>

"ኦርቶዶክስን መንካት የማይነካውን መንካት ነው...!!!"

 
“ኦርቶዶክስን መንካት የማይነካውን መንካት ነው…!!!”
ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፦የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ነው፥ብሔራዊ ጀግና ነው።ከዚያም በላይ አፍሪካዊም ዓለም አቀፋዊም ነው።በዘር ከረጢት ውስጥ የሚ ከቱት ሰው አይደለም።እርሱም ከዓለም አቀፋዊነት ማማ ላይ ወርዶ የዘረኝነት አዘቅት ውስጥ መዝቀጥ አይፈልግም።እኔ ኃይሌን በቅርብ አውቀዋለሁ።እንድንቀራረብ ምክንያት የሆነንም፦የአትሌቶቻችን የተክሊልና የቅዱስ ቍርባን ጋብቻ ነበር።አትሌት ሚሊዮን ወልዴ፥ ወንድማማቹ አትሌት አሰፋ መዝገቡ እና አየለ መዝገቡ፥እንዲሁም አትሌት ተስፋዬ ቶላ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጋብቻቸውን በመሠረቱ ጊዜ፦በዚያ አጋጣሚ ተገናኝተን ብዙ ነገር አንሥተን ተወያይተናል።ከአንድም ሁለት ጊዜ ቤቱ ጋብዞኝ በቤተ ክርስቲያን እና በሌሎችም ጉዳይ አውግተናል።ለኪዳነ ምሕረት ያለው ፍቅር ልዩ ነው፥በኦሎምፒክ ያገኘ ውን የወርቅ ሜዳልያ ለእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገዳም የሰጠው ለዚህ ነው።
             ዛሬ ስለ ኃይሌ እንድጽፍ ገፊ ምክንያት የሆነኝ በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ላይ ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው።በእውነቱ የመንፈሱ ጥንካሬ በዝዋይና በሻሸመኔ ያ ሁሉ ሀብት ንብረት በሃይማኖትና በብሔር አክራሪዎች የወደመበት አይመስልም።እርሱ የሚያስ በው ከቍሳቍስ በላይ መተኪያ የሌለው የሰው ሕይወት ያውም በአሰቃቂ ኹኔታ ጠፍቶ አል ብሎ ነው ።ይህ አሳቡ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሜዳልያ የሚያሸልም ነው።የተጎ ዳው ኃይሌ ብቻ አይደለም፥በስሩ ይተዳደሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እስከነ ቤተሰቦቻቸው ተጎድተዋል።ትልቁ ጽድቅ እንደ ፈረንጅ ዕርዳታ ሠርቶ መብላት የሚች ልን ሰው በምጽዋት ማኖር ሳይሆን የሥራ ዕድልን በመፍጠር ራስን ማስቻል ነው።ይህንን የሕይወት መመሪያውን አከብርለታለሁ።ሰው መኖር ያለበት በሌላው ወዝ ሳይሆን በራሱ ወዝ ብቻ ነው።የምንኖረው ዓይናቸው የፈረጠ፥እጅ እግራቸው የተቆረጠ እንኳ ከማንም በላይ በራሳቸው ወዝ መኖር በሚችሉበት ዓለም ላይ ነው።መረዳዳቱ እንዳለ ሆኖ ላብን ማፍሰስ፥ወዝን ማንጠፍጠፍ ግድ ነው።”በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።… ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ትበላለ ህና፤” ይላል።ዘፍ፡፫፥፲፯።ታድያ በስንፍና ቡሉኮ ተጆብነው የሚኖሩ ሰዎች እንደ ንብ ታታሪ የሆኑ ሰዎችን ሀብት ንብረት የዶግ አመድ ሲያደርጉት እጅግ ያሳዝናል።ከሁሉም በላይ በበረከት የተመላች የደሀ ጎጆ ስትቃጠል ያበሳጫል።
            ኃይሌ በቃለ ምልልሱ፦የተናገረውን በጣም ጥቂቱን እንደ ወረደ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።ለመርሐ ግብሩ አዘጋጅ ሲመልስላት እንዲህ ነው ያላት።”… ያለሽ ሁሉ ያንቺ  አይደለም፥የእርሱ (የእግዚአብሔር) ነው።ማድረግ ያለብሽን ሁሉ ማድረግ አለብሽ፥ዐሥራ ቱን በኵራቱን መስጠት ግድ ነው። የግድ ነው የሚባለው ለምን መሰለሽ? በቃ እግዚአብ ሔር ሰጠ፥እግዚአብሔር  ነሳ ነው፥የሚባለው።ኢዮ፡፩፥፳፩።እግዚአብሔር በሰጠው ደግሞ፦እናንተ ለሌላው አስቡ፥እኔ ለእናንተ አስባለሁ ነው ያለው።”
