አባይ ነህ ካሴ
መስቀልን ሥራ እንጅ ቃል አይገልጠውም። ኹለት ጌታ መኾን አይቻልም። መስቀል ተራኪ እና መስቀል ገፊ በአንድ ራስ ኹለት ምላስ።
የመስቀል ቀባሪዎች መጀመሪያ የቀበሩት በሕሊናቸው ነው። ቀጥለው በተግባር። እነዚያ ቢያንስ ከቀበሩት ወዲያ አፋቸው ተለጉሟል። ዘመነኛው ቀባሪ ግን መስቀሉን እየሰበከ ይቀብራል። ከፊተኞቹ ስሕተት መማሩ ይኾናል።
ቀዳማዊቷ ዕሌኒ መስቀሉን ከተሸሸገበት አገኘች። አስቆፍራ አወጣች። የእርሷ የመንፈስ ወራሽ በኾነችው ዕሌኒ ምድር ግን አዲስ ቀባሪዎች መጡ። አለቆቻቸው ደግሞ ስለ ዕሌኒ ፈተና እና ድል የማያምኑበትን ይሰብኩናል። ዕሌኒነት እንደ ዳግማዊቷ ዕሌኒ በሥራ ይገልጡታል እንጅ በተሽሞነሞነ ቃል አይገኝም። “በአፎሙ ይድኀሩ ወበልቦሙ ይረግሙ” ይልባቸዋል። በአፋቸው ይባርካሉ በልባቸው ይረግማሉ ማለቱ ነው። መዝ ፷፩፡ ፬።
እንዴት በዕሌኒ ቦታ መስቀል ይቀበራል?
* * *
መስቀል ተራኪ እና መስቀል ገፊ በአንድ ራስ ኹለት ምላስ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ብለዋል ለታሪክ ይቀመጥ ….
* * *
እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት የሚከተለው ነው፦
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ።
በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል የድልና የፈተና ምልክት ነው። አባቶቻችን ያለ ፈተና ክብር አይገኝም ይላሉ።
መስቀሉም በአንድ በኩል እስከ ሞት የሚደርስ መሥዋዕትነትንና ፈተናን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ሊያስቀረው የማይችለውን ድል አድራጊነትን ያስታውሰናል። ሀገር ልቃ እንድትወጣ በሁለቱም ውስጥ ታልፋለች። በፈተናና በድል።
ፈተናው ብቻ ቢሆን ተስፋ በቆረጥን ነበር። ግን ድል እንዳለ ስለምናምን መከራውን ተቋቁመን እናልፈዋለን። ድል ብቻ ቢሆንም ተዘናግተን በተቀመጥን ነበር።
የምትፈለፈል ቢራቢሮ ከዕንቁላሉ ለመውጣት የምታደርገው ትግል፤ ለጥንካሬዋ አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ፤ በፈተና ውስጥ በጽናትና በትግል ማለፋችንም መሠረተ ጽኑ ያደርገናል።
አንዳንዶች ስለፈተናው ብቻ ያወራሉ። ስለዚህም ተጨንቀው ሕዝብን ያስጨንቃሉ። ሰው ፈተናን ብቻ ካሰበ የዓለም መጨረሻ የደረሰ ይመስለዋል። ነገሮችን ሁሉ ያለቀላቸውና ያበቃላቸው አድርጎ ያያቸዋል።
ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ስትነሣ ብዙዎቹ ስለመቀበሩ ብቻ ነበር የሚነግሯት። የት እንደተቀበረ እንደማይታወቅ፤ ከተቀበረ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ፤ ለማውጣት አስቸጋሪ የሆነ፤ ሁኔታው ሁሉ ተስፋ እንደሚያስቆርጥ ነበር የሚነግሯት። እርሷ ግን እንደተቀበረ ብቻ ሳይሆን እንደሚወጣም ታምን ነበር። እንደጠፋ ብቻ ሳይሆን ሊገኝ እንደሚችልም ታምን ነበር።
