>

የጃነሆይ (ጃል) ሜዳን ከእምነትና ከስፖርት መናገሻነት ወደ ጎመን ተራነት !! (ደረጄ ከበደ)

የጃነሆይ (ጃል) ሜዳን ከእምነትና ከስፖርት መናገሻነት ወደ ጎመን ተራነት !!

ደረጄ ከበደ

በኦርቶዶክሶች ላይ እየደረሰ ያለው መገፋት፣ ካቶሊኮችንም ጴንጤቆስጤዎችንም፣ እስላሞችንና ሌሎች የእምነት ዘርፎችንም ሊያስቆጣቸው ይገባል። ነግ በኔ የሚል አዋቂ ነው።  የእነ ዶ/ር አቢይ ቡድኖች እንደደረጉት የአምልኮ ነፃነትን ለጴንጤቆስጤውና ለሌሎች ያለገደብ ሰጥተው (ለእሬቻም ሳይቀር)፣ ኦርቶዶክስንና አማኞቹዋን ማሳደድ ደግሞ ወንጀል፣ፀያፍና ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው…!
—-
እሬቻ ከደብረዘይት ሆራ ወደ መስቀል አደባባይ በልዩ ክብርና በልዩ ባንዲራ ታጅቦ አዲስ አበባ ሲገባ፣ በኦርቶዶክሶች በታላቅ ድምቀት ለብዙ ዘመናት ሲከበሩ የቆዩት የጥምቀትና የመስቀል በአላት ደግሞ(መስቀል በደብረዘይት፣በሞጆና በናዝሬት ውጭ እንዳይወጣ በኦሮሞ ፖሊስ መታገዱ ታውቆአል፣ ጥምቀትም ሜዳው ተወስዶበታልና እንደተለመደው ውጭ ላይወጣ ይችላል) እየተገፈተሩ አደባባይ ላይ መከበራቸው ቀርቶ በየቤተክርስትያኑ ግቢ ተወስነው፣ በተለመደው ታላቅ ክብርና ሞገሳቸው ሳይደምቁ፣ ህዝብ ሳያያቸው, ፀሃይ ሳይሞቃቸው ታፍነው እንዲያልፉ በተረኞቹ በኦሮሙማ አራማጆች ተፈርዶባቸዋል።
በየአመቱ ጥምቀተ ባህር ሲደምቅበት የቆየውና የልዩ ልዩ ስፖርት መካሄጃ ሆኖ የነበረው ታላቁ የጃነሆይ ሜዳ (ጃል ሜዳ) ለግማትና ለክርፋት ተዳርጎ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች የበሽታ መራቢያ ሆኖአል። ካልጠፋ ተንኮል ሜዳውን ለማበሻቀጥ አስተዳደሩ የተጠቀመው ሴራ፣ አትክልት ተራን ከነበረበት ከጊዮርጊስ ፒያሳ ጀርባ አምጥቶ ጃል ሜዳ ላይ ከዝንቡና ግማቱ ጋር መዘርገፍ ነበር። ለመሰሪነት ይህን አስተዳደር ማን አክሎት??? ታሪክንና እሴትን ለማጥፋት የዶ/ር አቢይን ጭፍራ ማ ተገዳድሮት???
በአረንጉዋዴ ሳር ውበቱን ጠብቆ ለአዲስ አበባ ህዝብና ለኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የጃነሆይ ሜዳ በአትክልት ነጋዴዎችና ገበያተኞች  ኮቴ ተረጋግጦ፣ ሳሩም ረግፎ ለላቆጠ ጭቃ ተጋልጦአል። እንግዲህ ስፖርተኞች በጃል ሜዳ እርማቸውን ያውጡ። እንግዲህ ጥምቀተ ባህር የሚዋደቅለት ጀግና የለውምና እስከወዲያኛው ጃነሆይ ሜዳን አይረግጠውም፣ አያየውም። የእኔም የልጅነት ትዝታዬ አብሮ ተቀብሮአል ማለት ነው። በጃል ሜዳ ላይ ተተክሎ ለብዙ አመታት የቆየው መስቀልም በአቢይ አስተዳደር በኦሮምያ ፖሊሶች ትእዛዝ ከጃል ሜዳ ሲነቀል የተቀረፀ ቪዲዮ አይቼ ልቤ በጣም አዝኖ ነበር። ፖሊሶቹ መስቀሉን ሲነቅሉ መስቀሉ ላይ ተጠምጥመው በታልቅ ጩሀት ያነቡትን የኦርቶዶክስ ወገኖቻችን ከአእምሮዬና ከልቤ ማውጣት አይቻለኝም።
በአንድ ፕሮግራም ላይ ጠ/ሚኒስትሩ የጃል ሜዳውን መጨመላለቅና የመስቀሉን በፖሊሶች መነቀል እንዳልሰሙ  በተለመደው የክህደትና የሃሰት ምላሳቸው ሲናገሩ ሰማሁ። በራሳቸው ትእዛዝ አስፈርሰው፣ አስደምስሰው አላየሁም ነበር አልሰማሁም ነበር የሚሉ የ21 ኛው ክፍለ ዘመን ገራሚ ጠ/ሚኒስትር እሳቸው ናቸው። አንዳንዴ የሚቀልዱም ይመስለኛል። አንድ መሪ የህዝብን መፈናቀል፣ የታላላቅ ታሪካዊ ስፍራዎችንና እሴቶችን መደርመስ፣ የጃንሆይ ሜዳን አዲሱ የአትክልት ተራ መሆን፣ እኛ ከሃገር ውጭ ያለነው ዜጎች ስንሰማ፣ እዛው አዲስ አበባ ተቀምጦ መስማት ካልቻለ፣ ለስራው ብቁ ያልሆነ ጊዜውን አለባሌ ጉዳዮች ላይ የሚያውል መሪ ነው ማለት ነው።