          ” እርግጥ ኦርቶዶክስ መጠበቅ አለባት፥ኦርቶዶክስን መጠበቅ ሀገርን መጠበቅ ነው፥ኦርቶዶክስ እኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ተናገሩት  ሀገር ናት።ለኔ ኦርቶዶክስን መጠ በቅ ያለበት ኦርቶዶክሱ ብቻ መሆን የለበትም፥ኦርቶዶክስን የሚጠብቅ ኦርቶዶክሱ ብቻ ከሆነ ሀገር ፈረሰች ማለት ነው።አንዳንድ ጊዜ ሰው በወኔ ብቻ ተነሥቶ በስሜት የሚናገ ረው ትክክል አይደለም፥ብዙ ነገር ያነቃንቃል።እኔ እፈራለሁ፥ኦርቶዶክስ ስትነካ ብዙ ነገር ይጠፋል።ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመልከት (ከታሪክ መማር) ያስፈልጋል።ትናንት ሀገራችንን የወረረችው የፋሺስት ኢጣልያ ዓላማ ኦርቶዶክስን መነቅነቅ ነበር፥ታዲያ ለምንድነው ኦርቶ ዶክስን ነቅንቀው በዚያው ያላጠፏት? (ለምንድነው እነርሱ በዓለም ፊት የትዋረዱት)? በመ ጀመሪያውኑ የማይነካውን በመንካታቸው ነው፥የማይነካውን ስለነኩ ለእነርሱ ከባድ ነበር።”
           “እኔ እና አንቺ ኦርቶዶክስ ስለሆንን አይደለም፥እዚህ መነጋገር ያለብን።ኦርቶዶክስ ደግሞ ከማንም በላይ ሃይማኖቱ የሚያዝዘው ሰውን በሰውነቱ መቀበል ነው፥ምንም ሃይ ማኖት ይከተል የሚያከብር ነው።ኦርቶዶክስ እኮ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥ፍርድ የእግ ዚአብሔር ነው፥ቅጣት የእግዚአብሔር ነው፥ብሎ ከቤቱ የሚቀመጥ ነው እንጂ በቀለኛ አይደለም።ወደ ኋላ ልመልስሽና አድዋ ላይ ጣልያን ተሸንፎ ሄደ፥ከዚህም የተነሣ እኛ ጀግ ኖች ነን እንላለን።እስኪ አስቢው፥እዚያ ቦታ (ከዐውደ ውጊያው) ፈጣሪ አብሮአቸው ባይ ኖር ኖሮ ማሸነፍ ይችሉ ነበር? እውነት ያን ሁሉ የጣልያን ሠራዊት፥ዓለምን ይገዛ የነበረውን ኃይል የኛ ጀግንነት ብቻ ነው ድል ያደረገው? አይደለም።አንዲት ደሀ ሀገር አይደለችም ድል ያደረገችው፥እግዚአብሔር ነው።ቀጥሎም አርባ ዓመት ተዘጋጅቶ በተመለሰም ጊዜ በአም ስት ዓመት ውጊያ የተሸነፈው በእግዚአብሔር ኃይል ነው።”
            “አሁንም የምነግርሽ በዚህች ሀገር ላይ ሌላ ችግር ሌላ ፈተና ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን እኔ እና አንቺ አናሸንፍም፥እኔ እና አንቺ ምናልባት ምክንያት ልንሆን እንችላለን። ጀግኖቹ ጄነራል እገሌ፥ራስ እገሌ፥ፊታውራሪ እገሌ … ቢባልም እነርሱ ምክንያቶች ናቸው። ቅድም እንዳልኩሽ ነው።በሩጫው ዓለም እኔ ምክንያት ነኝ፥አበበ ቢቂላ ምክንያት ነው። እውነት አበበ ቢቂላ ከሌላው (ከሰለጠነው ዓለም ሯጮች) በላይ የበለጠ ዝግጅት አድርጎ ነው? አሁን ኃይሌ የሚባል ትል ከእነዚያ ዝግባ ከሚያካክሉ ሰዎች መካከል አሸንፎ ሲወጣ ይጨበጨብለታል።ነገር ግን ሊጨበጨብለት የሚገባው አካል አለ፥ይሁን እንጂ ያ አካል የሚጨበጨብለት ሳይሆን ዝም ብለሽ በልብሽ የምታስቢው ነው።”(ቅዱስ ዳዊት፦ እኔ ትል ነኝ ሰው አይደለሁም ብሎ እንደ ተናገረው አይነት ነው)።
            ” በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ከገንዘብም ከቍሳ ቍስም በላይ ልንጠብቃት እንደሚገባ አስባለሁ።በእርግጥ አሁን፥አሁን ብዙ ችግር አለ። በኦርቶዶክስ መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ፈተና እንደሚበዛባት አውቃለሁ፥ከድሮ ጀምሮ ፈተና አለ፥ራሱ ሃይማኖቱንም መከተል ፈተና አለው፤”ብሎአል።
              ሌሎችም ስምና ዝና ያላችሁ ኦርቶዶክሳውያን እንዲህ እየወጣችሁ የመመስከር መንፈሳዊ ግዴታ አለባችሁ።በየጓዳው ማጉረምረሙ ትርጉም የለውም፥በሃይማኖት ጉዳይ እንደ ዲፕሎማት መሆን አይጠቅምም፥ከዚህ በላይ ቤት ክርስቲያን ምን ይምጣባት? ሌሎቹ እኮ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉት በታዋቂ ሰዎቻቸው በኵል ነው።ስለ ዚህ እናንተም ደክማችሁ ባገኛችሁት ታዋቂነት ተጠቅማችሁ “አትረዱን፤” እያላችሁ ተጽ ዕኖ ፍጠሩ።ፍትሕ ርትዕ መጠየቅ የሚያስፈራ የሚያሳፍርም አይደለምና።ፈጣሪ ከእርሷ ጋር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ተቆርቋሪ ሰው እንደሌላት መሆን የለባትም።ይህንን ማድረግ ያለባ ችሁ ለማንም ብላችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ (ለነፍሳችሁ ድኅነት) ስትሉ ነው።ያን ጊዜ በሰው ዘንድ እንደ ታወቃችሁ ሁሉ በእግዚአብሔርም ዘንድ የታወቃችሁ ትሆናላችሁ፥የሚበልጠው ይህ ነው።የእግዚአብሔር ቸርነት፥የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥አሜን።
Filed in: Amharic