>

የፍትኅ ሥርአቱ የአማራ-ጠልነት ማንበሪያ  ሆኖ መቀጠል አይኖርበትም ...!!!  የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ወቅታዊ መግለጫ

የፍትኅ ሥርአቱ የአማራ-ጠልነት ማንበሪያ  ሆኖ መቀጠል አይኖርበትም …!!!
 የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ወቅታዊ መግለጫ
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
     መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም
         አዲስ አበባ ሸዋ

ንቅናቄው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራንም በሥርዓቱ ውስጥ እየታየ ያለውን መረን የለቀቀ ዘረኝነት እና የሙስና ንቅዘት አይነተኛ ማሳያ ነዉ ብሎታል።
በማንነቱ የተገፋው ሕዝብ ባደረገው ሰፊ ትግልም ቀንደኛ የሆኑትን ጠላቶች በከፊል ከስልጣን ማስወገድ የቻለ ቢሆንም እስካሁን የተሟላ ውጤት ላይ አልደረሰም ነው አብን በመግለጫው።
ትግሉ በስኬታማነት ሳይጠናቀቅ የቀረው በበርካታ ምክንያቶች መሆኑን የገለፀው አብን በዋናነት መንታ ተልዕኮን ያነገበ ትግል በመሆኑ ምክንያት እንደ ሕዝብ ራስን የመከላከል እና መብትን የማስከበር እንቅስቃሴው ላይ፣ በተጓዳኝ ያለው የአገር ኅልውናን የመታደግ እና የማስቀጠሉ ምዕራፍ ተፅእኖ ሲያሳድርበት ተስተውሏል ነው ያለው።
አብን ሲቀጥል በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ጽንፍ የረገጡ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች  የአገር አንድነት፣ ቀጣይነት እና ሉዓላዊነት እምብዛም የማይገዳቸው፣ አለፍ ሲልም ከአገር ጥቅም በተፃራሪ የሚሰለፉ ጭምር መሆናቸው የሕዝባችንን የትግል ሸክም በእጅጉ እንዳከበደዉ እንረዳለን ሲልም አክሏል።
የአማራው ራስን የመከላከል እና መብትን የማስከበር የትግል ክፍል አገርን ለመታደግ ከሚደረጋው የትግሉ ክፍል ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ አንሶ ይታያል ብሏል።
በትግሉ መገባደጃ ወቅት የተተካው እና <<የለውጥ ስርአት>> የሚባለዉ ለአገራችን ሰፊ ተስፋን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ሕዝባችን የታገለላቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ያልቻለ፣ አንዳንዶቹን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ያልሆነ እና ከሕዝባችን የአገራዊነት፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና የወንድማማችነት መንፈስ የራቀ ፖለቲካዊ ቅኝት እንዳነገበ መረዳት ይቻላል ሲል ነው የገለፀው።
አገራችን የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባት፤ የዜጎች መሰረታዊ መብቶች ልቅ በሆነ መልኩ እየተጣሱ፤ ማንነትን እና እምነትን መሰረት ያደረጉ በርካታ ጥቃቶች እየተፈጸሙ እና ዜጎች ለደቦ ፍርድ እና ለመንጋ ጥቃት ተጋልጠዉ ባሉበት ሁኔታ መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሊታደግ ሲገባዉ በተቃራኒ የተጋነነ ዳተኝነት ሲያሳይ ቆይቷል ሲልም ወቅሷል።
