>
5:18 pm - Tuesday June 15, 9379

ነገረ ብርሃኑ ጁላ ... ?!? (አቻምየለህ ታምሩ)

ነገረ ብርሃኑ ጁላ … ?!?

አቻምየለህ ታምሩ

ባለጊዜ ስለሆነ ብቻ በጋዜጠኞችና በሚተቹ ግለሰቦች ላይ እየዛተ ያዙል ልቀቁኝ በማለት  ሲደነፋ የሚውለው ብርሃኑ ጁላ ራሱን ወታደር ሆኖ ያገኘው ባጋጣሚ ነበር። ብርሃኑ ጁላ ራሱን ጦር ሜዳ ያገኘው ደርግ የገበሬ ልጆችን እያነቀ ወደ ጦር ግንባር ሲያግዝ አብሮ ተግዞ ነበር። ብሬም ወደ ጦር ግንባር የተሰማራው የደርግን ለብ ለብ ወታደራዊ  ስልጠና ጨርሶ በሰሜን በኩል የተነሱትን ገንጣይ አስገንጣዮቹን ሻዕብያንና ወያኔን ለመውጋት ነበር።
ሆኖም ግን የተሠጠውን ብሔራዊ ተልዕኮ ሳይፈጽም በ1981 ዓ.ም. ጎብየ በተባለ ቦታ በኢትዮጵያ ሠራዊትና በወያኔ የገበሬ ወታደሮች መካከል በተካሄደው ጦርነት ተሸንፎ “ሜይደይ”  ወይም  ወያኔዎች 22 እያሉ በሚጠሩት ክፍለ ሠራዊት ተማረከ። የማረኩት የወያኔ የገበሬ ወታደሮች  እንዳይገድሉት ስለፈራ “አየር ወለድ ነኝ”፤  “ሐኪም ነኝ”፤ “ከሔሊኮፕተርም  እዘላለሁ” በማለት ራሱን አሻሽጦ ሕይዎቱን አተረፈ። ለተወሰነ ወራት ያህል  ተሃድስ ከሰጡት በኋላም መለስ ዜናዊና ክንፈ አብርሃ ኦሕዴድን ሲመሰርቱ ብርሃኑን የኦሕዴድ ታጋይ አደረጉት።
ወያኔ  በመንግሥትነት ከተሰየመ በኋላ በ1987 ዓ.ም. ሠራዊቱን ሲያደራጅ ምርኮኛው ብርሃኑ ኮሎኔል የሚል ማዕረግ ታድሎት የሜይደይ ወይም 22 የሚባለው የወያኔ ክፍለ ሠራዊት አዛዥ ሆኖ ተመደበ።  ይቺ ሜይደይ ወይም 22 የምትባለዋ ብርሃኑ የኮሎኔልነት ማዕረግ በመለስ ዜናዊ ታድሎት በአዛዥነት የተሾመባት ክፍለ ሠራዊት  ከስድስት ዓመታት በፊት የማረከችው ክፍለ ሠራዊት ናት።
ወያኔ ከማረከው  በኋላ እንደ ብርሃኑ ጁላ መጫወቻ ያደረገው  ሌላ ምርኮኛ ያለው  አይመስለኝም። ወያኔ በብርሃኑ ጁላ የተጫወተበት ማዕረግ አድሎ የማረከችውን  ክፍለ ሠራዊት “እንዲመራ” አዛዥ አድርጎ  በመሾም ብቻ አልነበረም።  ወያኔ የማረከውን ብርሃኑ ጁላን ኮሎኔል የሚል ማዕረግ አድሎ የማረከችውን ክፍለ ሠራዊት እንዲመራ አዛዥ  አድርጎ ከመደበው በኋላ  ጎብየ ላይ በ1981 ዓ.ም. የማረከውን የወያኔ ታጋይ ደግሞ ኀምሳ አለቃ የሚል ማዕረግ አድሎ  በብርሃኑ ስር መደበው።  ይህ ብርሃኑን የማረከው  የወያኔ ኀምሳ አለቃ ኮሎኔል ማዕረግ ታድሎት  ክፍለ ሠራዊት አዛዥ የሆነውን ብርሃኑን በሚመራው ክፍለ ሠራዊት ፊት የሚጠራው “ሙሩኽ ” ወይም ምርኮኛው በማለት ነበር። ወያኔ ብርሃኑን ኮሎኔል አድርጎ የማረከችው ክፍለ ሠራዊት አዛዥ  ካደረገ በኋላ የማረከውን ታጋይ ደግሞ ኀምሳ አለቃ አድርጎ  በሥሩ የመደበው ከምርኮኛው ኮሎኔልነት የታጋዩ ኀምሳ አለቅነት እንደሚበልጥ ብርሃኑ ሁልጊዜ እያሰበ እንዲኖር ለማድረግ ነው።
