድለት? ወይስ የዕድልና የአጋጣሚ ግጥምጥሞሽ? – ወንድሜ ለእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ቁርጥ ያለ መልስ ለማግኘት ራስህን አታስጨንቅ፡፡ እኔ እንደ ሰማዕቱ ፈረሰኛ ተዓምር አድርጌ ወሰድኩት፡፡ አንተ ደሞ እንደፈለግክ አድርገህ ውሰደው፡፡ ዋናው ነገር የዚአድባሬ መድፍ በሐረሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ላይ ተተኩሶ ተምዘግዝጎ ሄዶ ዒላማውን ካገኘ በኋላ በሆነ ያልታወቀ ምክንያት ሳይፈነዳ በቤተክርስትያኑ ቅጥር ፊት ለፊት እንደተቸከለ እኛ እያየን እንድንደመምበት መቅረቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሐረሩን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሳስብ ሁልጊዜ አንዲት በሐረር አራተኛ ሠፈር የስመ ጥሩው የግሩም ጋይንት ሆቴል ባለቤት የነበረች ሴት ወይዘሮ ሁሌም ትዝ ትለኛለች፡፡
ያች ሀብታም ወይዘሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት በየዓመቱ ስለት ነበራት፡፡ የሽቶ ስለት፡፡ እና በምዕመኑ ሁሉ ላይ ልዩ ልዩ ውድ ሽቶዎችን እያወጣች እንደጉድ ታርከፈክፍልን – ወይም ታርከፈክፍብን ነበር! አሁን ድረስ የእርሷ ሽቶዎች ሽታ ይመጣብኛል! እንዴት ያለ ግሩም ስለት ነው? – ግን የሚያሳዝነው ሃይስኩል የእኔ አንድ ሲኒየሬ የነበረና የት/ቤታችን 10 ቁጥር ኳስ ተጫዋች የነበረው የግሩም ጋይንቷ ወይዘሮ አንድ ልጇ – ግሩም – እዚያው ሐረር እያለሁ ወያኔ ከገባች በኋላ ብዙም ሳይቆይ – ኦሲስ የሚባለው የፖሊስ ሆስፒታል የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ዳይቭ ዘልዬ እጠልቃለሁ ሲል – ውሃ ደረቱን መቶት (ገርፎት) – ራሱን ስቶ ወደ ውሃው ሰጠመ፡፡ ላይፍ ሴቨር ደረሰለት፡፡ ግን አጠገቡ ወደነበረው ወደ ህይወት ፋና ሆስፒታል እየተወሰደ መንገድ ላይ እንዳሸለበ ቀረ፡፡ ለብዙዎቻችን ግሩምን ለምናውቅና የኳስም የትምህርትም ችሎታውን እንደ አርአያ ለምንከተል ተማሪዎች – የግሩም ሞት መሪር ሐዘን ነበር፡፡ ውሃ ልቡን ሰንጥቆት ሞተ እየተባለ ነበር ይወራ የነበረው፡፡
እና የእኔም የዋና ገመድ በግሩም ሞት የተነሳ ተቋርጦ ቀረ፡፡ ዋና ይገድላል! እና አጭር ትዕዛዝ ወረደልን፡፡ ከቤተሰብ የላይኛው ምክርቤት፡፡ ከዋና ቦታ ፍጹም ተከለከልን፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለትማ መደበኛ የዋና ቦታ አትሄድም፣ ግን፣ ከት/ቤት ጓደኞችህ ጋር ሆነህ በየወንዛወንዙና በየኩሬው (በተለይ የሸንኮሩ መቆራ) እየሄድክ ባልጠራ ውሃ ላይፍ ሴቨር በሌለበት እንደ ልብህ እየተንቦጫረቅክ የውሃ አምሮትህን ታወጣለህ ማለት ነው፡፡ ወንድሜ! ላይፍ ሴቨር ህይወትን የሚያድን ቢሆን ኖሮ – የምስኪኑን የግሩምን ህይወት ያድን ነበር፡፡