እነርሱ ስለ ፈተና ሲናገሩ፤ እርሷ ግን ከፈተናው ወዲያ ስላለው ድል ጭምር ነበር የምታወራው። ልዩነታቸው እዚህ ላይ ነበረ።
‹ፈተና› ደካማና ተሸናፊዎችን ሲሰብራቸው በተቃራኒው ለአሸናፊዎች የትምህርት ዕድል ነው።
አሸናፊዎች ከፈተናው ትምህርት ወስደው ይለወጡበታል፤ እንደ ብረት ጠንክረው፣ እንደ ካስማ ጸንተው ይወጡበታል። ፈተና ለሚሸነፉ ሰዎች ተስፋ መቁረጫ ጥቁር ጭንብል ነው።
በፈተናው ይማረራሉ እንጂ ከፈተናው አይማሩም፤ ድቅድቁን ጨለማ እንጂ ደማቁን ብርሃን ሊያዩ አይችሉም፤ የፈተናው መንገድ እንጂ የፈተናው ፍጻሜ በጭራሽ ዐይታያቸውም።
መጽናናትና መዳንን ያገኙበት ውድ ስጦታቸው ነው። ይሄን የሚያውቁ የዚያን ዘመን ጨቋኞች መስቀሉን ሲቀብሩት ዓላማ ነበራቸው።
ክርስቲያኖቹ ትእምርት እንዳይኖራቸውና በተሸናፊ ሥነ ልቡና ውስጥ እንዲኖሩ ይፈልጋሉ።
ልክ እንደ መስቀሉ ጭንቅላታቸውን እንዲቀብሩ፣ ዝቅ አድርገው እንዲያስቡና ዝቅ ያለ መንፈስ እንዲላበሱ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው።
ነገር ግን ይሄ በመስቀሉ የሚያምኑትን አላሸነፋቸውም።
ከዓመታት በኋላ ውድ ስጦታቸውን፣ ያንን የተቀበረ መስቀል በብዙ ጥረትና ትጋት ቆፍረው አውጥተውታል።
የብልጽግና ጉዟችን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እጅግ ወሳኝና ውድ ስጦታችን ነው።
ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት፣ በርሃብና በቸነፈር፣ በልዩ ልዩ ችግሮች ትከሻዋ የጎበጠው ሀገራችን ከሸክሟ የሚያሳርፏት፤ ብሩህ ነገዋን እንድታይ ቀና የሚያደርጓት፤ ክብርና ዝናዋን ከሚመጥን የብልጽግና ደረጃ ላይ የሚያደርሷት ልጆችዋን ትሻለች።
በጥቃቅን ፈተናዎች ሳይሸነፉ፣ በእንቅፋትና በጋሬጣው ተጠልፈው ሳይወድቁ፣ ከመከራው ወዲያ የሚታየውን የሚጨበጥ ተስፋ ይዘው ወደፊት እንዲገሠግሡ ሀገራችን ትፈልጋለች።
ያኔ መስቀሉ ተቀብሮ ሳለ በመስቀሉ ፊት ሦስት ዓይነት ሰዎች ነበሩ።
የመጀመሪያዎቹ መስቀሉን የማይፈልጉትና ከመሬት በታች የቀበሩት ሲሆኑ ዓላማቸው የመስቀሉን ደብዛ ማጥፋት ነበር።
በሁለተኛው ረድፍ ያሉት ተስፋ ቆርጠው ሌላውን ተስፋ ለማስቆረጥ ታጥቀው የተነሡት ናቸው።
በየአጋጣሚው መስቀሉን ቆፍሮ ስለማውጣት ሲነሣ የሚያከላክሉና አብዝተው ስለመከራው የሚናገሩ ነበሩ።
ተአምር ተፈጥሮ እስካልወጣ ድረስ የመስቀሉ ነገር እንዳከተመለትም ያምናሉ። በተቃራኒው ሦስተኛ ላይ ያሉት መስቀሉ እንዲወጣ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፤ ከሁሉም በላይ ‹መስቀሉ ይገኛል› የሚል ጽኑ እምነት የነበራቸው ብርቱዎች ናቸው።
