ውርድ ከራስ…!?!
ያሬድ ሀይለማርያም
* ውስጡ የተናጋ እና ሰላም ያጣ አገር ሁሌም ለውጪ ደፋሪዎች የተጋለጠ ነው!!
* የውጪው ነቆራ እና ትንኮሳ ‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁም’ ነው ነገሩ። እስኪ እራሳችን ያዋረድናትን ኢትዮያን እናክብራት፣ ከፍ እናርጋት፣ ሰው አይደለም አውሬም በሰላም የሚያድርባት አገር ትሁን፣ ከልመና እንውጣ፣ ከተንኮል እና የጎጥ አስተሳሰብ እንላቀቅ፣ ኢትዬጲያን መንደር ለማድረግ ከሚሯሯጡት ካድሬዎች እንታደጋት…!!!
እኛ ያዋረድናትን አገር ሌላው በምንተዳው ነው የሚያከብራት? እኛ ተስማምተን እና ተከባብረን መኖር አቅቶን ወንድም ወንድሙን በጠራራ ጸሃይ አርዶ የሚፎክርበት አገር ፈጥረን ስናበቃ፣ ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ አገራችው አይደለም እየተባሉ የሚፈናቀሉባት ምድር አድርገናት ስናበቃ ትራንፕ በቃላት ደፈረን ብሎ እዬዬ አይገባኝም። የውጪው ነቆራ እና ትንኮሳ ‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁም’ ነው ነገሩ። እስኪ እራሳችን ያዋረድናትን ኢትዮያን እናክብራት፣ ከፍ እናርጋት፣ ሰው አይደለም አውሬም በሰላም የሚያድርባት አገር ትሁን፣ ከልመና እንውጣ፣ ከተንኮል እና የጎጥ አስተሳሰብ እንላቀቅ፣ ኢትዬጲያን መንደር ለማድረግ ከሚሯሯጡት ካድሬዎች እንታደጋት።
እኛ ተከባብረን እንደ አንድ አገር ሕዝብ ብሔራዊ ራዕይ ኖሮን አብረን መቆም ከቻልን ሌላው እዳ ገብስ ነው። ኤርትራን ከሸኝን ከሦስት አሥርት አመታት በኋላ ትግራይን ደግሞ ለመቀነስ መቀሌና አዲስ አበባ ከትመው የሚፎካከሩ ሰንካላ ፖለቲከኞችን የተሸከመች አገር የትራንፕ ሽሙጥና ስድብ ምን ያደርጋታል?
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የውጪ ጥቃት ሲሰነዘር ወይም የተሰነዘረ ሲመስለን ከጫፍ ጫፍ፣ ከልጅ አዋቂ ሳንል የምናሳያትን ቁጣ እና በአንድ ድምጽ የመገንፈል ስሜታችንን አፈናን፣ ጭቆናን፣ ግፍን፣ ሙስናን፣ ዘረኝነት እና ጎጠኝነትን፣ የውስጥ ፖለቲካ ንቁሪያችንን፣ በሕዝብና በአገር ሃብት ላይ የሚደርሱ ውድመቶችን እና ዝርፊያዎችን፤ እንዲሁም የፍትሕ መጓደለን እና መድልዖን ለመዋጋት አውለናት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያን ገና በጠዋቱ ፍትሕ የሰፈነባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት፣ ድህነትን አሸንፋ ለሌሎችም የምትተርፍ የበለጸገች አገር እናደርጋት ነበር። ውስጡ የተናጋ እና ሰላም ያጣ አገር ሁሌም ለውጪ ደፋሪዎች የተጋለጠ ነው።
ውስጣችንን እናጽዳ፣ ከሸርና የመጠላለፍ ፖለቲካ እንውጣ፣ ጎጠኝነትን እንጠየፍ፣ ኢትዮጵያዊያን በሰውነታቸው ተከብረው እና ተከባብረው የሚኖሩባት አገር እንፍጠር፣ የግፍ ጽዋው ይንጠፍ፣ ለእውነት እና ለፍትሕ አብረን እንቁም። ኢትዮጵያዊያን ለውጭ ጠላት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በተጣቡን ግፍ፣ መድሎ፣ ሙስና፣ አፈና፣ ድህነት እና ሌሎች ክፉ እሳቤዎቻችንም ላይ አብረን በጋራ እንነሳ። ያኔ …