አንድ ቀን ብርሃኑ ጁላ ከአዋሳ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ፈልጎ  ከዕዝ ማዕከሉ ኮብራውን  እየነዳ ሲወጣ ያየው የማረከው ኀምሳ አለቃ የጫናቸውን ሰዎች አውርዶ እሱን  ብቻ ይዞ  ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድና የጫናቸውን ሰዎት ተመልሶ እንዲወስድ ቢጠይቀው ብርሃኑ ፍቃደኛ አልሆነም ነበር። በዚህ የተናደደው የማረከውም ኀምሳ አለቃ ብርሃኑን አብረውት በነበሩት  ሰዎች ፊት  “ምርኮኛ” ብሎ ሰደበው። በዚህ የተናደደው ብሬም አዲስ አበባ ሲደርስ  በወቅቱ የወያኔ ኤታማጆር ሹም ወደነበረው ወደ ጻድቃን ገብረ ትንሳይ ቢሮ ሄዶ ኀምሳ አለቃው “ምርኮኛ” በማለት እንደሰደበው አቤት አለ።  ጻድቃንም  ኀምሳ አለቃው ጠርቶ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው በትግርኛ ታሪኩን የጻፋው ቀዳሚው ምስክር ነግሮናል። ጸሐፊው ጨምሮ እንደነገረን ብርሃኑ ጁላ  “ምርኮኛ” ብሎ ከሚጠራው ሰው በላይ በምድር ላይ የሚጠላው ሰው የለውም።
ልክ እንደ ብርሃኑ ጁላ ሁሉ ወያኔ ማዕረግ እያደለ የሠራዊት አዛዥ ካደረጋቸው የኦሮሞ ተወላጅ ምርኮኞች መካከል የደቡብ ዕዝ ሎጀስቲክ ኃላፊ ሆኖ የተመደበውና ብርጋዴር ጀነራል ማዕረግ የታደለው ኩመራ ነገሬ  [በዐቢይ አሕመድ ዘመን ሜጀር ጀኔራል ሆኗል]፣ የብርጋዴር ጀኔራልነት ማዕረግ ታድሎት የምስራቅ እዝ የብርጌድ አንድ አዛዥ ተደርጎ የተሾመው ማጫ ደበሌ፣  ብርጋዴር ጄነራልነት ታድሎት  የወያኔ መከላከያ ሚንስትር የሆነው አባ ዱላ ገመዳና  ኮሎኔልነት ታድሎት የስምንተኛው መካናይዝ ኃይል ኮማንደር የተደረገው ገመቹ አያና ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ብርሃኑ ጁላ ወያኔና ሻዕብያ ጥጋባቸውን ማስቻል አቅቷቸው ባድመ ላይ ወርደው ጫማ  ሲሰላኩ የማረከችው ክፍለ ሠራዊት አዛዥ ሆኖ በማረከው ኀምሳ አለቃ እየተመራ የካቲት 16 ቀን 1991 ዓ.ም. በባድመ ግንባር ቀኝ ክንፍ በኩል በፍቅያ፣ ገብረ ሽካ፣ ወዲ ኾለላ፣ ሓዱሽ ዓዲ ገብታ እስከ ቡምበት  ድረስ ዘምቶ ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ ዛሬ ራሱን ወደር የማይገኝለት የሠራዊት አዛዥ አድርጎ  ቡራ ከረዩ የሚለው ባለ አራት ኮከቡ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ  “የመራው”  የጦር ግንባር ቢኖር ይህ የማረከችው ክፍለ ሠራዊት አዛዥ ሆኖ ተመድቦ  በማረከው ኀምሳ አለቃ እየተመራ  በባድመ ጦርነት በ1991 ዓ.ም. ሓዱሽ ዓዲ ላይ ያደረገው “ውጊያ” ብቻ ነው።
በጋዜጠኞችና በተቺ ግለሰቦች ላይ ሲደነፋ የሚውለው ብርሃኑ ጁላ  የሚመራው  ወደር የማይገኝለቱ ጦር ግን በመተከልና በወለጋ የታጠቁ  ኃይሎች በየቀኑ በግፍ ለሚረሸኗቸው  ሴቶች፣ አረጋውያንና ሕጻናት ሲደርስላቸው አላየነውም። ነው ወይስ ወደ የማይገኝለቱ የብርሃኑ ጁላ ጦር ጉልበት የሚያወጣው በግል ጋዜጦና መፅሔቶች፣ በግል ሬዲዮኖችና የቴሌቪዥን ስርጭቶች፣ በሚነበቡና በሚደመጡ ዌብ ሳይቶች፣ በጋዜጠኞች፣በተቺ ምሁራንና በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ ብቻ ነው?
Filed in: Amharic