እነዚያ ብርቱ ክርስቲያኖች የተቀበረውን መስቀል ለማየት የበቁት ተራራውን ንደው፤ ክምሩን ቆሻሻ ደረማምሰው፤ አፈሩን ምሰውና ብናኝ አቧራውን በአፍና በአፍንጫቸው ጠጥተው ነበር።
ላብ ሳያስወጣ፣ ጉልበት ሳያብረከርክ፣ አቧራ ሳያለብስና ምንም ሳያስለፋ የሚሳካ መልካም ነገር የለም።
የሀገራችን ዴሞክራሲ የሚሳካው፣ ነጻነትና እኩልነት እውን የሚሆነው ተገቢውን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ተከትለን ስንሠራ እንጂ እንደ ተአምር ከሰማይ የሚወርድልን ነገር አይደለም።
ፖለቲካችን የሚስተካከለው፣ ኢኮኖሚያችን የሚያድገው፣ ብልጽግናችን እውን የሚሆነው ዳር ቆመን በመመልከት ወይም እንደ ታዛቢ አፋዊ አስተያየት በመሰንዘር ሳይሆን ባለቤት ሆነን ስንሠራው፣ የበኩላችንን ማበርከት ስንችልና የውጣ ውረዱ አካል ስንሆን ብቻ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን መከራችንን ከሚያብሱና ፈተናችንን ብቻ ከሚነግሩን መሠናክሎች ማምለጥ አለብን።
እነሱ ዘላለም ፈተናችን ላይ ብቻ እንድንጣድ የሚፈልጉ ናቸው። ዘወትር በልቅሶና በትካዜ እንድንኖር ከማድረግ ውጭ ለቁስላችን መድኃኒት፣ ለተራበ ሆዳችን ምግብ፣ ለታረዘ ገላችን አልባስ አያቀርቡልንም።
በጊዜያዊ ችግሮቻችን እንድንጠመድ ከማድረግ በዘለለ ሥር ለሰደዱ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ አያቀብሉንም።
ከማላዘን ፖለቲካ ምን ጠብ የሚል ነገር እናገኛለን ብንል መልሱ ኪሳራ እንጂ ትርፍ፤ መከራ እንጂ ዕረፍት አይሆንም።
ኢትዮጵያ እስካሁን ተፈትናለች፤ አሁንም እየተፈተነች ነው፤ መጠኑ ቢለያይም ወደፊትም ፈተና ማጋጠሙ አይቀርም።
ዋናው ቁም ነገር ከፈተና በኋላ እንደ ወርቅ ነጥሮ መውጣት መኖሩን አለመርሳት ነው። እሳት ለወርቅ ማቃጠያው ብቻ ሳይሆን ማንጠሪያውም ጭምር ነው።
ይበልጥ በእሳት ሲመታ፤ ይበልጥ ንጹሕ ይሆናል። ይለወጣል። ፈተናዎቻችን ነጥረን እንድንወጣ እንጂ ቀልጠን እንድንቀር አያደርጉንም።
ሀገራችን ወደፊት እንዳትራመድ አስረው የያዟት ትብታቦች የቱንም ያህል ቢበዙ ተበጣጥሰው ማለቃቸው አይቀርም።
ግድግዳ ሆነው መንገድ የዘጉባት ቋጥኞች የቱንም ያህል ቢገዝፉ ተንደው ይወድቃሉ። ሕብዛችን ብሩህ ቀን እንዳያይ የሚያደርጉት የጽልመት መጋረጃዎች በብርሃን ሰይፍ ይቀደዳሉ።
ገፍተው መስቀለኛ መንገድ ላይ ያቆሟት ሲያልፉ፣ ሀገራችን ተስፋ ባላቸው ኅሊናዎች፤ በተባበሩ እጆች፤ በቆረጡ ልቦች፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትና ፍቅር እንዳለ በሚያምኑ ልጆችዋ ብርታት ከችግሮቿ በላይ ከፍ ትላለች፤ ብልጽግናዋም ያለጥርጥር እውን ይሆናል።
መስቀሉ ከተቀበረበት ቀን ይልቅ የወጣበት እለት እንደሚከበር ሁሉ ኢትዮጵያም የድል ታሪኳን እያከበረች መሄዷን ትቀጥላለች።
ከእንግዲህ ሥልጣኔና ብልጽግናዋን አፈር ለሚያለብሱ አካላት ቦታ የላትም።
ለጊዜው መኖራቸው እያወቀች፣ መንገዷን እንደሚቆፍሩ እያየች፣ ‹አንድ ቀን ወደ ቀልባቸው ሊመለሱ ይችላሉ› በሚል ተስፋ ዐይታ እንዳላየ ታልፋቸው ይሆናል።
ነገር ግን በየትኛውም ዕንቅፋት ከመንገዷ አትገታም፡፡
አቧራውን ጠርጋ፣ አፈሩንም ንዳ ታሪክ መቀጠል እንደምትችል፣ ጉድጓድ ሲምሱላት የነበሩም ራሳቸው ሲገቡበት ታያለች። የኢትዮጵያ ድል የፈተናዎቿን ብቻ ሳይሆን የፈታኞቿንም ታሪክ እንደሚዘጋ ምንም ጥርጥር የለውም።
የመስቀል በዓል በሀገራችን ከሃይማኖታዊ ዋጋው በዘለለ ባህላዊ ትርጉምም ተሰጥቶት ይከበራል።
በተለይም በደቡቡ የሀገራችን ክፍል መስቀል የተለየ ግምት ይሰጠዋል።
የተነፋፈቁ የሚተያዩበት፣ የተለያዩ የሚገናኘበት፣ ዝምድና የሚጠነክርበት፣ አንዱን ምዕራፍ ጨርሰው ወደሌላ ምዕራፍ የሚሸጋገሩበትና ብሩህ ተስፋ የሚበሰርበት እለት ነው።
ቤተሰብ ተሰባስቦ በደስታ የሚያሳልፈው፣ ስለ ቀጣዩ ጊዜ የሚመካከሩበት፣ ልጆች ከወላጆቻቸው ምርቃት የሚቀበሉበት፣ ማኅበረሰባዊ ዕሴት የሚጠናከርበት ዕለት ነው።
ይሄንን ሀገራዊ አንድነትና ትብብራችንን የሚጠናከርበት የመስቀል በዓልን ስናከብረው ከመብላት ከመጠጣቱ ጎን ለጎን የበዓሉን ሰሞን ቁም ነገር የምናከናውንበት እንዲሆን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ፣ በድንገተኛ ጎርፍ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን አስታዋሽ ይፈልጋሉ።
ስለዚህ ከበዓሉ ጎን ለጎን የተቸገሩትን ከጎናችሁ አለን ልንላቸው፣ የድጋፍ እጃችንን ልንዘረጋላቸው ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈ ወቅቱ አንዳንድ ሰብሎች አፍርተው ለመሰብሰብ ዝግጅት የሚጀምሩበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ሳምንታት አርሶ አደሩን ለማገዝ፣ በዝናብ የሚበላሽ ሰብል እንዳይኖር ተጠቃሎ እህሉ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ከጎናቸው ሆነን ርብርብ ለማድረግ ከወዲሁ ልናስብበትና ቅድመ ዝግጅት ልናደርግ ይገባል።
በመጨረሻም፣ ችላ በማለታችን የተነሣ የመስፋፋቱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ እንደ ሀገር እያደረሰብን ያለው ችግር ለመቀነስ የየበኩላችንን አስተዋጽኦ ከማበርከት መቦዘን የለብንም፡፡
በዓሉንም ስናከብር የበሽታው ሥርጭት ከሚጨምሩ ድርጊቶች በመቆጠብና ተገቢውን የጥንቃቄ ርምጃዎች ተግባራዊ በማድረግ እንዲሆን እያሳሰብኩ በዓሉ የሰላም፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ እንዲሆን እመኛለሁ።
በድጋሚ እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ። ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።