>
5:13 pm - Friday April 19, 7957

ኢትዮጵያ ዓምዷና ውዱዷን አጣች! ለራሳችን እናልቅስ...(ከይኄይስ እውነቱ)

ኢትዮጵያ ዓምዷና ውዱዷን አጣች

ለራሳችን እናልቅስ

ከይኄይስ እውነቱ


‹‹የማይቀር ዕዳ የሞት እንግዳ›› ይላሉ ሊቃውንት አባቶቻችን፡፡ ከኵት እስከ ሽበት÷ እስከ መጨረሻው ሕቅታ ድረስ ኢትዮጵያዊ ሆነው፣ ኢትዮጵያን ብለው ለኢትዮጵያ ሲሉ ኖረው፣ ከስንብታቸው አንድ ወር በፊት ሰውና ኢትዮጵያዊ የምንሆንበትን፣ የአገር ህልውናና አንድነት የሚጸናበትን፣ ከምንገኝበት እጅግ አደገኛ አጣብቂኝ የምንወጣበትን የአዲስ ዓመት ገጸ በረከት ‹‹ዛሬም እንደትናንት››ን በዚህ በዕርግና ዕድሜአቸው ትተውልን ወደ አባቶቻቸው ተከማችተዋል – መምህሬና የመንፈስ አባቴ ጋሼ መሥፍን ወልደ ማርያም፡፡ 

ከዋኖቻችን አንዱና ግንባረ ቀደም የሆኑትን የኢትዮጵያን ጠበቃ በጎውን ዘመን እንዲያዩ ሁሌም እንደምመኝላቸውና ጸሎቴም እንደሆነ በአካል እቤታቸው ተገኝቼ ነግሬአቸው ነበር፡፡ የአምላክ ፈቃድ አልሆነም፡፡ ምናልባትም ሊመጣ ያለውን ከእስከዛሬም የከፋውን ጥፋት እንዳያዩ መውሰዱ ይሆን? ዛሬ አብዛኛው ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብሎ በአድርባይነት የአገራችንን ጥፋት ዝም ብሎ በሚመለከትበት ሰዓት፣ ሰው በጠፋበት ሰዓት፣ የድርሻቸውን የመክሊታቸውን ብቻ ሳይሆን አትርፈው አትረፍርፈው ለኢትዮጵያችን ትሩፋት ሠርተው፣ እምባቸውን ጭምር ገብረውላት አልፈዋል፡፡ ጋሼ መሥፍን እንዳዘኑ በዕረፍት ቢለዩንም ቀሪዎቹ ለራሳችን ለአገራችን እናልቅስ፡፡ የአባታችንን ነፍስ በመካነ ዕረፍት በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልን፡፡

ለኢትዮጵያ ዓምዷና ውዱዷ (ዋልታና ማገር) የሆኑት ጋሼ መሥፍን የነፃነትና የሰላማዊ ትግል ብሔራዊ ምልክቶቻችን መካከል ዋናውና ቀዳሚው ናቸው፡፡ ባቈዩልን ግዙፍ ሥራዎቻቸው ሁሌም ሕያው ናቸው፡፡ ሁሌም በልባችን ጽላት ተቀርፀው ታትመው ይኖራሉ፡፡ ጋሼ መሥፍንን የምንወድ ከሆነ በቃላት ሳይሆን ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይወሰኑ በአደባባይ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተማሩትን ትምህርት፣ የሰጡአቸውን ምክሮች፣ የሰነዘሩአቸውን ተግሣፆች ገንዘብ አድርገን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለመታደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋትና ቁርጠኝነት የምንነሳበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን፡፡ 

በ90 ዓመታቸው የልደት በዓላቸው ላይ እንዲህ የሚል ምኞቴን ገልጬ ነበር፣ https://www.ethioreference.com/archives/22233

‹‹ የኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የፈሪሃ እግዚአብሔር መንፈስ፣ ሕዝባዊ መምህርነትና ምሁርነት፣ ሰብአዊነት፣ ለጭቈና እና ጨቋኝ አልበገርም ባይነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ ተቈርቋሪነት፣ ለዕውቀት መጠማትና ለእውነት ማደር፣ ጠያቂ/መርማሪ አእምሮ፣ከቁም ነገር የዋለ ሕይወት፣ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ የሚመኙላት መንግሥተ ሕዝብ ÷ ዕድገትና ልማት፣ ትንሹን ትልቁን ለማንበብና ለማዳመጥ ያላቸው ትዕግሥት፣ ባጠቃላይ የመንፈስ ጥንካሬ አምላከ ኢትዮጵያ በትውልዱ ላይ እጥፍ ድርብ አድርጎ እንዲያሳድር ጸሎቴና ምኞቴ ነው፡፡  ››

የአገር ‹የኔታው› ጋሼ መሥፍን ትተውልን ያለፉት ሥራዎቻቸው ሐውልታቸው እንደሆኑ ባምንም፣ ባገዛዙ በኩል ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጁ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቂ መታሰቢያ እንድናደርግላቸው ለኢትዮጵያውያን በሙሉ (ባገር ቤት ለምንገኝም ሆነ በውጭ ላላችሁ ወገኖቼ) ታናሽ ወንድማችሁ ጥሪዬን በማክበር አስተላልፋለሁ፡፡ 

 

 

Filed in: Amharic