” ወዲ ፣ አፈወሪቂ ማናቸው ? ”
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ ( ለንደን)
የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን ያዘዘው ዋነኛ ትእዛዝ “ሰው ሁን” የሚል እንደነበር በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ እናነባለን፡፡ ሰው ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ሁን ተብሎ መታዘዙ ሰው መሆን በስጋና በደም ጸንቶ ከመንቀሳቀስ የዘለለ ቁም ነገር መለኪያ እንዳለው የሚያስረዳ እውነት ነው ::
ወዲ አፈወርቂ ከወደ ባህረ ነጋሽ (ኤርትራ ) ከሰሞኑ ብቅ ብለው ” ኢትዮጵያ ጎረቤት ሐገራችን ሳትሆን ሐገራችን ናት !” ሲሉ በመደመጣቸው ብዙዎቹን አ ጃይብ !! አስኝቷል ::
የእስራኤሉ ንጉስ ” ሰው ” ሁን አይደለ ያሉት ::ሰው ስትሆን እምነት ዋስትና ብሔራዊ ማንነት ይፈታተንሐል ::ስለዚህ ወዲ አፈወርቂ ” ኢትዮጵያ ጎረቤት ሐገራችን ሳትሆን ሐገራችን ናት !” ቢሉ ምን ያስገርማል ?” ዕውነትን መናገር ትልቅ ድፍረት፣ ይጠይቃል :: እውነትን ማወቅ ደግሞ ትልቅ ጥረት ይጠይቃል።ዕውነትን ለመኖር ከሁሉ የሚበልጥ መስዕዋትነት ያስከፍላል። ምክንያቱም ዕውነትን ለመረዳት ብሩህ ልቦና፣ ለመናገር ንፁህ ህሊና፣ ለመኖር ደግሞ የሰውን ሁለንተና ይጠይቃል።”
በርግጥም ሁሉም ሰዎች ስለ እውነት ማሰባቸው እውነታ ቢኖረውም ሁሉም ሰዎች በትክክል ስለ ብሔራዊ ክብራቸው ማሰባቸው ግን በጥያቄ ምልክት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ይበቃኛል :: ልብ ያለው ልብ ይበል ::” ሰው ሁን ” አይደል ቁም ነገሩ ::
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወዲ አፈወርቂ (ኢሱ) የህይወት ታሪካቸው ሲፈተሽ ፣ ከተንቤኑ ተወላጅ ክብር አፈወርቂ አብርሀና ከአድዋዋ ተወላጅ የወ/ሮ አዳነች ልጅ ሲሆኑ ሁለት ሴት እህቶችና አራት ወንድሞች ሲኖራቸው ከሳቸው ጋር በጠቅላላ ሰባት ናቸው ::ታዲያ ከዘር ሐረጋቸው ስንነሳ ወዲ አፈወርቂ (ኢሱ) በናትም ባባትም የትግራይ ተወላጅ ናቸው :: አባታቸው ክብር አቶ አፈወርቂ አብርሀ በመቀሌ ከተማ ለብዙ አመታት እስከ ጡረታ ጊዚያቸው ድረስ በመሬት ይዞታ ሚኒስትር ሰርተዋል :: አጎታቸውም ደጃዝማች ሰለሞን አብርሀ በወቅቱ የወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ነበሩ ::
ወንድሞቻቸው ፣ አማረ አፈወርቂ ….አማኑኤል አፈወርቂ …ኤርምያስ አፈወርቂ ፣ ዮናስ አፈወርቂ ሲሆኑ እሳቸውን ጨምሮ አምስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ሲሆኑ ወ/ፅጌረዳ አፈወርቂና ወ/ሮ አሪያም አፈወርቂ ሁለቱም ታናናሽ እህቶቻቸው ናቸው :: ወዲ አፈወርቂ ለቤተሰቦቻቸው፣ሁለተኛው ልጅ ናቸው ::ስለዚህ ( ኢሱ ) ወዲ አፈወርቂ ” ኢትዮጵያ ጎረቤት ሐገራችን ሳትሆን ሐገራችን ነች !” ሁሉም ፣ኤርትራዊ በሀገሩ ጉዳይ ዘብ መቆም አለበት ቢሉ ምን ይገርማል ??¨
በተበላሸ የታሪክ ፍርስራሽ ላይ መብቀላችን የሁላችንም ጥፋት አይደለም። በተበላሸው የታሪክ ፍርስራሽ ላይ ስንነታረክ የምንሞት ከሆነ ግን ተጠያቂዎቹ እኔና አንተው ነን ። ለማንኛውም በወዲ አፈወርቂ የህይወት ታሪክ ዙሪያ እንደ አስፈላጊነቱ በሰፊው እመለስበታለሁ ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ ::