>

"....እስክንድር ነጋ....." (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

“….እስክንድር ነጋ…..”

” …አሳሪዎቹም ጉልበታቸውን ከጭንቅላታቸው አላወጡም! ታሳሪውም አልሰለቸውም…. ” 

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

አንዲት የአሜሪካ ሴት ልጇን አንድ ሰካራም መኪና እየነዳ ሲሄድ ገጭቶ ገደለባት፤ እርር! ድብን! ብላ አዘነች፤ አልበቃትም፤ የአንድ ሰው ትግል ጀመረች፤ አሜሪካን አዳረሰችው፤ እናቶች ሁሉ ተሰባሰቡላት፤ ከዚያ ቀስ እያለ ሌሎችም ሁሉ እየገቡበት ትልቅ አገር-አቀፍ ንቅናቄ ሆኖ እየጠጡ መንዳት በሕግ እንዲከለከል አደረገች፤  በዚች በአንድ ሰው ብርታት አሜሪካ የተሻለ አገር ሆነ።
በኢትዮጵያችን በየቀኑ ቤት እየፈረሰ ሰዎች እንደአበሻ አገር ቆሻሻ በየመንገዱ ላይ እየተጣሉ ሲያለቅሱ እናያለን፤ መንግሥት አለ? ማንም ምንም አያደርግም፤ መንግሥት አለ? ባለሥልጣኖቹም የማፍረስ ትእዛዛቸውን ያስተላልፋሉ፤ አፍራሾቹም ሥራቸው አድርገውት ያፈርሳሉ፤  መንግሥት አለ? እንዲያውም ለምዶባቸው ቅርስ የተባለውን የደጃዝማቹን ቤት አፈረሱት! መንግሥት ማለት አፍራሽ ግብረ ኃይሉን የሚቆጣጠረው ነው መሰለኝ!
ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል እንደሚባለው ሆኖ እስክንድር ነጋ የሚያለቅሱትን ሰዎች አስተባብራለሁ ብሎ ተነሣ፤ ጠጠር አንወረውርም እያለ! የፍቅር፣ የመደመር፣ የይቅር ባይነት ዲስኩር ትዝ ብሎት፣ የክርስቶስን ትምህርት አስታውሶ ለተገፉትና ተስፋ ለቆረጡት ተናገረ፤ በሕግ ተማመኑ ብሎ፤ ይለይልህ ብለው ራሱን አስፈራሩት! እኔ ሳውቅ እስክንድር ነጋ ሲታሰር ሲፈታ ሠላሳ ዓመታት የሆነው ይመስለኛል፤ አሳሪዎቹም ጉልበታቸውን ከጭንቅላታቸው አላወጡም! ታሳሪውም አልሰለቸውም! እኛም አልተለወጥንም!
Filed in: Amharic