>

ለማ ጉያ :-ኢትዮጵያዊው የአርት አምባሳደር (ታምሩ ገዳ)

ለማ ጉያ :-ኢትዮጵያዊው የአርት አምባሳደር

ታምሩ ገዳ


የቀለም አባት ሎሬት ሠዓሊ ሻምበል (የክብር ዶ/ር) ለማ ጉያ፣ ለአገር እና ለሕዝብ ብዙ ሠርተዋል፤ ለፍተዋል፣ ደክመዋል – «ይህቺ ናት አገሬ፤ ይህቺ ናት ኢትዮጵያ» እያሉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለአለም  ህዝብ አስተዋውቀዋል።

-ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ከአባቱ ከአቶ ጉያ ገመዳ እና  ከእናቱ ከወ/ሮ ማሬ ጎበና በ1921 በቢሾፍቱ ደሎ ቀበሌ ተወለደ፡፡  ገና በልጅነቱ በቤተሰቡ ግድግዳ ላይ በአፈር እና በአመድ  የተለወሰ ስእል በምስል በቤተሰቡ በጎረቤት እና በጓደኞቹ ዘንድ አድናቆት ለማግኘት ችሏል።

– ለማ ጉያ ከሰለጠነበት የአየር ሃይል ሙያ በተጓዳኝ ለዚህ ሙያና ስራ መግባት በር የከፈተለትን የስነ-ጥበብ ሙያ ሳይዘነጋው በአስመራ የኢጣሊያኖች የስዕል ት/ቤት ከደሞዙ እየቈረጠ በክፍያ በመማር የሙያ ማዳበር ስራውን ጀመረ፡፡ በተለይም በፖርትሬት በመልክአምድር በቁሳቁስ (Still- Life) ስራዎች በመጠቀም በመማር በተፈጥሮ የታደለውን እውቀት ሊያዳብር ችሏል፡፡

አርቲስት ለማ ጉያ   ቢሾፍቱ ውስጥ በቀደዳማዊ ኃይለስላሴ  በተሰጠው መሬት ላይ የሰራውን ጋለሪን በማሻሻል በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አርት ጋለሪ ባለቤት ሲሆን የጋለሪውን መታሰቢያ በኒልስን ማንዴላ ሃውልት በማጀብ አራት የጋለሪ ቤቶችን በመገንባት ለህዝብ ምንግዜም ክፍት ሆነው ስራዎቹን ወጣቱ ትውልድ  ሰለ ባህሉ  በቀላሉ እንዲማርበት መንገድ ጠርጓል፡፡

– በህይወት ዘመኑ ወደ 1ዐ ሺህ የሚጠጉ የስዕል ውጤቶችን ለሃገሩ ያበረከተው አርቲስት ለማ ጉያ በመሠረተው ጋለሪ ግቢ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመክፈትም የዜግነት ግዴታውን ተወጥቷል፡፡

– አርቲስት ለማ ጉያ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ኘሬዝዳንት ጀኮብ ዙማ በተደረገለት ጥሪ ለሦስት ጊዜ በ ገዢው ፓርቲ (ኤኢንሲ) አመታዊ ስብሰባ ተሳትፏል፡፡

–  ስራዎችን ከኢትዮጵያ ውጪ  በአሜሪካ ፣በስዊዲን፣በኬኒያ፣በእንግሊዝ በናይጄሪያ ወዘተ አሳይቷል ሦስት ትውልድ የተናገሩ የጥበብ ሥራዎችን የሰራ በሚል በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማህበር ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ በተለያዩ ጊዚያትም ሽልማቶችን አግኝቷል።

– በአፍሪካ ህብረት ህብረቱን ያገለገሉ ፀሐፊዎችን በኦሮሚያ የባህል ማዕከል በአዲሱ ህንፃ የኦሮሚያ ኘሬዝዳንቶችንና የኦሮሞ ባህልና ትውፊትን የሚያሳዩ የቆዳ ላይ ስዕሎችን አያበረከተ ይገኛል፡፡

–  የዛሬ 86 ዓመት ቤተሰቦቹ አውሮኘላን ለማየት መደብ ላይ ተነጥፋ ተኝቶበት የነበረው ሌጦ ዛሬ የአርቲስቱ የጥበብ አሻራ መገለጫ ሆኖ የወቅቱን የእጣ ፈንታው መወለድ ሽታ ሆኖ ቀርቶ ነበር፡፡ አርቲስቱ በማህበራዊ ኑሮውም ሆነ በስራው አሁንም ደከመኝ ሰለቸኝ አይልም፡፡አሁንም ፖሌቱንና ቡርሹን ይዞ  ይሰሩ ነበር።

