በእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ…!!!
ባልደራስ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ/ም ከሰዓት በኃላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል፡፡ ፓርቲው ሊቀመንበራችን እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጽህ መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ስርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኑአቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል፡፡ ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በዛሬው የችሎት ውሎ ታዝበናል፣
1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት ፣
2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች፣ በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማም ከተናገሩ በኃላ፣ ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል፡፡ ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሃሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በስራ ላይ ያውላል፡፡ መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ህዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
ጥቅምት 13 ፣ 2013 ዓመተ ምህረት