ቆይ እሺ እምነትስ? ስለትስ? በፈጣሪ መታመንስ ግን ዋጋ እንዴት ሳይኖረው ቀረ? የግሩም እናት እንዲያ በየዓመቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሽቶዋን እንደ ዝናብ ውሃ በሰው ላይ ስታርከፈክፈው ኖራ፣ ፈጣሪ አንድ ብቸኛ ልጇን እንዴት በውሃ ይነጥቃታል? ምንድነው የዚህች ዓለም ቀመር ግን? የዚያኛውስ ዓለም? አንዳንዴ አይገባኝም! ዝም ብለህ ኑር በቃ! ወይም ዝም ብለህ ዋኝ! ቀንህ ከደረሰ አምላክም ብትሆን አታመልጣትም፡፡ እና በጸጋ ተቀበል፡፡ ኤሎሄ ስለምን ተውኸኝ አትበል፡፡ ነፍሴን ተቀበላት ብቻ በል፡፡ ያን ለማለት ዕድሉ ካለህ ነው፡፡ ከሌለህስ? ከሌለህማ ድንገት የሞባይል ሂሳብህ አልቆ ነበር ማለት ነው፡፡ ድነገት የምድር ላይ ጉብኝትህ ተጠናቀቀ ማለት ነው፡፡ በቃአ… ‹‹መርሃባ!›› ብለህ፣ ‹‹አሜን›› ብለህ፣ ከፈለግክም ‹‹አሚን›› ብለህ፣… ቀንህ ሲደርስ… በደስታ ወደ መጣህበት መመረሽ ነው! ወደየት? ወደ መጣህበት ነዋ! ወደዚያው ወደ አይጠሬው! በጊዜ ወደማይለካው – ጊዜ ወደማይታወቅበት – ወደ ዝንተ ዓለምህ!
ለማንኛውም ወንድሜ፤ የሐረር በር ላይ ወዳሉት ምስሎች ቀልብህን ሰብሰብ አድርገህ ተመለስልኝ፡፡ መሐል ላይ ያለው ያው የኛው ጓድ መንግሥቱ ነው፡፡ ከግራና ከቀኙ ያሉት ደግሞ የሶቭየቱ መሪ ጓድ ብሬዥኔቭና የኩባው መሪ ጓድ ካስትሮ ናቸው! እነ መንጌ፣ ብሬዥኔቭ፣ እና እነ ካስትሮ…. እንዲህ በሐረር አንደኛ መንገድ መግቢያ አናት ላይ በኩራት ተሰይመው፣ አላፊ አግዳሚውን ቁልቁል እየገረመሙት ኖሩ፡፡ መስከረም 2 በየዓመቱ ሲመጣ አደሬዎች ባህላዊ ልብሳቸውን ለብሰው ከጀጎል ተሰብስበው የሚወጡትና አሁን ወዳስፈረሱት የሐረሩ የራስ መኮንን ሐውልት ወዳለበት ወደ አብዮት አደባባይ የሚወጡት በዚህ በር በኩል አድርገው – በእነ ጓድ መንግሥቱ እየተገረመሙ ነበር፡፡
እነዚያ በባህላዊ አለባበስ፣ በጎናፌ፣ በጌጣጌጥ በቀለማት ያጌጡ የአደሬ እናቶችና ወጣት ኮረዶች የጣውላ ማጨብጨቢያ ይዘው ቀጭ ቀጭ ቀጭ እያደረጉ ሲወጡ ፈዝዘን እናያቸው ነበር፡፡ ‹‹አያ ሆሆ ወንዲሜ ጓዲ መንጊሥቱ! አያ ሆሆ ወንዲሜ ጓዲ መንጊሥቱ! … አያ ሆሆ… ››፡፡ እስካሁን ጭብጨባቸውና ዜማቸው ይህን ስፅፍ ራሱ በጆሮዬ ያቃጭልብኛል፡፡ በነገራችን ላይ ቅርስ ማለት፣ ታሪክ ማለት፣ የተጻፈውና የሚታየው ብቻ አይምሰልህ፡፡ እንዲህ በትዝታ የሚያቃጭልብህ፣ ከታሪክ መዝገብ ላይ ተፍቆ የቀረው፣ በቀልብህ፣ በእዝነ ልቦናህ፣ በህልምህ ሁሉ የሚመጣብህ – የማይታይ፣ የማይጨበጥ፣ የማትዳስሰው ነገር ግን እውን ሆኖ የሚታይህ ነገር ሁሉ ነው ቅርስ፡፡ ይህ ሁሉ ተጨምሮበት ነው ታሪካችን ምሉዕ ሊሆን የሚበቃው፡፡ እነዚህን ህያው ትውስታዎች ጥሎ፣ ሌላ ሌላውን ብቻ አንጠልጥሎ የሚጻፍ ታሪክ፣ የሚጠበቅ ቅርስ፣ የሚጓዝ ጊዜ… ግንጥል ጌጥ ነው፡፡ የአንድ ጆሮ ጉትቻ ብቻ!
