>

ዐቃቤ ሕግ "በእነ ጃዋር  መሐመድ ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መሰረትኩ !" አለ (ሕብር ሬዲዮ)

ዐቃቤ ሕግ “በእነ ጃዋር  መሐመድ ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መሰረትኩ !” አለ

ሕብር ሬዲዮ

* በውጭ አገር ያሉም በሌሉበት ተከሰዋል
ዐቃቤ ህግ ክሱ ፍርድ ቤት ከመድረሱ በፊት ለምን ይፋ ማድረግ እንደፈለገ የጠቀሰው ነገር የለም
የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር እና የኦኤም ኤን መስራችና የቀድሞ ዳይሬክተር የነበረው ጃዋር መሐመድ፣የፓርቲው ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እና ሌሎችም ላይ በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ ጠቅሶ በሽብር ወንጀል ሲል ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱን ይፋ አድርጓል።
ዐቃቤ ህግ ክሱን አስመልክቶ የሚከተለውን ጽፎዋል።
“ሰበር ዜና
—————–
ጁሀር ሲራጅ መሀመድ፤ በቀለ ገርባ፤ ሀምዛ አድናን፤ እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን  የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN)፤ ደጀኔ ጉተማ ፤ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጣቃላይ በ24 ሰዎች ላይ  እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ ፤የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ፤ የለቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል የፌደራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶች ያስከፈተ ሲሆን፤ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ “
ዐቃቤ ህግ ክሱ ፍርድ ቤት ከመድረሱ በፊት ለምን ይፋ ማድረግ እንደፈለገ የጠቀሰው ነገር የለም።እነ ጃዋር የታሰርነው በፖለቲካ አቋማችን ነው ሲሉ ከዚህ ቀደም ለፍርድ ቤት መናገራቸው ይታወሳል።
Filed in: Amharic