አገሬን ፋና ላምሮት ላይ አየኋት ፤ ፈራኋትም…!!!
(በድሉ ዋቅጅራ)
.
.
ለወትሮው ሪሞት ጥሎኝ ካልሆነ የፋና ላምሮትን የድምጻውያን ውድድር አልከታተል፡፡ ትላንት መጨረሻውን አየሁት፡፡ ውጤቱ ከታወቀ ጀምሮ የተወዳዳሪዎቹ አካባቢ ሰዎች በተለመደው መንገድ ጎጥ ለይተው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ውጊያ ገጥመዋል፡፡ አንዳንዶቹም ለሰፈራቸው ተወዳዳሪዎች የሽልማቱን ያህል ገንዘብ አዋጥተን እንሰጣለን እያሉ ነው፡፡ ይህ አይደንቅም፣ ቅኝታችን ሁሉ የጎጥ ነው፡፡ በጎጥ ሰው በሚገደልበት ሀገር በጎጥ መሸለም ከጽድቅ ይቆጠራል፡፡ ሰዎች ስለዚህ ነገር ሲያወሩ ያሳዝነኛል፡፡
.
ትልቁ ልናወራበት፣ ልናወግዘው የሚገባው ጉዳይ ፋና የህዝብን ድምጽ የተጠቀመበት መንገድ ነው፡፡ ለ27 አመታት በድብቅ በአስተዳዳሪዎቹ እየታዘዘ ያካበተውን ልምድ በቀጥታ ስርጭት ሲጠቀምበት ማየት ተስፋ ማስቆረጥ ብቻ አይደለም – ያስፈራል፡፡
.
እውን ቴሌ ለስድስት ተወዳዳሪዎች የሚሰጥ ድምጽ መሰብሰብ አቅቶት ነው? እንዳሉት አቅቷቸው ከሆነ ለምን እስከደረሱበት ደረጃ ያለውን አልወሰዱም? እኔ እስካየሁት እንኳን በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ከፍተኛው 26 000፣ ዝቅተኛው5000 ነበር፡፡ ለምን ችግር ካለ ሌላ ጊዜ አይካሄድም? መልሱ ቀላል ነው፤ እነሱ የህዝብ ድምጽ አያስጨንቃቸውም፤ ለእነሱ የህዝብ ድምጽ ፕሮፓጋንዳና የገቢ ምንጫ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡
.
ለመሆኑ ፋናና ቴሌ ስንት ስንት ሚሊየን ደረሳቸው? ፋና2ኛ እና 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች እዚያው ላይ ሽልማት ማዘጋጀቱን ስናይ ገቢው ምን ያህል እንዳስፈነደቃቸውና ስሜታዊ እንዳደረጋቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ ፋና ያላግባብ የሰበሰበውን የህዝብ ገንዘብ መመለስ አለበት፤ በንቀት ለወረወረው የህዝብ ድምጽም በግልጽ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል፡፡
.
ሀገሬ ውስጥ ምርጫ ከተጀመረ ጀምሮ ድምጽ ይጭበረበራል፤ ህዝብ ድምጼን ብሎ ይነሳል፤ በዚህ የተነሳ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ በፋና የተደረገው ይኸው ነው፤ ከህዝብ ድምጽና ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ፣ ገንዘቡን ወስዶ ድምጹን አይናችን እያያ ወረወረው፡፡ በዚህ የተነሳ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ጦርነት ተጀመረ፡፡
.
በመሰረቱ እኔ ትላንት ስድስቱምን ተወዳዳሪዎች ወድጃቸዋለሁ፡፡ በእርግጠኝነት ማሸነፍ አለበት የምለው አልነበረኝም፡፡ በዳኞችና በህዝብ ድምጽ የሚያሸንፈውን ለማወቅም ጉዋግቼ ነበር፡፡ የሆነው ግን እንዳያችሁት ነው፡፡
.
አንደኛ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታና ለህዝብ ድምጽ መከበር ታላቁን ድርሻ የሚጫወቱት የብዙሀን መገናኛዎች ናቸው፤ እንደፋና ያሉ ከሀያ ሰባት አመት በሽታ ያላገገሙ ተቋማትን ይዘን (እኔ አሁን ሌሎቹም ተቋማት ተመሳሳይ ናቸው የሚል አመለካከት እያሳሰበኝ ነው) እንዴት ነው የህዝብ ድምጽ የሚከበርበት ዲክራሲያዊ ምርጫ የምናካሂደው? ያስፈራል፡፡
.
ሁለተኛ፣ በየአካባቢው፣ ‹‹እገኔ (የጎጣችን ተወዳዳሪ) ነበር ማሸነፍ ያለበት›› ብሎ ከመሟገትና በህዝብ ድምጽ ላይ ከተፈጸመው ንቀት የትኛው ነው መሰረታዊ? አንድ ሰው እንደሚያሸንፍ ይታወቅ ነበር እኮ! ውሳኔው ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደረገው የህዝብ ድምጽ አለመከበሩና እስኪቋረጥ ድረስ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ ተወዳዳሪዎች አለማሸነፋቸው ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ከፍተኛየህዝብ ድምጽም አግኝተው ሊሸነፉ ይችሉ ይሆናል፤ የህዝብ ድምጽ ምን ያህል ዋጋ እንደተሰጠው አላውቅም) ይም ሆነ ይህ ግን የህዝብ ድምጽ አልተከበረም፡፡ በአጠቃላይ የህዝብ ድምጽ አለመከበር ነው ችግሩን የፈጠረው፤ እና ይህ አያሳስብም? ነገ በድምጻችን መንግስትችንን መምረጥ ስለመቻላችን ምን ዋስትና አለ? እባካችን እንደህዝብ ትልቁን ጥያቄ ቀድመን እንመልስ፡፡