>

በዓለ መስቀል፤  (ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው)

በዓለ መስቀል፤    

ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል የምታከብረው መስከ ረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ነው።እነኚህም አይሁድ በክፋት ቀብረው ሰውረውት የነበረውን መስቀል ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት እና መስቀሉ የተገኘበት ዕለታት ናቸው።ክቡር መስቀሉ ከክርስቲያኖች ተሰውሮ የኖረው ለሦስት መቶ ዓመታት ነው።
፩፥፩ ክቡር መስቀሉ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
             መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር፦በክፋት የተመሉ አይሁድ፥ በጌታ መስቀል እና መቃብር ምክንያት ይፈጸሙ የነበሩትን አያሌ ተአምራት አይተው በምቀ ኝነት መነሣሣታቸውን ይተርካል።አይሁድ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ እስከ ፷፬ ዓ.ም. ድረስ ምንም ኃይል አልነበራቸውም።ከ፷፬ ዓ.ም. በኋላ ግን ራሳቸውን ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ዓመጽ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።በዚህን ጊዜ ክርስቲያኖ ቹን ወደ ጌታ መስቀል እና መቃብር እንዳይቀርቡ ከልክለው ቦታውን የቆ ሻሻ መድፊያ አደረጉት።ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥፍራው ትልቅ ጉብታ ሆኖ በአካባቢዎች ከሚ ገኙ  ጉብታዎች ጋር ተመሳሳለ።ከዚህም ጋር እሥራኤል በየጊዜው ይማረኩ ስለ ነበረ፥ ከምርኮ ሲመለሱ የከተማይቱ መልክ እየተለዋወጠባቸው መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክ ለኛ ጉብታ ለመለየት አልተቻለም ነበር።በተለይም ከ፩፻፴፪ – ፩፻፴፭ ዓ.ም. በተደረገው ጦር ነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ጠፍታ ነበር።ዳግመኛም ንጉሥ ሐድርያን በ፩፻፴፭ ዓ.ም. ኢየሩሳ ሌምን በአዲስ ፕላን በመሥራቱና በጎልጎታ የቬነስን መቅደስ በመገንባቱ ክርስቲያኖቹ  ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ ሆነባቸው።ያን ጊዜ ጎልጎታ ከከተማዋ ውጪ ነበር፥ዛሬ ግን በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ክልል ይገኛል።
፥፪፦ መስቀሉ እንዴት ሊገኝ ቻለ?
           ክቡር መስቀሉን ፈለጋ ያገኘችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ኅሌኒ ናት።ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች ሙሉ ነፃነት የሰጠ የሮም ንጉሥ ነበር።ከዚያ በፊት ምንም ነፃነት አልነበራቸውም።ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የሰጣቸው መብት፦፩ኛ ቤተ ክርስቲያንን ከግብር ነፃ አደረጋት። ፪ኛ፦ከመንግሥት ገቢ ለቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ድርሻ ሰጣት። ፫ኛ፦ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች የበዓል ቀን በመሆኗ በግዛቱ ሥራ እንዳይሠራ በ፫፻፳፩ ዓ.ም. አወጀ። ፬ኛ፦ለቤተ ክርስቲያን ኑዛዜ የመቀበልና ውርስ የመውረስ መብት ሰጣት። ፭ኛ፦በክርስቲያኖች መካከል ለሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባት፥ወንጀል ነክ ላል ሆነ ጉዳይ ለኤጲስ ቆጳሳት የዳኝነት ሥልጣን ሰጣቸው። ፮ኛ፦ክርስትና የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ።በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የመዳን መልእክት እያወጀች ሐዋርያዊ ጉዞዋን እንድትቀጥል ያደረገ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ነው።ንጉሥ ቆስ ጠንጢኖስ በመስቀል ምልክት የተደረገለት ተአምር ነበር።ይኸውም የሮምን የምዕራቡን ክፍል ይገዛ የነበረው ማክሴንዲዮስ የጦር ኃይሉን ባዘመተበተት ጊዜ፥እርሱም በበኲሉ «ምታ ነጋሪት፥ ክተት ሠራዊት፤» ብሎ ለጦርነት ተዘጋጀ።ገና በጉዞ ላይ እንዳለም፦«በዚህ ድል ታደርጋለህ፤» የሚል በመስቀል ቅርጽ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈረ ሰማይ አየ።በዚህም እየተመራ ሄዶ ድል አደረገ።በዚህን ጊዜ፦ ሠራዊቱ በፈረሱ አንገት፥በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ እንዲያደርግ አወጀ።ሮምን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መግዛት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ለአርባ ዓመታት ለአራት ተከፍላ በኋላም ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር።