ለማ ጉያ   በናዝሬት/አዳማ መምህራን ኮሌጅ  ቢገቡም መለዮ ለባሽ  በመሆን አገራቸውን ለማገልገል ከነበራቸው ብርቱ  ፍላጎት የተነሳ በአየር ሃይል ውስጥ  ተምረው በከፍተኛ ነጥብ ተመርቀዋል፡፡ በአስመራ ከተማም በአየር ሃይል መምህርነት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ጉዟቸው የአርት ፍቅራቸው አልተለያቸውም ነበር።የአየር ኃይል ነገር ከተነሳ የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉበት አየር ኃይላችን  ለማሰብ እና ጡረተኛ አባላቱን ለመርዳት አዲስ አበባ ሻራተን  ሆቴል በተደረገ ገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም ላይ የአርት ስራቸውን ለጨረታ በማቅረብ ወደ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ተሸጦ ገቢ አድርገዋል።

– በሀገራችን ታሪክ በስዕሉ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነችው ሥዕል ያለስተማሪ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል፡፡

– አርቲስት ለማ ጉያ ‘አፍሪካ አርት ጋለሪ’ አቋቁመዋል፡፡ የጋለሪውን መታሰቢያ በኒልስን ማንዴላ ሃውልት በማጀብ አራት የጋለሪ ቤቶችን በመገንባት ለህዝብ ምንግዜም ክፍት ሆነው ሥራዎቻቸውን ወጣቱ ትውልድ እንዲማርበት አድርገዋል፡፡

– በቆዳ ስራ ላይ የሚቀርጹት የፖርትሬት ምስል ታዋቂነትን አትርፎላቸዋል፡፡ በተለይ በፍየል ቆዳ ላይ ሙሉ በሙሉ ፀጉሩ ሳይነሳ ተፈጥሮአዊ ወዙንና መልኩን ይዞ የፊትን ገፅ ብቻ በቀለም በመስራት የበርካቶችን አድንቆት አትርፈዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 5 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. በወሰነው መሠረት ለአርቲስት ለማ ጉያ ገመዲ የክብር ዶክትሬት በስነ-ጥበብ እንዲሰጥ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

ከቀለም አባት ጋር ብዙ ጊዜ በቃለ መጠይቅ ተገናኝተናል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አይረሴ ጨዋታን አውግተናል። በቢሾፍቱ ከቤተሰቦቻው ጋር በመሆን «የአፍሪካ ሙዚየም» በሚል ባሰሩት የጥበብ ማዕከል ሥራዎቻቸውን በተደጋጋሚ በክብር አስጎብኝተውኛል።

– አርቲስት ለማ ጉያ አምስት ልጆችን ወልደዋል።

ሦስት ሴቶች ልጆቻቸውና ሁለት ወንድ ልጆቻቸው አራቱ የስነ-ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

• ትዕግስት ለማ ጉያ – [ክብርት ሰክረተሪ]

• ነጻነት ለማ ጉያ – [ሠዓሊ እና የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያ]

• ደረጀ ለማ ጉያ – [ሠዓሊና ሲኒማቶግራፈር እና የፕሮዳክሽን ባለሙያ]

• ሠላማዊት ለማ ጉያ – [ሠዓሊ፣ መምህርት እና የሙዚቃ ባለሙያ – በአሜሪካ]

• ዳዊት ለማ ጉያ – [ሠዓሊ] ናቸው።

ወንድማቸው ቱሉ ጉያ እንዲሁ  ሰአሊ እና በአዲስ አበባው የአርት ትምህርት ቤት ውስጥ በሙያቸው ወጣት ኢትዮጵያኖችን በማፍራት ይታወቃሉ።

ሎሬት ሠዓሊ ሻምበል የክብር ዶ/ር ለማ ጉያ ቢሾፍቱ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ክሊኒክ  በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ዛሬ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

“የሸክላ ገበያ” እና የደንከል ልጃገረድ” በተባሉ ሥራዎቻቸው አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ ከ10ሺህ በላይ የቆዳ ላይ ድንቅ ሥራ ባለቤት ነበሩ። በወጣትነት ዘመናቸውም «ሥዕልን ያለአስተማሪ» የተሰኘ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳትመዋል።

ሰዓሊ ለማ ጉያ ሐሙስ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓም በቢሸፍቱ ስታዲየም የክብር ሽኝት ይደረግላቸዋል፤ ከዚያም በምሥራቅ ሸዋ አደአ ሊበን ወረዳ ዳሎ ቀበሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል።

Filed in: Amharic