ወንድሜ! ጨዋታዬን ስጀምር ለሁሉም ጊዜ አለው ብዬሀለሁ፡፡ ሁሉም ተሰባሪ ነገር የሚጀምርበትና የሚያበቃበት ጊዜ አለው፡፡ የእነ መንጌም ‹‹አያ ሆሆ…›› የተባለባቸው፣ መስከረም 2 የሚደምቅባቸው፣ እነዚያ ከትውስታ የማይጠፉ ውብ የሐረር ቀኖቻችንም ያው እንደማንኛውም እንደተጀመረ ነገር አበቁ፡፡ አበቁና ወያኔዎች መጡ፡፡
ሐረር ከወያኔዎች መምጣት በፊት – ጓድ መንግሥቱ የወጣበት የጀግናው የኦጋዴን አንበሣ ሠራዊት መናኸሪያ ነች፡፡ ሐረር የኦጋዴን አንበሶችን የቦክስ ውድድር ለማየት ቀላዳምባ የወታደሮች ካምፕ በየቅዳሜና ዕሁዱ የምናቀናባት እና ‹‹እኔም እንዳባባ›› የሚለውን የትልቅ ወታደር ፋቲግ፣ ከስክስ ጫማና የብረት ቆብ ጋር ያጠለቀ ህጻን ልጅ በትልቁ ተስሎ እያየን ወታደር ለመሆን በልጅነት የምንመኝባት የጀግኖች ሀገር ናት፡፡ ወይም ነበረች፡፡ ከኦጋዴን አንበሣ ጀርባ በኩል ከቀላዳምባ ወረድ ስንል የሐረርን አሮጌው ስቴዲየምና የጥምቀተ ባህር ሜዳ እንቦርቅበታለን፡፡
በነገራችን ላይ ወያኔዎች የሐረርን ምድር ከመርገጣቸው በፊት ሐረር የብዙ ዕውቅ የእግር ኳስ ክለቦች መናኸሪያም ነበረች፡፡ የባቢሌ ክለብ፣ የቢራ ክለብ፣ የዱቄት ክለብ፣ የኦጋዴን አንበሣ ክለብ፣ የከነማ ክለብ፣ የፖሊስ ክለብ፣ ወዘተ..፡፡ በበኩሌ የማልረሳቸው እጅግ ተወዳጅና አስደናቂ ችሎታ የነበራቸው ተጫዋቾች እስካሁን ይመጡብኛል፡፡ በተለይ የሐረር ቢራው 10 ቁጥር ዶክተር ሰለሞን! ዶክተር ሆኖ የኳስ ፍቅር ያልለቀቀው የኳስ ተዓምረኛ! የዱቄት ፋብሪካ ተጫዋቹ ቄንጠኛው 8 ቁጥር የጎል አዳኝ ወንድወሰን! የባቢሌ ፋብሪካው ተከላካይና መሐል ተመላላሽ ተጫዋቹ ዘንካታው የሰፈራችን ልጅ 9 ቁጥሩ ተስፉ! የጥቁር አንበሣው የቀኝ አማካይ ተመላላሽ አጥቂ 14 ቁጥሩ ፊልሞን! ሐረር ላይ ለግጥሚያ የሚመጡት የአዲሳባ ቡናና ኦሜድላ ክለቦች፣ ምርጦቹ የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ክለብ ተጫዋቾች፡፡
በነገራችን ላይ አንድ ቀን ከእማማ ማሚቴ ቤት እንጀራ ልገዛ ዘው ዘው ስል… የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ግብጠባቂ የነበረውን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጠባቂ የነበረውን የሐረር ልጅ አስደማሚውን ተካበ ዘውዴን ዘው ዘው ሲል አግኝቼው – በመስገብገብና በማሽቃበጥ ሰላምታ ሰጥቼው የሰፈር ጓደኞቼ ላይ ጉራዬን የነዛሁባት ቀን ራሱ አትረሳኝም! አይ ሐረር! አይ ልጅነት! አንድ ስለ ሐረር ከተማ የቀድሞ የኳስ ክለቦች ሳስብ ሁሌ የማይረሳኝ አንድ ልቤን የሚሰብረው ነገርም አለ፡፡ የእኔ ዘመን እኩዮቼ የነበሩ የሐረር ልጆችም እንደማይዘነጉት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ያ የኦጋዴን አንበሣው 14 ቁጥር ታዋቂ ተጫዋች ፊልሞን – ሐረርን ለወያኔዎች አላስረክብም ብሎ በጀግንነት ሲዋጋ ደረቱን በጥይት ተመትቶ ያለፈ ድንቅ ብሔራዊ ጀግናችን ነበረ!