መንግስት በጊዜው ተገቢዉን ክትትል አድርጎ በማስቆም ዜጎችን ከመታደግ ይልቅ ለአጥፊዎቹ የተለሳለሰ ፖለቲካዊ አቋም ይዞ ቆይቷል ያለው ንቅናቄው በተግባር በተገለጡት የዘር ማጥፋት ወንጀሎችም በርካታ የመንግስት ኃላፊዎች ጥቃቱን ባለመከላከል የኃላፊነት ጉድለት በማሳየት በተዘዋዋሪ መንገድ ለአጥፊዎቹ ድጋፍ አድርገዋል ብሏል።
በለውጥ ኺደቱ ላይ ሰፊ ቅሬታዎች እንዳሉት መደበቅ አይፈልግም ያለው አብን ድርጅታችን የሕዝብ እንጅ የቡድን ወገንተኝነት የሌለዉ ሕዝብ እና አገር ወዳድ ድርጅት ሲሆን የሚከተለዉ የትግል መስመርም በአማራ ሕዝብ ጉዳዮች እና በአገራችን መካከል ያለዉን ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ አበክሮ ይገነዘባል ሲል አክሏል።
ሃቀኛ አገር ወዳድ ከሆኑ፣ ዴሞክራሲን፣ ፍኅን እና እኩልነትን ለማስፈን ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር  ስትራቴጂክ አጋርነት ሊኖረው እንደሚችል ይገነዘባል።
አብን የኮሮናን(COVID-19) ወረርሽኝን ተከትሎ በክልላዊ እና በአገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ የያዘው አቋምም በወቅቱ ከተሳካላቸዉ አግላይ፣ ዘረኛ እና አምባገነናዊ ሥርዓት ለማስፈን ካልሆነ አገሪቱን ለመበታተን የተዘጋጁ ኃይሎች ሊፈጥሩ የሚችሉትን ጥምረት ማምከን ለሀገር እና ለህዝብ አስፈላጊ ነው ብሎ ከማመን የመነጨ መሆኑን አውስቷል።
 በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሰፊ የፖለቲካ ተቃርኖ እና የአሰላለፍ ልዩነት ሊታረቅ የሚችልበት መሰረት ሳይጣል ማዕከላዊ መንግስቱ የሚዳከምበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል አገርን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ በሚል የበኩሉን ለመወጣት ከማለም እንደሆነም ፓርቲው ጠቅሷል።
ወቅታዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች ሕዝባችንን ለፖለቲካ ማስያዥያነት በመጠቀም ልዩ ጥቃት ሊሰነዝሩበት እንደሚችሉ በመገመት መንግስት ከወዲሁ ልዩ የመከላከል እንቅስቃሴ እንዲያደርግም አሳስበን የነበርን ቢሆንም መንግስት በኛ ማሳሰቢያ እና በገባው ቃል መሰረት ተፈፃሚ ሳያደርግ በመቅረቱ የበርካታ ወገኖቻችን ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፣ ንብረትም ወድሟል ሲልም አክሏል።
መንግስት ሕግ በማስከበር ረገድ ያሳየውን ዳተኝነት በመተው ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀን በጥፋቱ የተሳተፉትን አካላት በሙሉ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቦ እንደነበር ያወሳው ንቅናቄው ይሁን እንጅ በመንግስት በኩል አጠቃላይ የሥርዓት አልበኝነቱ እና የጥላቻ ፖለቲካው የአገራችንን ኅልውና ጭምር ፈተና ላይ የጣለው መሆኑን በመገንዘብ በሕግ የበላይነት ጉዳይ እንደማይደራደር መግለፁን መነሻ በማድረግ የዘገየ ቢሆንም ትክክለኛ እና አዋጭ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ግምት ነበርን ብሏል።