እንግዲህ ይህ ለምን ሆነ የሚለውን  ጥያቄ ስንጠይቅ ነው የሰውን ተንኮለኛ ልብና ድብቅ አጀንዳ ማየት የምንችለው።
የአቢይ እስተዳደር አትክልት ተራን ወደ ጃነሆይ ሜዳ የወሰደበት ምክንያት ሌላ ስፍራ አጥቶ አልነበረም። ሴራውና የገማው ጥንስስ ተልእኮው፣ ኦርቶዶክስንና ተከታዮቹዋን ማዳከምና የአምልኮ ነፃነታቸውን መግፈፍ ነበር። ባቀኑዋት ሃገራቸው አባላቱ በአሎቻቸውን የሚያከብሩበትን ስፍራ በማጥበብ ቀስ በቀስ ከጨዋታ ውጭ ሊያደርጉዋቸው ታስቦ ነው። ቀስ እያለም አዳዲስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናትን ለመገንባት ቦታ ማግኘት ዳገት የመውጣትን ያህል እንዲከብድ፣ ሆን ተብሎም በቢሮክራሲ ጥልፍልፎሽ ውስጥ እንዲወድቅ ይሰራበታል። ዛሬም እየታየ ነው። ምንም እንኩዋን የአማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ የመስበር ጥንስስ ይዞ የመጣው ወያኔ ቢሆንም፣ ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ነው የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናት ለቃጠሎ፣ አባሎቹዋም ለጄኖሳይድ የተዳረጉት። አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የመጡበትን መርሳት
ለምንድነው በሆነው ነገር ያዘንኩት?? እኔ ፕሮቴስታንት ነኝ ለምን ስለኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናትና አማኞች ነፃነት እቆጫለሁ??
ጉዳዩ የአምልኮን ነፃነትና የሰው ልጅ መብትን የተመለከተ ነው። ደርግ ፕርቴስታንቶችን ሲያስረን፣ ሲያንገላታን፣ ፀሎት ቤቶቻችንን ሲዘጋ የነበረበት ዘመን እንደ ትላንት ትዝ ይለኛል። በወቅቱ የዘመርን የሰበክን ቤተክርስትያን የሄድን በጠመንጃ ሰደፍ ተወገርን። ብዙዎች ለብዙ አመታት ታሰሩ ስለእምነታቸው ዋጋ ከፈሉ። ደርግ የአምልኮ ነፃነትን ለወደደው ሰጥቶ ለሌሎች ደግሞ የከለከለበት ዘመን ነበር። በደርግ ጊዜ ኦርቶዶክሶች እንዲያመልኩ ፈቃድ ነበራቸው። ፕሮቴስታንታቶች ግን የስቃይ ዘመን አሳለፍን።
ዛሬ !  ጊዜ ነገራትን ገለባበጠና፣ ጥቂት ፕሮቴስታንቶች እርካብና መንበሩን ያዙና፣ የሌሎችን የአምልኮ ነፃነት ሲነፍጉና፣ ቤተክርስትያናት ሲቃጠሉ ዝም ብለው ሲያዩ፣ በውስጤ ትልቅ ነውጥ ፈጥሮብኛል።ከወያኔ የመጣው የኦርቶዶክስና የአማራው ጥላቻ እግዚአብሄርን እናመካለን እናውቃለን በሚሉ በጣት በሚቆጠሩ መሪዎች ተፋፍሞ መቀጠሉ የሰው ልጅን ክፋት ጥግ አሳይቶኛል።
በኦርቶዶክሶች ላይ እየደረሰ ያለው መገፋት፣ ካቶሊኮችንም ጴንጤቆስጤዎችንም፣ እስላሞችንና ሌሎች የእምነት ዘርፎችንም ሊያስቆጣቸው ይገባል። ነግ በኔ የሚል አዋቂ ነው። ደርግ እንዳደረገው፣ የአምልኮን ነፃነት ለሌሎች ሁሉ ሰጥቶ ለፕሮቴስታንቱ ብቻ እንደከለከለው አይነት ሲሆን ዴሞክራሲ የለም። የዛሬዎቹ የእነ ዶ/ር አቢይ ቡድኖች እንደደረጉት የአምልኮ ነፃነትን ለጴንጤቆስጤውና ለሌሎች ያለገደብ ሰጥተው (ለእሬቻም ሳይቀር)፣ ኦርቶዶክስንና አማኞቹዋን ማሳደድ ደግሞ ወንጀል፣ፀያፍና ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። በአስቸኩዋይ እንዲቆም ሁላችንም ልንታገለው ይገባል
የዜጎችን የመናገር፣የመፃፍ፣የማምለክ፣ የመሰብሰብ ነፃነት ለስልጣን ማቆያ ወይም ለሌላ አጀንዳ የሚከለክል መንግስት በአስቸኩዋይ ሊወገድ ይገባዋል እላለሁ !!  ተባረኩ !
Filed in: Amharic