ቀፎ ሰቅሎ ንብ አደን…!!!
በድሉ ዋቅጅራ
ኤታማጆር ሹሙ በአንድ የኮማንዶ ሰልጣኞች ምርቃት ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹ከ20 በላይ ጥቃት ሞክረዋል፤ ሰሞኑንም በጉራ ፈርዳ ጥቃት አድርሰዋል፤ እስከዛሬ አልተሳካላቸውም፤ ወደፊትም አይሳካላቸውም›› ብለዋል፡፡ ለመግደል ቃት ስቦ የገደለ እንዴት ነው አልተሳካለትም የሚባለው? በዚህ ሁለት አመት ውስጥ ስንት ህይወት ነው የጠፋው? አይሳካም ያሉት ለውጡን መቀልበስ ከሆነ፣ የለውጡ ስኬት የምን ያህል ዜጎች ህይወት ነው የሚፈልገው?
የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት በአዲስ ከተተካና ለውጡ በይፋ ከተጀመረ ቢያንስ ሁለት አመት፡፡ የሽግግር ጊዜ በርካታ ተጠባቂና ድንገት መጣሽ ችግሮች የተሞላ ነው፤ ግን አጭር ነው፡፡ በእኛ ሀገር፣ በዚህ የለውጥ ጊዜ መፈናቀልና ስደት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የተጀመሩ ግንባታዎች መስተጓጎል፣ . . . ተጠባቂ ከነበሩ ችግሮች መካከል ነበሩ፡፡ በእነዚህን ችግሮች ለውጡ አዎንታዊ እርምጃ አሳይቷል፡፡
ይሁን እንጂ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ያልተጠበቀው ብሄርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋና ግድያን መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ የለውጡ መልክና አርማ እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ የለውጡና የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ችግር፣ ይህ ብሄር ተኮር ግድያ ነው፡፡ ዛሬ ኤታማጆር ሹሙ በአንድ የኮማንዶ ሰልጣኞች ምርቃት ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹ከ20 በላይ ጥቃት ሞክረዋል፤ ሰሞኑንም በጉራ ፈርዳ ጥቃት አድርሰዋል፤ እስከዛሬ አልተሳካላቸውም፤ ወደፊትም አይሳካላቸውም›› (ጥቅሱ ቃል በቃል አይደለም) ብለዋል፡፡ ለመግደል ተኩሶ የገደለ እንዴት ነው አልተሳካለትም የሚባለው? በዚህ ሁለት አመት ውስጥ ስንት ህይወት ነው የጠፋው? አይሳካም ያሉት ለውጡን መቀልበስ ከሆነ፣ የለውጡ ስኬት የምን ያህል ዜጎች ህይወት ነው የሚፈልገው?
.
በተለይ አሁን አሁን የሚደረጉት ግድያዎች በተለያየ አካባቢም ቢሆን፣ በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠሩና ሆን ተብሎ የእርስ በርስ ግጭትን ለመጫር የሚደረጉ መሆናቸውን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በመሆኑም ይህ ችግር የሚወገደው፣ ከዚህ ድርጊት ጀርባ ያሉት ሀይሎችን በመቆጣጠር ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው፣ ችግሩ በተፈጸመበት ቦታ ያሉ ሀላፊዎችንና ድርጊቱን የፈጸሙትን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ አግባብ ቢሆንም፣ ችግሩ እንዳይቀጥል ዋስትና አይሆንም፡፡ እነዚህ ሰዎች ንቦች ናቸው፤ ቀፎውን ከተሰቀለበት እስካላወረድን ድረስ ሌሎች ንቦች ይመጣሉ፡፡ በረቱ ውስጥ ቀፎ ያስቀመጠ በረቱ በተተራመሰ ቁጥር ንብ ቢያድን በረቱ ሰላም አይሆንም፤ ከብቱ ሰላም እንዲሆን ቀፎውን ከበረቱ ማውጣት አለበት፡፡