የ ኦሮ ማራ ጥምረት ህብረት….ሞቱን ባያስቀርልን እንኳን ምን ያህል በግድያው አሰቃቂነት፣ ግፍነት፣ ወንጀልነት ላይ ተወያየ…?!?
መስከረም አበራ
ማንኛውም ፖለቲካዊ ስምምነት፣ጥምረት ወዘተ መመዘን ያለበት ባመጣው ውጤት ነው። የአማራ እና ኦሮሞ የፓርቲዎች፣ምሁራን ያደረጉት ውይይት ፣ኦሮማራ የተባለው ብዙ የተባለለት ነገር ምን አመጣ? ብሎ መጠየቅ ውጤት የሚሻ ሰው ጥያቄ ነው። በተለይ ነገሩ ከሚሊዮኖች በህይወት የመኖር መብት ጋር የሚያያዝ ነውና እንዲሁ “ከሚቀር ይጥቆር”በሚል የሚይዙት የዋዛ ነገር አይደለም።
ኦሮማራ የተባለው ጥምረት ወያኔን አስወገደ ሊባል ይችላል። ከዛስ? አሁን ላይ ጥምረቱ ራሱ ህልውና አለው ወይ? ህልውና ካለው ተፋፍሞ የቀጠለውን የአማራውን ሞት እንዴት በጥቂቱ እንኳን እንዲቀንስ አላደረገም? በክልሉ ያለውን የአማራን ሞት መቀነስ ብዙ አመታት ይፈጃል ከተባለ ከሃጫሉ ሞት በኋላ የተከሰተው አሰቃቂ ዘር ተኮር ግድያ ከተከሰተ በኋላ ኦሮ ማራ ይባል የአማራ እና የኦሮሞ ምሁራን ወዘተ ህብረት ሞቱን ባያስቀርልን እንኳን ምን ያህል በግድያው አሰቃቂነት፣ግፍነት፣ወንጀልነት ላይ ተወያዬ? እንደው በትንሹ ምን ያህል የሚዲያ ፍጆታ ወስዶ የነገሩን ወንጀልነት አወገዘ? የተጎዱትንስ ሄዶ አፅናንቷል?የት ወደቃችሁ ብሏል?
ሌላው በጣም ወሳኝ ጥያቄ ኦሮማራ ነን ያሉትም ሆኑ፣የአማራና ኦሮሞ ምሁራን መድረኮችን ተካፍሎ የወጣ የኦሮሞ ምሁር ሆነ የኦህዴድ ባለስልጣን ሚዲያ ካገኘ በማግስቱ ነፍጠኛ፣ወራሪ ከማለት ወደኋላ ብሎ ያውቃል?በኦሮማራ ተዓምር አመጣን የሚለው ሽመልስ መስሎኝ መስቀል አደባባይ ላይ ነፍጠኛን ሰበርን ያለው! ቢያንስ “ነፍጠኛ፣ወራሪ” የሚለውን የሞት ፊሽካ የመሰለ ንግግር ሊያስቆም ያልቻለ ድርድር ሆነ ውይይት፣ ማህበር ሆነ ጥምረት ፋይዳው ምንድን ነው?
እንደው ዝም ብሎ መገናኘቱም ጥሩ ነው ከተባለ ሁለት የአንድ ሃገር ሰዎች ተገናኝተው ቀናትን አሳልፈው በመለያየታቸው ላይ የቅሬታ የለኝም።ግን ያለንበት ዘመን እንዲህ የሚያዝናና አይመስለኝም።
እና ትክክለኛው መንገድ ምንድን ነው? ከተባለ፤ ከኦሮማራ ጀምሮ ሌሎች ከዚህ ቀደም በአማራ እና ኦሮሞ መኳንንት መካከል የተደረጉ ጥምረቶች ምን የፈየዱት? ብሎ መገምገም፣ ከብዙ ውይይት ጥምረት በኋላም ነገሩ ፈቀቅ እንዳይል በማድረጉ ረገድ የትኛው ወገን ነው አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ያለው? ለዚህ አሉታዊ ተፅዕኖው ምን አይነት ሃላፊነት ይውሰድ? ዛሬ ህብረት ፣ጥምረት ብሎ ነገ ነፍጠኛ ወራሪ የሚለውን የሞት ጥሩምባ የመንፋቱ መንስኤው ምንድን ነው?የሚለውን አብስሎ መነጋገሩ እንጂ ሌላ አዳዲስ ጥምረቶችን በአዳዲስ የስብሰባ ቦታዎች ማድረጉ ሲሰሙት ለጆሮ መልካም ከመሆኑ ባሻገር የደሃውን ህዝብ የቢለዋ ሞት የሚያስቀር አይመስለኝም።