አጠቃላይ ጉዳዩ በመንግስት በኩል ከአድሎ በፀዳ እና ባልተለሳለሰ መልኩ መያዝ እና የአንድ መንግስት ዝቅተኛ ኃላፊነት የሆኑትን የሕግ ማስከበር እና የዜጎችን መብት መጠበቅ ስራዎች በተገቢዉ መልኩ ሊያከናወን ይችላል በሚል የነበረው በጎ ግምትም ክፍተት እንደነበር ተመልክቷል።
“ሕግ ማስከበር የማይችል ደካማ መንግስት እንዲኖር የማይፈለገውን ያክል አምባገነናዊ መንግስትም ተፈላጊ እና ተመራጭ ሊሆን አይችልም፤ ተመራጩ ጠንካራ፣ ፍትኃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ የግልፅነት መርኅ የሚከተል እና ለሕዝብ ተጠያቂ የሆነ መንግስት ነው።” ሲል የገለፀው ድርጅቱ አሁን ላይ ሕግ እና የዜጎችን መብት የማስከበር አቅም እንዲኖረው የምንፈልገው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ እና ግልፅነት የጎደለው እየሆነ መምጣቱን ተረድተናል ብሏል።
በሕግ ማስከበር ሰበብ በአንድ በኩል ለፖለቲካ ሚዛን ማስጠበቂያነት፣ በሌላ በኩል አጋጣሚውን በመጠቀም የተከፉ የወቅቱ ባለስልጣናት ለያዙት ቂም ማወራረጃ ታስበው የሚፈፀሙ የእስር እና የማንገላታት ተግባራት ፍፁም ተቀባይነት የላቸውም ያለው አብን በእነ አቶ እስክንድር ነጋ እና በድርጅታቸው ባልደራስ፣ በእነ አቶ ልደቱ አያሌውና በአስራት ጋዜጠኞች የተደረገውን እስር፣እንግልትና ክስን መንግስታዊ ለሆነው ዘረኛ አካሄድ እንደማሳያነት ጠቅሷል።
በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ በሥርዓቱ ውስጥ እየታየ ያለውን መረን የለቀቀ ዘረኝነት እና የሙስና ንቅዘት አይነተኛ ማሳያ መሆኑንም ገልጧል።
ይኼ ሁሉ ችግር እየተፈጸመ ባለበት ሁኔታ የፌዴራሉ መንግስት እና የገዥዉ ብልጽግና ፓርቲ አካል የሆነዉ የአማራው ቅርንጫፍ አማራ ጠል ትርክት በመንግስት መዋቅር እና በሕግ ሽፋን ተግባራዊ ሲደረግ እና ወገኖች እንዲሸማቀቁ እና እንዲጠቁ ሲደረግ በታዳሚነት መመልከቱ የአማራን ሕዝብ እና አብንን ቅር እንደሚያሰኝ ለመግለፅ እንወዳለን ብሏል፡፡
የአማራ ሕዝብ ወኪል እና ተቆርቋሪ ነኝ ለማለት ቢያንስ መሰረታዊ ችግር የሆነዉን አማራ ጠል ትርክት በመንግስት ፖሊሲዎች እና መዋቅሮች አማካኝነት እንዳይተገበር በጽኑ መታገልን እንደሚጠይቅ ማወቅ ያስፈልጋል ሲልም አክሏል፡፡
በአማራዊትብብር መንፈስ የተቃኘዉ የአብን እንቅስቃሴ የአማራ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በትዝብት የሚመለከታቸዉ እና ለምርጫ ክርክር ብቻ መዝግቦ የሚያልፋቸዉ አይደሉም ያለው ንቅናቄው:
1. ለአማራ ሕዝብ እና ለመላው ፍትኅ ወዳድ ኢትዬጵያዊያን እነዚህን የፍትኅ መዛነፍ አይነተኛ ማሳያዎችን በመውሰድ በሕግ እና መዋቅር የተደገፈዉን ጭቆና ለማስወገድ ትግላቸዉን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
2. መላዉ የአብን አባላት እና ደጋፊዎች ሕዝባችን በማንነቱ ተለይቶ የሚጠቃበትን ማናቸዉንም ማዕቀፍ በግልጽ በመቃወም ለዘላቂ ፍትኅ፤ ዴሞክራሲ፤ እኩልነት እና ሰላም መስፈን የሚደረገዉን ትግል አጠናክረዉ እዲቀጥሉ እያሳሰብን፤
3. በመንግስት በኩል ያላግባብ እየታየ ያለዉ የማዋከብ፣ መብቶችን የማጣበብ እንቅስቃሴ እንዲቆም እና እየቀረበ ያለዉ ክስ በአስቸኳይ እንዲነሳ አበክረን እንጠይቃለን ሲል መግለጫውን ቋጭቷል፡፡
Filed in: Amharic