            እናቱ ንግሥት ኅሌኒ በልጇ ዘመን የተገኘውን የክርስትና ነፃነት ተጠቅማ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክቡር መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች።በዚያም ጉብታ የሆነውን ሥፍራ ሁሉ በማስቆፈር ብዙ ብትደክምም መስቀሉን ለማግኘት አልቻለችም።በዚህን ጊዜ ኪራኮስ የተባለው አረጋዊ፦ «ደመራ አሰደምረሽ፥ ዕጣን አፍስሰሽበት ብታቀጣጥይው ጢሱ ይመ ራሻል፤» ባላት መሠረት ሳትጠራጠር አደረገችው።የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ እንደ ቀስተ ደመና ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመለከታት።ቁፋሮ ውም መስከ ረም ፲፯ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ተፈጸመ።የተገኙት ሦስት መስቀሎች ስለነበሩ የክርስቶስን መስቀል በተአምራቱ ለዩት።ዕውር አበራ፥አንካሳ አረታ፥ለምጽ አነጻ፥ሙት አስ ነሣ።ንግሥቲቱም የከበረ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ በክብር እንዲያርፍ አድርጋለች።
፪፦ መስቀል
           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ተላልፎ በመሰጠት ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፥ክቡር ደሙንም ያፈሰሰበት መስቀል ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው።
፪፥፩፦ ድኅነታችን የተፈጸመበት (መዳናችን የተረጋገጠበት) ነው፤
           «ኢየሱስም ሆምጣጣውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ፥ አለ፤» ይላል።ዮሐ ፲፱፥፴። በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን (መዳናችን) ነው።ይኸውም የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው።ሉቃ ፩፥፴፩።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፥ኃጢአታችንም ተሰረየልን።» ብሏል።መድኃ ኒት ከድንግል ማርያም መወለዱን ለእረኞች አስቀድመው የሰበኩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው።ሉቃ ፪፥፲፩።
፪፥፪፦ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተወገደበት ነው፤
            አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው የወደቀባቸው የሥጋና የነፍስ መርገም ለሰው ልጅ በጠቅላላ ተርፎት ነበር።«ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአ ዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው።» ይላል። ሮሜ ፭፥፲፬።ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው።በኦሪቱ እንደተጻፈው በእንጨት ተሰቅለው የሚ ሞቱ ርጉማን ነበሩ።ዘዳ ፳፩፥ ፳፫።ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረ ገመ ነው፥ተብሎ ተጽፎአልና፤ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ (መር ገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ስላመጣብን ኃጢአት ተላልፎ በመሠዋት) ከሕግ እርግማን ዋጀን።» በማለት ገልጦታል።ገላ ፫፥፲፫።ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢ አታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።» ብሏል።፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬።
 
፪፥፫፦ ዲያቢሎስ የተሸነፈበት ነው፤
            ጥንተ ጠላታችንን (ገነትን ያህል ርስት፥ እግዚአብሔርን ያህል አባት ያሳጣንን ዲያቢሎስን) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገልን በመስቀሉ ነው። « ጥልን በመስ ቀሉ ገደለ፤» ይላል።ኤፌ ፪፥፲፮።ጥል የተባለው ለሰውና ለእግዚአብሔር መጣላት ምክን ያት የሆነ ዲያብሎስ ነው።እኛም በኃይለ መስቀሉ ድል እያደረግነው የምንኖር ሆነናል።
፪፥፬፦ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤
            የጥል ግድግዳ የተባለው ኃጢአት ነው።እርሱም ሰውና እግዚአብሔርን ለያይ ቷቸው ኖሯል።«በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለያይታለች፥ ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሠውሮታል።» ይላል።ኢሳ ፶፱፥፩።ይህ ከእግዚአብሔር ለያይቶን እግዚአብሔርን ሰውሮብን የኖረ የጥል ግድግዳ (በዲያቢሎስ ምክር የተሠራ ኃጢአት) የፈረሰው በመስ ቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው።«በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ፤» ይላል። ኤፌ ፪፥፲፭።
፪፥፭፦ እርቅ የተፈጸመበት ነው፤
           ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። ሰውና እግዚአብሔር በመታረቃቸው ነፍስና ሥጋ፣ሰውና መላእ ክት፣ሕዝብና አሕዛብም ታርቀዋል።እኛ በበድልን እርሱ ክሶ (የደም ካሣ ከፍሎ ) ታርቆናል።«ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚ አብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።» ይላል።ሮሜ ፭፥፲፣ ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፰፣ ኤፌ ፪፥፲፮፣ «ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ።» የሚ ልም አለ። ቆላ ፩፥፳።
፪፥፮፦ አምላካዊ ይቅርታ የተገኘበት ነው፤
           «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።» በማለት ገርፈው የሰቀ ሉትን በቃሉ ይቅር ብሎአቸዋል።ሉቃ ፳፫፥፴፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ በሞቱ የሰውን ዘር በጠቅላላው ይቅር እንዳለው ሲናገር፦ «አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣ ችሁና ንጹሓን፥ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።» ብሏል። ቈላ ፩፥፳፪።
፪፥፯፦ አምላካዊ ሰላም የተሰጠበት ነው!
            ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥ ቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ስሙም ድንቅ መካር፥ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።» በማለት ትንቢት የተናገረለት አምላክ ፍጹም ሰላምን የሰ ጠን በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት ነው።ኢሳ ፱፥፯።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።» ብሏል።ኤፌ ፩፥፲፯።ሰላም ማለት ከኃጢአት ነፃ መሆን ነው።
፪፥፰፦ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው።
           ጌታችን የማታ ተማሪ የነበረውን ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፦ «እግዚአ ብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤» ብሎታል።ዮሐ ፫፥፲፮።ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የጻፈውን የጌታን ትምህርት መሠረት አድርጎ፦«በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፥በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥እርሱ ወደደን እንጂ እኛ የወደድነው አይደለንም፥ኃጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።» ብሏል።፩ኛ ዮሐ ፬፥፱-፲፩።
፪፥፱፦ የገነት በር የተከፈተበት ነው፤
           ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው፥ድኅነተ ምዕመናንንም በመስቀል ላይ የፈጸ መው ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነትን ለመክፈት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፥በቀኙ ተሰቅሎ፥ «አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፤» እያለ ሲማጸነው የነበረውን ወንበዴ፦ «እውነት እልሃ ልሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ፤» ብሎታል።ሉቃ ፳፫፥፵፪-፵፫።ስለሆነም፦
፪፥፲፦ በመስቀሉ እንመካለን፤
            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት ( ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት የሆነበት)፥እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት (እኔም በዓለም ዘንድ ሙት የሆንኩ በት)፥ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር  ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፤»ብሏል። ገላ ፮፥፲፬።በመሆኑም ዓለምና ቅዱስ ጳውሎስ በደሙ በከበረ በመስቀል፥በጌታ ደም ላይ በተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን እና በደሙ በጸናች ወንጌል ምክንያት ተለያይተዋል። አንዳ ቸው ለአንዳቸው ሙት ናቸው።ዓለም ሕያው የሆነችልን፥እኛም ሕያው የሆንላት የሚመስ ለን የዓለም ፈቃድ ፈጻሚዎች ከቅዱስ ጳውሎስ ልንማር ይገባል።ዓለም ታልፋለች፥እኛም እናልፋለንና።
፥፲፩፦ በመስቀሉ ከአጋንንት ጦር እንድናለን
           ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፦ «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት (ከአጋን ንት ጦር ) ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህም እንዲድኑ።» ያለው ስለ መስቀል ነው።መዝ ፶፱፥ ፬።በመሆኑም በመስቀል ምልክት አማትበን፥ከአጋን ንት ፈተና እንድናለን።
፪፥፲፪፦ መስቀል ኃይላችን ነው!