ወያኔ-ኢህአዴግ ወደ ሐረር ከገባ በኋላ፣ እና የእግር ኳስ ክለቦችን ከሐረር ምድር እስክታጠፋቸው ድረስ… የፊልሞን የልብ ጓደኛው የነበረው ሌላው የቀድሞ የኦጋዴን አንበሣ ተጫዋች አባቡ ሁልጊዜ በማልያው ላይ በግራ ደረቱ ላይ ጥቁር የልብ ቅርጽ ያለው ጨርቅ አሰፍቶ ለጥፎ ነበር የሚጫወተው፡፡ በአካል የተለየውን ውድ ጓደኛውን ፊልሞንን በፍቅር እያስታወሰ፡፡ አባቡ፡፡ እና ፊልሞን፡፡ አንዱ እዚህችው የሐረሮች ምድር ላይ በህይወት አለ፡፡ አንዱ ጉብኝቱን ጨርሶ ወደዚያኛው ዓለም በጀግንነት ተሰናብቷል፡፡ ጓደኝነት እንዲህ ነው፡፡ አሁን አባቡስ በህይወት ይኖር ይሆን? አላውቅም፡፡ የኳስ ፍቅር እና የሐገር ፍቅር የተዋሃዱበት የሐረር፡፡ ትዝታዎቼ ብዙ ናቸው፡፡
ስለ ሐረር በር የጀመርኩት ዋናው ጨዋታዬ አላለቀም አይደለም የምለው፡፡ ገና አልተነካም፡፡ ተመልሼ እመጣለሁ፡፡ ዓይኖችህን አሹለህ፣ ጆሮዎችህን ሞርደህ ጠብቀኝ! አላህ ካለልኝ፣ ፈጣሪዬ ቆሌዬን ከፈቀደው ተመልሼ በቆያዩ ጨዋታዎች ላዋዛህ – ወይም አዛ ላደርግህ እመጣለሁ! ዮረቢ ጀኤ!
በነገራችን ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የሐረርን ምድር የረገጥኩት በ1991 ዓመተ ምህረት ክረምት ላይ ነው፡፡ ከምወዳት ውብ ከተማ ከሐረር በአካል ከራቅሁ እንደ ቀልድ 20 ዓመት አለፈኝ ማለት ነው፡፡ 20 ዓመት በአካል ከሐረር ከራቅኩ ነው፡፡ በመንፈሴስ፡፡ በመንፈሴማ 20 ሰከንድ አይሞላኝም፡፡ አሁንም እዚያው ነኝ፡፡ እንዴት እቀራለሁ!?
ፈጣሪ ዓመታችንን ይባርክ! ዘመናችንን ይባርክ! ጀባ ጀባውን.. ቸር ቸሩን ያሰማን! ፍቅር ጀባ! ቡና ጀባ! በርጫ ጀባ! ቢዝነስ ጀባ! አዱኛ ጀባ! ሁሉም ጀባ! ይሁንላችሁ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic