>
5:28 pm - Monday October 10, 1396

"ማንነታችንን ያስታወሱን ፕሮፌሰር መስፍን ነበሩ...!!!" (አሳዬ ደርቤ)

“ማንነታችንን ያስታወሱን ፕሮፌሰር መስፍን ነበሩ…!!!”

አሳዬ ደርቤ

* “… ግን ደግሞ የኔ ንግግር (‹‹አማራ የለም››) ያልተጠበቀ ውጤት አምጥቶ (እኔ ማን ነኝ የሚል የቁጭት ስሜት ፈጥሮ) ጠቀማችሁ እንጂ አልጎዳችሁም!›› ብለው ተሰናበቱኝ!
 
 የአማራ ብሔርተኛ ፕሮፌሰሩን በሕይወት ሳሉ ባያመሰግናቸው እንኳን ካለፉ በኋላ ‹‹ነፍስ ይማር›› ማለትን ሊነፍጋቸው አይገባም!
 
ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹አማራ የለም›› የሚል ንግግራቸውን ሸገር ኤፍኤም ላይ ሲደግሙት በሰማሁ ጊዜ ‹‹ሕልውናዬ በእርስዎ ውስጥ ከሌለ የእርስዎም ክብር በእኔ ውስጥ ሊኖር አይችልም›› የሚል ይዘት ያላት አንዲት አንቀጽ ለጥፌ ነበር፡፡ ያም ጽሑፌ ካስቀየማቸው ሰዎች አንዷ ሕይወት እምሻው እንደነበረች አስታውሳለሁ፡፡
.
ከዚያ በኋላ ግን ስለ ፕሮፌሰሩና ስለ መጽሐፍቶቻቸው ሳስብ ከገፈፉኝ ይልቅ የሰጡኝ በልጦ ስለታየኝ ጽሑፌን እርሳቸው ያነቡታል ብዬ ባለስብም ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ አመንኩ፡፡ በአንድ ወዳጄ አማካኝነትም ስልካቸውን አገኘሁና ደወልኩላቸው፡፡
‹‹ማን ልበል?›› አሉኝ፡፡
‹‹እኔ እንጂ እርስዎ አያውቁኝም›› አልኳቸው፡፡
‹‹ምን ፈልገህ ነው?››
‹‹የሆነ ጊዜ ላይ በተናገሩት ንግግር በስጨት ብዬ ተገቢነት በሌለው ቃል ሶሻል ሚዲያ ላይ ወቅሸዎት ነበር››
‹‹ከአማራዎች መሃከል አንዱ መሆን አለብህ››
‹‹እውነት ነው››
‹‹ታዲያ ጽሑፍህን ልታነብልኝ ፈልገህ ነው?››
‹‹ኧረ በፍጹም የኔታ! ይቅርታ ልጠይቅዎት አስቤ ነው››
‹‹ባልቀየምህም ይቅርታህን ተቀብያለሁ! ግን ደግሞ የኔ ንግግር ያልተጠበቀ ውጤት አምጥቶ ጠቀማችሁ እንጂ አልጎዳችሁም!›› ብለው ሲሰናበቱኝም ንግግራቸውን ያጣጣምኩት ምስጋናዬን እና ምኞቴን ገልጬ ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ ነበር፡፡
.
ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉትም ለአማራ ብሔርተኝነት መፈጠር ከፕሮፌሰር አስራት ትግል በላቀ መልኩ የእሳቸው አሉታዊ ቃል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰር አስራት በሕይወት ሳለ አማራነታችንን ሊያስታውሰን ቢሞክርም ትግሉ ፍሬ አፍርቶ ሕዝቡን ከጎኑ ማሰለፍ አልቻለም ነበር፡፡
በእስር ቤት ሲንገላታ ኖሮ ካለፈ በኋላም አብዛኛው ብሔር ሥርዓቱ የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም ከዜግነቱ ይልቅ ማንነቱን ሲያስቀድም አማራው ግን በማንነቱ ፈንታ ለእሱ ቅንጣት ታክል ቦታ የሌላትን አገሩን ተሸክሞ ሲንገላወድ ነው እድሜውን ያሳለፈው፡፡ ከክልሉ የወጡ ፖለቲከኞችና ሙህራንም ቢሆኑ ከሕዝቡ የተሻሉ አልነበሩም፡፡
.
ከሶሻል ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ‹‹አማራ የለም›› የምትለው የፕሮፌሰር መስፍን የቆየች ቪዲዮ መንሸራሸር ስትጀምር ግን ‹‹እኛ ታዲያ ምንድን ነን›› የሚለው በረከተ፡፡ በየጊዜው ከሚፈጸመው ጥቃት ይልቅ የፕሮፌሰሩ ቃላት ሕመም ፈጣሪ ሆና አማራነትን የምታስታውስ ሆነች፡፡
ፌስ-ቡክ ላይ የአማራ ብሔርተኝነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከምስጋናው (መለክ ሓራ) ጋር መስበክ የጀመረው መሳፍንት ባዘዘው እንደውም በአሉታዊ ንግግራቸው አወንታዊ ውጤት ያስገኙትን ፕሮፌሰር ውጭ አገር በሄዱበት ሰዓት እስከ ማንጓጠጥ ደርሶ ነበር፡፡
.
የሆነው ሆኖ ግን ለአማራ ብሔርተኝነትና ለአብን መመስረት ሌሎች አስገዳጅ ነገሮች ቢኖሩም ከዚሁ ጎን በጎን ግን የፕሮፌሰሩ ቃላት የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድርጓ እሙን ነው፡፡
ስለሆነም ‹‹አማራ የለም›› የሚል ንግግራቸውን ሰምቶ ‹‹ኧረ አለን›› ማለት የጀመረ የአማራ ብሔርተኛ ፕሮፌሰሩን በሕይወት ሳሉ ባያመሰግናቸው እንኳን ካለፉ በኋላ ‹‹ነፍስ ይማር›› ማለትን ሊነፍጋቸው አይገባም፡፡
.
በበኩሌ ግን ከዚህ በተጨማሪ የትኛውንም ሥርዓት ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ለአገራቸውና ለወገናቸው እጅግ ብዙ አበርክቶዎችን ሲያደርጉ የኖሩት ፕሮፌሰር በማለፋቸው የተሰማኝን ልባዊ ኀዘን ስገልጽ ለሥማቸው መወሳትን፣ ለሥጋቸው እረፍትን፣ ለነፍሳቸው ጽድቅን በመመኘት ነው፡፡🙏
Filed in: Amharic