>

"የፍቅር ተምሳሌት፣ የሙዚቃዋ ንግስት፣ ፍቅርን የተራበችው እመቤት - ጂጂ....!!!" (ጉልላት ገለታው)

የፍቅር ተምሳሌት፣ የሙዚቃዋ ንግስት፣ ፍቅርን የተራበችው እመቤት – ጂጂ….!!!”

 
ጉልላት ገለታው

የጂጂ የእንቁነቷ ማስጥር  ምስጠቷ ነው:-
 ዓለምን በመግለብለብ አታያትም፨ይልቅስ ምስጥ ብላ አይታ፣ እርግት ብላ አሰላስላ፣እልም ብላ ጠልቃ ገብታ ዓለም በሆዷ የቋጠረችውን ጥልቅ ሚስጥር  ትቀዳለች፤ በልዩነት ለእኛ ታቀብላለች  ።
 የእኔ ቢጤው ደግሞ የጅጅን ግጥሞች ሚስጥር የሚረዳው ቀስ እያለ ነው።ጅጅ ተመስጣ የፃፈችውን ተግለብልቦ መረዳት አይቻልም ፣ከምስጠቷ ፣ከጥልቀቷ ካልተጋሩ በቀር!
*  *  *
የፍቅር ተምሳሌት የሙዚቃ ንግስት:-
 እጅጋየሁ ሽባባው ጂጂ ሁሌም ስለ አድዋ ስናስብ ጦር ሜዳ ከተፋለሙ ጀግኖቻችን ባሻገር  የዚች ድንቅ ከያኒ “ትናገር አድዋ” ሙዚቃ በትውስታችን መምጣቱ ፤
ስለ አባይ ስናሰላስል “የማያረጅ ውበት የማይልቅ ቁንጅና” ብላ ያዜመችው ዜማ በህሊናችን መስረጉ ፤
አዲስ አመት ሲመጣ “እቴ አደይ አበባ” ብለን ማዜማችን፤  እንዲህ ውጥንቅጣችን ወጥቶ ስንራወጥ “እስከመቼ…” ስትለን እህህ ማለታችን
አስከትላም “እኔን የራበኝ ፍቅር ነው” ብላ እኛንም ፍቅር ርቦናል እኮ እንድንል ማድረጓ አይቀሬ ነው።
ጂጂ ለኢትዮጵያ ያላት ፍቅር:-
ጂጂዬ እኮ ኢትዮጵያ የሚል ስም ጠርታ አይደለም ሳትጠራ እንኳ  የቢጫ ወርቅ ምድሯን ፣ የኤደን ገነት ምንጭ መፍለቂያዋን፣ የአባታችን ኢትኤልና የእናታችንን እንቆጳ ግዮን መኖሪያዋን  በሁሉም ዜማዎቿ ያስቃኘችን ባለ ቅኔ ድንቅ ከያኒ ናት። ስለ እሷ ምን ልል እችላለሁ? ጂጂዬን የትኛው መወድስ ሊያወድሳት፤ የትኛውስ የአድናቅት ልክ እሷን ሊገልፃት ፤ እኔስ በየትኛው የቃላት ስደራ ችሎታዬ ላሞግሳት፤ እንዲሁ ሙዚቃዎቿን እያዳመጥኩ የእኔ ልበ ሙሉ ሴት ፣ የእኔ የሙዚቃ ንግስት ብቻ ልበላት እንጂ።
ጂጂ እኮ ምን ያህል እንደምንወዳት አታውቅም!!!
አንድ ቀን ልክ እንደ ሌላ ቀን እህቷ ደወለችላት። አነሳችው። “ጂጂ ሰው ባንቺ ፍቅር አብዷል” አለቻት። ጂጂ እየሳቀች መለሰች…”ለመሆኑ ግን ጂጂ የምትባል ዘፋኝ እንዳለች ያውቃሉ?” hell yeah ሁሉም ለሷ ፍቅር መስጠት የጀመረው በጣሞ ዘግይቶ ነው። ጎድተናትም ይሆናል።
ጂጂ ጀማሪ ሁና አታውቅም:-
አዲስ ድምፃዊ ሁና በሀገሪቱ ትላልቅ በሚባሉ የዜማና የግጥም ደራሲዎች በርካታ ሙዚቃዎችን እንድትሰራ ተጋብዛ ነበረ። እንደ ጀማሪ ሙዚቀኛ አልተስገበገበችም። ግራም አልተጋባችም።
