የንፁሃን ደም ጩኸት በጉራ ፈርዳ
አልይ እንድሬ – ደሴ
ጉራ ፈርዳ በደቡብ ክልል በቤንች ማጅ (ሸኮ) ዞን የሚገኝ ወረዳ ነው፡፡ የወረዳው ከተማ ቢፍቱ ሲሆን ከሚዛን ተፈሪ 43 ኪ.ሜ ያህል ይርቃል፡፡ በ2008 ዓም የተጠና ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ወረዳው በ27 ቀበሌ የተዋቀረ ሲሆን ከ45 እስከ 50 ሺህ ህዝብ ይኖርበታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ወረዳውን በደቡብ የሸኮ ወረዳ፣ በሰሜን የቤንች ወረዳ፣ በምስራቅ ከጋምቤላ ክልል እና በተወሰነ ደረጃ ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ ሲዳማ፣ ትግሬ፣ኦሮሞ፣ አማራና ሌሎችም በብዛት እንደሚኖሩበት ይታወቃል (ሙሉቀን፣2008) ፡፡
ሰሞኑን በጉራ ፈርዳ ወረዳ በሰላማዊ የአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመ ሁለት ተከታታይ ጅምላ ጭፍጨፋ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል፡፡ የመጀመሪያው ጥቅምት 8/2013 ዓም 2ኛው ደግሞ ጥቅምት 11/2013 ዓም የተፈፀመ ጥቃት ሲሆን በሁለቱም ጥቃት በጠቅላላው 26 ሙስሊሞችና 5 ክርስቲያኖች በአጠቃላይ 31 ሰዎች በግፍ መገደላቸው በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የተገለፀ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ በአንድ መቃብር ውስጥ አራት አስከሬን እየተደረጉ መቀበራቸውም ተነግሯል፡፡
የደቡብ ብሄርብሄረሰቦችና ህዝቦች ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ጥቅምት 12/2013 ዓም በፌስቡክ ገፁ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን የሰጡትን መግለጫ ወቢ በማድረግ እንዳሰፈረው በወረዳው ጥቅምት 8 እና ጥቅምት 11/2013 ዓም በሁለት ቀበሌዎች በተፈፀመ ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና አንድ ሽህ አራት መቶ ሰማኒያ (1480) አባዎራዎች ተፈናቅለው በቢፍቱ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ መሆኑን በመግለፅ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ 16 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስፍሯል፡፡ በቀጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንድ የፖሊስ አባልና አራት አመራሮች እንደሚገኙበት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ተገልጧል፡፡
የጥቃቱ መነሻ መንስኤ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊም ይሁን ሃይማኖታዊ፤ደማቸው በከንቱ የፈሰሰው ዜጎች ዘራቸውና ሀይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ይህ ጅምላ ጭፍጨፋ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰው ልጆች ላይ ሊፈፀም የማይገባው አሳፋሪ ተግባር መሆኑ ሊካድ አይችልም፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡
በቤንች ማጅ (ሸኮ) ዞን የአማራ ተወላጆች በጅምላ መፈናቀል መገደልና ንብረታቸውን መዘረፍ የጀመሩት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ከ1986 እሰከ 2004 ትንሽ ጋፕ ብሎ ከቆየ በኋላ እንደገና በ2005 እና በ2007 ዓ.ም ተባብሶ የከፋ የግድያና የመፈናቀል ጥቃት ደርሶባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በ2005 የተፈናቀሉ አማሮች ቁጥር ከ20000 ሽህ እንደሚበልጥ ተመዝግቧል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ2007 ዓ.ም ደግሞ አስቀድሞ በታቀደ ግድያ 600 ያክል ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን ከመፈናቀል ጋር በተያያዘ ደግሞ በወቅቱ በጉራ ፈርዳ ወረዳ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሰረት እንኳን ከ3364 በላይ ህፃናት፣ እናቶችና ነፍሰ ጡር ሴቶች በ2007 ዓ.ም ብቻ በጅምላ መፈናቀላቸውንና ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 860 ህፃናት ጎዳና ላይ መበተናቸውን አስታውቋል፡፡
ይህ ተከታታይ ጥቃት የሚያሳየው በዞኑ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ምንም ዓይነት ህጋዊ ከለላ እንደማይደረግላቸው ነው፡፡ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ነገርም የለም፡፡ ገጀራ እንኳን እንዲይዙ አይፈቀድላቸውም፡፡ በመዠንገር፣ሜንኢትና ሸኮ ህዝቦች ዘንድ ገጀራ መያዝ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን አማሮች ገጀራ ይዘው ከተገኙ ይቀማሉ፡፡ ገጀራቸውን የተቀሙት አማሮች 100 ብር ከፍለው እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ የአማሮችን ንብረት እየቀሙና ብር እየተቀበሉ መስጠት እንደ ገቢ ምንጭ ቆጥረው የሚኖሩ የአካባቢ ባለስልጣናት በብዛት በህወሃት የአገዛዝ ዘመን እንደነበሩ የጥፋት ዘመን በተሰኘ መፅሃፍ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
በህውሃት ዘመን የሆነው ሆኖ አልፏል፡፡ ዛሬ ለውጥ አልመጣም እንዴ? ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ፀሃፊዎች በጉራፈርዳ ሰሞኑን ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ ሲፅፉ ‘’ዛሬም በጉራ ፈርዳ…’’ የሚል ርዕስ ሰጥተውት ተመልክቻለሁ፡፡ ትክክል ነው፡፡ መቼ ነው በጉራ ፈርዳ የንፁሃን ደም መፍሰስ የሚያቆመው? የህውሃት አመራሮች ‘’ዛሬም በየቀበሌውና በየወረዳው ስልጣን ላይ እንደተሰገሰጉ ናቸው እንዴ? ዛሬም የህውሃትን ጉዳይ እያስፈፀሙ ነው እንዴ? ከላይ እንደገለፅኩት በሰሞኑ የጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አንድ የፖሊስ አባልና አራት አመራሮች እንደሚገኙበት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ መግለጫ አመላክቷል፡፡ ይህ አስተዳደር ታዲያ ከህውሃት ዘመን በምን ተሻለ? ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና መንግስት በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል፡፡