           መስቀልን በእጅ መጨበጥ፥በአንገት ማንጠልጠልና መሳለም በዓለም ዘንድ ሞኝ ነት ነው፥ለክርስቲያኖች ግን የእምነት ሥራ ነው። «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።» ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፰።በመሆኑም በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተገለጠ ኃይለ እግ ዚአብሔር እስከ ዘለዓለሙ አይለየንም።
፪፥፲፫፦ ለመስቀሉ እንሰግዳለን!
           ቅዱስ ዳዊት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።» በአለው መሠረት የጌታችን እግሮች በመስቀል ላይ፥ ያውም በቀኖት ላይ ስለቆሙ ለመስቀሉ እንሰግዳለን። መስቀሉን በደሙ ቀድሶታልና፥ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንሰጣለን።እግዚአብሔር በረድኤት በደብረ ሲና ራስ በቆመ ጊዜ፥ «ወደዚህ አት ቅረብ፥ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደ ሰች ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤» በማለት ሙሴን አስተምሮታል።ዘዳ ፫፥፭።እንኳን ፈጣሪ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንኳ የቆመበትን መሬቱን፥አፈሩን በመቀደሱ፦ «አንተ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ።» በማለት ኢያሱን ሲያዘው እርሱም የታዘዘውን ሲያደርግ እናገኛለን።ኢያ ፭፥፲፭።
          እንግዲህ መሬቱን፥አፈሩን የቀደሰ አምላክ ፦ሥጋውን የቆረሰበትን፥ ደሙን ያፈሰሰ በትን፥ ነፍሱንም አሳልፎ የሰጠበትን መስቀል አልቀደሰውም ለማ ለት እንዴት ይቻላል? ፈጽሞ አይቻለም።ለመሆኑ ከቅድስት ኅሌኒስ ምን እንማራለን? ያን ጊዜ የተቀበረው መስ ቀሉ ነበር፥በመሆኑም በብዙ ድካም ከወርቅ ዙፏኗ ወርዳ ከአፈር ላይ ተቀምጣ፥ቆፍራ አስ ቆፍራ መስቀሉን አውጥታለች።ዛሬ የተቀበረው በመስቀሉ የተገኘው ፍቅርና ሰላም ነው። ፍቅር በጥላቻ፥ሰላም በጦርነት፥አንድነት በመለያየት፥እምነት በክህደት፥መንፈሳዊነት በሥ ጋዊነት፥የሕዝቦች ውህደት በዘረኝነት ቆሻሻ ተቀብሮአል።ይኸንን ቆፍረን ካወጣን ያን ጊዜ የዘመኑ ኅሌኒዎች እንሆናለን።መስቀሉን ተሸክመን በጥላቻና በዘረኝነት ቆሻሻ የተቀበርንም በቅድሚያ ራሳችንን ቆፍረን እናውጣ፥ካልሆነልን ደግሞ መስቀሉን ለመስቀሉ ጌታ አስረ ክበን ዘወር እንበል፥እንቅፋት አንሁን።ዘመኑን ከተቀበርንበት የምንወጣበት ያድርግልን። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅ ነት፥ የመስቀሉ በረከት አይለየን፥ አሜን።
Filed in: Amharic