ያመጡትን አዳመጠችላቸው። ቆም ብላም አሰበች። እናም እንዲህ አለቻቸው “እነዚህ ዘፈኖች በጣም አሪፍ ዘፈኖች ናቸው። ደስ ይላሉ። ነገር ግን የኔ ቀለም አይደሉም” ። እውነት ነው ። ይችን ልጅ አማተር ብሎ ከመጥራት የባሰ ምንም ነውር የለም።ያደረገችው ነገር እንዲሆን ያቺ ሰው የግድ ጂጂ መሆን ነበረባት።
የጀማሪዎች ችግር ቀለማቸውን አለማወቅ ነው።
ጂጂ ንቃን አታውቅም:-
የጥበብ ሰዎች ለኛ ያላቸውን ክብር የምለካው በሚሰሩት ስራ ነው። ጂጂ በፍፁም ልቧ ታከብረናለች ለማለት ሥራዎቿን ማዬት በቂ ነው። አዎ ከአንድ ኢትዮጲያ እስከ ጉራማይሌ፤ ከአድዋ እስከ
አባይ፤ ከናፈቀኝ እስከ ጉዴ ፈላ፤ ከባለዋሽንቱ እስከ ካህኔ ድረስ ንቃን አታውቅም። እሷም ስትናገር “ሙዚቃ ለህዝብ የምሰጠው ውዱ ስጦታዬ ነው። ለምትወጂው ህዝብ ደግሞ የማትወጂውን ነገር አትሰጭውም” ትላለች ጂጂ። በእያንዳንዱ የሙዚቃዋ
ሰከንዶች እያከበረችን ነው የሰራችው።
ጂጂ ምን ያክል ጥሩ እንደሆነች አታውቅም:-
የሷን ድምፅ፡ ሮፍናን ሰብስቦ እንደሚሰራቸው የድምፅ ቅንብሮች እግዜር፣ አላህ፣ ጦሳ፣ ዋቃ ተሰብስበው እንደቀመሙት አታውቅም። ጭራሽ ደምህን ስታፈላው “እኔ የምሰራውን ቅላፄኮቀላል ነው። የትኛዋም ድምፃዊ ልትሰራው ትችላለች” ትልሀለች
ጂጂ ጥበብን በድላ አታውቅም:-
ከልቧ ስለምትሰራ ጥበብ አኩርፋት አታውቅም። ተወነች ተሸለመች። ዘፈነች ተሸለመች። እሷን ተዋናይ “እንበልሽ ዘፋኝ?” ብለህ ስትጠይቃት ደግሞ “ሰዓሊ ነኝ” ብላ ትንግርት ትሆንብሀለች የጥበብ መንደር ውስጥ ገብተህ እሷ ያልደቀሰችበት ቦታ
አታገኝም። ራሷን ለጥበብ አድምታ ነው የኖረችው። ጥበብን አቀማጠለቻት እንጂ አልሸቀለችባትም። እና እንዳልኳችሁ ነው… ምናልባት ጥበብ ጂጂን በድላ ይሆናል እንጂ ጂጂ ጥበብን በድላ አታውቅም።
ከሁሉም በላይ ግን..
ጂጂ መንደሬ ሁና አታውቅም:-
እሷ አድዋን ስታቀነቅነው ለምን ይመሰልሀል አጥንትህን የሚቀጠቅጥ…ቅስምህን የሚሰብር ስሜት የሚሰማህ? ምክንያቱም ዘፈኑን የምትጀምረው “የሰው ልጅ ክቡር…ሰው መሆን ክቡር” ብላ ነው። በዚያ ስልት ስታንጎራጉረው ላንተ ሲል የረገፈው የሬሳ መዓት ከፊትህ ተከምሮ ይታይሀል። አደራ አለብኝ ትላለህ።
አየህ እሷ የሰበከችህ ከኢትዮጲያዊነትም የዘለለ ነገር ነው። እሷ የነገረችህ ስለ አርበኞቻችን ብቻ ሳይሆን ሰውነት እና ነፃነት ስላላቸው ዘላለማዊ ግመዳም ጭምር
ጂጂ ለኔ ዘፋኝ አይደለችም ዘፋኞች ናት:-
 የሀገሬ ልጅ አይደለችም።ሀገሬ ናት።ልደትሽን እስከዛሬ የማከብረው ጥቅምት 11 ነበር። ቤተሰቦችሽ በ13 ነው አሉ። ጂጂዬ አንቺ እኮ ቅኔ ነሽ። ዛሬም ነገም ያለሽ። በየቀኑ የምትወለጂ። እንኳንም ተወለድሽልኝ…እንኳንም ተወለድሽልን!ዜማዬ- ቅኔዬ- ጂጂ ሁሌም እወድሻለሁ
ጂጂዬ መልካም ልደት ንግስቷ!!!
 እንኳን ተወለድሽ ሁለመና ቆንጆዋ እመቤት 😘
Filed in: Amharic