>
5:13 pm - Friday April 18, 2988

ጌታ ሆይ ተሎ ፍረድ!! (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ጌታ ሆይ ተሎ ፍረድ!!

 

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ


‘’የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሀል፤ አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ’’ (ዘፍጥረት 4፣10-11)

 

ጥቅምት 12 ቀን 2012ዓ.ም. አቶ ጃዋር መሀመድ በፀጥታ ሀይሎች ተከብብሁ በሚል ስበብ በተፈጠረ ሁከት መንግስት ባመነው ቁጥር እንኳን ከ86 በላይ ሰዎች እንደሞቱ እና ከስምንት ወራት በኃላም ደግሞ ሰኔ 23 እና 24 2012ዓ.ም. የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በዚህው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በርካታ ሰዎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንደተገደሉ እና በርካታ ንብረት እንደወደመ ይታወቃል፡፡ ጭፍጨፋው እና ጥቃቱ ያተኮረው በኦርቶዶክስ ክርሲቲያኖች እና በአማራዎች ላይ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ለዚህ ጥቃት ተሳታፊ የነበሩት ወንጀለኞች እና የየወረዳው አመራሮች በጥቃቱ ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና ለፍትህ እንደሚቀርቡ/እንደቀረቡም በመንግስት ሚድያ ቢገልፁም፤ ነባራዊ ሁኔታው ግን የተለየ እንደሆነ ተጠቂዎች (ለኢሳት መስከረም 14 ቀን 2013ዓ.ም. ባስተላለፈው ዜና) እንደሚከተለው ገልፀዋል፡፡

           የሰው ህይወት ያጠፉ ወንጀለኞች እና ንብረት ያወደሙ ወጣቶች በህግ ቁጥጥር ስር ባለመዋላቸው አሁንም ስጋት አለን በማለት አካባቢውን ለቀው እየወጡ እንደሁኑ ለኢሳት ገልፀዋል፡፡ የፅጥታው ሁኔታው አሁንም አስተማማኝ እንዳልሆነ እና ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ነው ያሳወቁት፡፡ እንደተጠቂዎች ገለፃ ዋና ዋናዎች አጢፊዎች እንዳልተያዙ እና ፖሊሶች ወንጀለኞችን ይዘው እንደሚለቋቸው፣ ፖሊሶች እና የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በጉዳዩ ተባባሪ እንደሆኑ፣ አይዟችሁ ሲሉዓቸው እንደነበር፣ አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ ከምትታረዱ ተብለው ተጠቂዎች እንደሚዛትባቸው፣ አሁንም እንደሚያስፈራሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ 

          መንግስት ተጠቂዎችን ወደ ቄያቸው መልሻለሁ ቢልም የጥቃት ሰለባዎች ግን አሁንም ወደ ቦታቸው እንዳልተመለሱና እንኳን ለማቋቋም ይቅርና ለህይወታችው አስጊ ሁኔታ እንደሆነ እና ከመንግሰት ምንም አይነት እርዳታ እንዳልተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮምኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ የክልሉ መንግስት የተፈናቀሉትን እያቋቋመ ነው የሚል መልስ እንደሰጡ እና የሚከሱን አካላት ሌላ ፍላጎት ያላቸው ናቸው እንዳሉ ኢሳት ዘግቧል፡፡ እንደ ኢሳት ዘገባ ተጠቂዎች ግን ዛሬም የሰቆቃን ህይወት እንደሚመሩ አስታወቀዋል፡፡

በትህነግ/ኢህአዲግ መራሹ ስርዓት ጊዜ በመንግስት ሚዲያዎች የሚሰሙ ዜናዎች ከነባራዊ ሁኔታው እጅጉን የራቁ እና የሀሰት ዘገባ ሲቀርቡ እንደነበር ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦህዴድ/ ብልፅግና መራሹ ስርዓት ተኮትኩቶ ባደገበት ስርዓት ዘየ መጓዙ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጲያውያን በባዕድ ሀገር መብታቸው ተጠብቆ እየኖሩ ሀገር ቤት ያለው ኢትዮጲያውያን ግን በገዛ ሀገራቸው ይገደላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ይፈናቀላሉ፡፡ በኦርቶዶክስ ክርሲቲያን እና በአማራ ደም እንዲህ እየተቀለደ እስከ መቸ እንደሚኖር አላውቅም? ምንም እንኳን ሰውን ባትፈሩ የፍጥረታት ባለቤት የእነዚህን ሰዎች ደም፣ግፍና ሰቆቃ ከእጃችሁ ይቀበላል እና እሱን ፍሩት፡፡ ጌታ ሆይ ተሎ ፍረድ!!

Filed in: Amharic