>

የአሜሪካው ፕሬዚደንት አይዘንሃወር — በኢትዮጵያ ጋሻ-ጦር ! ! !  (አሳፍ ሀይሉ)

የአሜሪካው ፕሬዚደንት አይዘንሃወር — በኢትዮጵያ ጋሻ-ጦር ! ! ! 

አሳፍ ሀይሉ

ጄነራል ድዋይት ዴቪድ (‹‹ኢኬ››) አይዘንሃወር — ባለብዙ ኮከቡ የአሜሪካ ታላቅ የጦር ጀግና — 34ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት — የኢትዮጵያ ጀግኖች የሚታጠቁትን — የጀግኖቹን ጋሻና ጦር አንግበው ነው የቆሙት — በዋሺንግተን ዲሲ፡፡
ጋሻና ጦሩ ለፕሬዚደንት አይዘንሃወር የተበረከተላቸው — ከፕሬዚደንት አይዘንሃወር ጋር አብረው በቆሙት — የጃንሆይ ቀ.ኃ.ሥ. አብሮ አደግ በሆኑትና ከዲፕሎማትነት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ባሉ ከፍተኛ ማዕረጎች — ሃገራቸውን ባገለገሉት በልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ — በእኛ የ1941 ዓመተ ምህረት እንቁጣጣሽ በዓል ሰሞን ነበር፡፡
የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በድል አድራጊነት በመወጣታቸው ከፍተኛ ዝናና ክብርን የተቀዳጁት እኚህ አሜሪካዊ ጀግና — ጄነራል ድዋይት አይዘንሃወር — ይህን በፎቶው የሚታየውን የኢትዮጵያውያ ጀግኖች ጋሻና ጦር ባነገቡ — ከጃንሆይ የተላከላቸውን (በፎቶው ልዑል ራስ እምሩ ይዘውት የሚታዩትን) በትረ-ሥልጣን በተቀበሉ — ልክ በ 5 ዓመታቸው — ማለትም በ1953 እ.ኤ.አ. — የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ — ለ 8 ዓመታትም አሜሪካንን መሩ — እስከ 1961 ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ.)፡፡
አይዘንሃወር ከሥልጣንም ከለቀቁም በኋላ እንደሳቸው በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ተሰሚነት ኖሮት የሚያውቅ ሰው አልነበረም ይባልላቸዋል፡፡ በጀግንነትም ከአሜሪካ መሪዎች — ምናልባት የሊንከን የጦር ጄነራል ከነበሩት — ከጄነራል አሊሴስ ኤስ ግራንት በቀር — የሚተካከላቸው አቻ አይገኝላቸውም ይባልላቸዋል — ጄነራል ድዋይት ዴቪድ አይዘንሃወር — ‹‹ኢኬ››፡፡
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴም በበኩላቸው በውትድርናው በኩል ምርጥ ጀግና ተዋጊ ነበሩ፡፡ በሕዝብም ዘንድ እንዲሁ ተወዳጅ የነበሩ — ሌላ ቀርቶ ጃንሆይ ከሥልጣን እንዲወርዱ እርሳቸው ለሕዝቡ ባላቸው ወገንተኝነት አማላጅ የተላኩ — ከመሣፍንቱ ለየት ያለ ዲሞክራትነትን የተላበሱ — በነፃና ዘመናዊ አስተሳሰቦቻቸው የሚታወቁ — ‹‹ሰውና ዕውቀት›› በሚልና፣ በኋላም ‹‹ካየሁት ከማስታውሰው›› በሚሉ ከሞታቸው በኋላ በታተሙላቸው የግለ-ህይወት መጻሕፍታቸው ላሁኑም ትውልድ ብዙ የታሪክ እውነቶችን ከትበው በማቆየት እስካሁንም ስማቸው በመልካም የሚጠቀስላቸው — የሚያኮሩ የታፈሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
እና… በቃ… ይህን አይዘንሃወር… መለሎ የሃበሻ ጀግና መስለው… የኢትዮጵያውያንን ጋሻና ጦር እንዲህ በማዕረግ ተሸልመው ሣይ… አቤት ልቤ በደስታ እንዴት እንደረሰረሰ….!!!!!!!!!! ያስተፌሰን!!!!
ትልቅ ታሪክ ያለን ሥልጡን ሕዝቦች ነን፡፡ ዓለም ሁሉ የመሠከረልን ጀግኖች ሕዝቦች ነን፡፡ ሐይማኖተኞች፣ ቅኖችና እንግዳ ተቀባዮች፣ — ፈሪሃ-እግዜርን የምናውቅ፣ ተቆንጥጠን ተመዝልገን በሥርዓት ያደግን — በራሳችን ቋንቋ፣ በራሳችን አልባሳት፣ በራሳችን ቁስ፣ በራሳችን ባህል፣ በራሳችን እምነት ተኮትኩተን፣ ተሸልመን ያደግን — ኩሩ፣ ባለይሉኝታ፣ ጨዋ ሃበሾች፣ ጨዋ ሕዝቦች ነን፡፡ ይህን እኛነታችንን ስናከብር ሌላው ያከብረናል፡፡ ይህን እኛነታችንን ስንጠብቅ ሁሌም ታላቅ ነን፡፡
ታላቅ ነበርን፤ ዳግምም ታላቅ እንሆናለን፡፡ 
ፈጣሪ አምላክ የብዙሃን እናት ኢትዮጵያን በቸርነቱ ይባርክልን፡፡ 
አበቃሁ፡፡ 
መልካም ጊዜ፡፡
____________________________
የልዑል ራስ እምሩ እና የጄነራል ድዋይት አይዘንሃወር ፎቶ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
“Abebe Shiferaw. Abebe Shiferaw saved to History. Ras Imru and President Eisenhower, Washington D.C. September, 1948”.
Filed in: Amharic