>
5:13 pm - Friday April 19, 3963

ነገረ ምርጫ ቦርድ  ‹‹ብርቱ-ካህን›› ያቺን ሰአት!  . (ኢያስፔድ ተስፋዬ)

ነገረ ምርጫ ቦርድ 

‹‹ብርቱ-ካህን›› ያቺን ሰአት! 

. ኢያስፔድ ተስፋዬ

* ከምርጫ ቦርድ የለቀቁት 2 ሰዎች ከመልቀቃቸው በፊት ስለመልቀቃቸው “የተነበየው” ፎርቹን ጋዜጣ ዛሬ ደግሞ  “ቦርዱ ላይ እየደረሰ ካለው ጫና አንፃር ብርቱካንም ብትለቅ አትደነቁ” የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል…!
 
የኢሳቱ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ብርቱካን የምርጫ ቦርድ ሀላፊ ሆና የተሾመች ቀን በስልክ ቃለመጠይቅ አድርጎላት ነበር፡፡
መሳይ፡ ‹‹የለውጥ ሀይሉ ብዙ መልካም ነገሮች እያደረገ ቢሆንም አሁንም በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ነውና ከኢህአዴግ ስርአት ባህርይ ተነስተን ይሄ ነገር በስራሽ ላይ ችግር ይፈጥርብኛል የሚል ስጋት አለሽ ወይ? ››
ብርቱካን፡ ‹‹ልክ ነህ መሳይ አሁንም ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡ ነገር ግን የለውጥ ሀይሉ እንደምታየው ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየሰራ ነው፡፡ ታስረው የነበሩ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ እና በሞያቸው የተመሰከረላቸው ሰዎችን ተቋማትን እንዲመሩ ወደፊት ማምጣቱ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ናቸው…››
.
ብርቱካን ተስፋ ሰጪ ስትል የጠቀሰቻቸው ነገሮች በሙሉ አሁን አንድ በአንድ እንደ ጤዛ ተነው፤ እንደ ጉም በነው ጠፍተዋል፡፡
በአንድ ወቅት ከአንድ ሚዲያ ጋር በእንግሊዘኛ ባደረገችው ቃለመጠይቅ “Eskindir a terrorist? no, No way! Eskindir is a very humble person, shy in a way…” ስትል የተሟገተችለት እስክንድር ሳይቀር በሽብር ወንጀል ተከሶ ግዞት ወርዷል፡፡
‹‹የለውጥ ሀይሉ›› የፈታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ተለውጫለሁ ብሎ ቃል ገብቶ፣ ምሎ ተገዝቶ ከውጭ ሀገር ያስመጣቸውን ሳይቀር ሰብስቦ አስሯል፡፡
በሞያቸው የተመሰከረላቸው ሹመኞችም ‹‹የካሮት ወ ዱላው›› ቀማሾች ከሆኑ ውሎ አድሯል፡፡ ወላፈኑ ብርቱካን ጋር ስለመድረሱ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ ለኦነግ ሰርተፍኬት በመስጠቱ የጌቶች ግልምጫ ደርሶበት እንደነበር በብዙ ተወርቷል፡፡
.
ምርጫ ቦርድ መች ሳተ? 
ስህተት 1 
ኢህአዴግ ተቀፍቅፎ ብልጥግና ሲፈለፈል! 
.
የቀድሞ ኢህአዴግ የአሁኑ ብልጥግና የሆነ ወዳጄ የኢህአዴግን የመፍረስ ሂደት ህግን እና የምርጫ አዋጁን የተከተለ አልነበረም የሚል ሙግት ስገጥመው የመለሰልኝን ነገር አልረሳውም፡፡
 ‹‹ሁሉን ነገር አሟልተናል የምርጫ አዋጁን 67 ‹ረ› ን ብቻ ነው የጣስነው፡፡›› ፡)
.
ይህቺ ‹ረ› ይህቺ ባቄላ አድራ ዛሬ የማትቆረጠምበት- ጥርስ የምትሰብርበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ ዛሬ ምርጫ ቦርዱ እና የቦርዱ አመራሮች ላይ ለሚደርሰው ጫና ሁሉ ይህቺ አጋጣሚ በር ከፋች ነበረች፡፡
.
ስህተት 2 
ሲዳማን ስቃይ ባልበዛበት ምጥ ማዋለድ ይቻል ነበር! 
.
የደቡብ ክልል ምክርቤት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ በ 1 አመት ውስጥ ህዝበውሳኔው ሊከናወን ሲገባው ጌቶች የደም ግብር ሳናይ አሻፈረኝን ስለመረጡ በወቅቱ ማከናወን ሳይቻል ቀረና፤ በወቅቱ አለመከናወኑ ብቻ ሳይሆን ለመዘግየቱ በቂ ምክንያት እና ማብራሪያ ማቅረብ ሳይቻል በመቅረቱ በ 11/11/11 ያ ሁሉ ጥፋት ደረሰ፡፡
ዛሬማ ምርጫ ቦርድ ህዝበውሳኔ እስኪያደርግ ታገሱ ማለት ቀርቶ በክላስተር የመሸንሸኑን የስራ ድርሻ አንቀፅ ‹ረ› ረግጦ የተቋቋመው ድርጅት ጠቅልሎ ወስዶታል፡፡
.
ከዚህ በኋላ ብዙ ስህተቶች ተሰርተዋል…. ስህተት መዘርዘሩን ገታ ላድረገው እና አሁንስ? ከዚህ በኋላስ? ብዬ ልጠይቅ
.
አሁንም ብርቱካን (ብርቱ-ካህን) የሚደርስባትን ጫና ተቋቁማ የመፅናት አቅም አላት ብዬ አምናለሁ፡፡ ባላታሰበ ሰአት ፅናቷን ደግማ ደጋግማ አስመስክራለችና!
 ግን ፀንታስ? ከፅናት እና ከብዙ ዋጋ መክፈል በኋላስ?
.
ተቃዋሚ እና ተፎካካሪ ሁሉ ከመንገድ ገለል በተደረገበት ሁኔታ ብልጥግናን ከራሱ ከብልጥግና ጋር ልታወዳድር ነው ወይ?!
.
ከምርጫ ቦርድ የለቀቁት 2 ሰዎች ከመልቀቃቸው በፊት ስለመልቀቃቸው “የተነበየው” ፎርቹን ጋዜጣ ዛሬ ደግሞ
“ቦርዱ ላይ እየደረሰ ካለው ጫና አንፃር ብርቱካንም ብትለቅ አትደነቁ” የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል።
እንደ መውጫ 
በቀለ ፣ ጃዋር፣ ሀምዛና ሸምሰዲን
“ከዛሬ ጀምሮ መንግስት ስሌለ ከእስር ተፈተን ከሚመሰረተው ባለአደራ መንግስት ጋር አብረን እንስራ?!?”
የሚል ደብዳቤ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አስገብተዋል
Filed in: Amharic