>
5:28 pm - Monday October 10, 1864

"ተው!" ሲል ሺ የሚንጫጫለት.. ብቸኛው ኢትዮጵያዊ...!!! ታታ አፍሮ (ነፃ ብዕር)

ተው!” ሲል ሺ የሚንጫጫለት.. ብቸኛው ኢትዮጵያዊ…!!!

ታታ አፍሮ (ነፃ ብዕር)
* መታደል እኮ ነው ጎበዝ! አትግደል ብሎ ሲጽፍ ገዳይ ካህን እንዳየ አጋንንት እንዲህ ሲጮኽ ማየት! ኧረ ምኑን ሞገስ ቢሰጠው ነው..? እንደው ምኑን ግርማ ቢያለብሰው ነው..? ተው ሲል ሺ የሚንጫጫለት..?
*    *    *
ከማንም ቀድሞ “…አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ…” ያለው ነብይ:-
•መንግስት እንደአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚቆጥረው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ !
•ሀገሩ ላይ ሰርቶ ለመብላት ከመንግስት ፈቃድ የሚጠይቅ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ !
•ሀገር ውስጥ ባይኖርም የጎዳና ተዳዳሪ ገጭቶ የሚታሰር ብቸኛው ኢትዮጵያዊ !
•“አበበ በሶ በላ” ብሎ ቢዘፍን የስፖርት ተንታኞች አበበ ግደይን ለመተቸት ነው ብለው ዘፈኑን የሚተነትኑለት ብቸኛ ኢትዮጵያዊ !
•በአማርኛ ቋንቋ የዘፈነውን ዘፈን ኬንያ ለማስመረቅ የሚገደድ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ !
•ሀይለማርያም ስልጣን ሳይለቅ ፣ አብይ አህመድ ሳይታወቅ ፣ ጌታቸው አሰፋ ሳይደበቅ ፣ ህወሃት ሳይገረሰስ ፣ ዘረኝነት እንዲህ ሳይነግስ ፣ ጃ war እንደልቡ ሳይደነፋ ፣ አክቲቪስቶች እንደ አሸን በሀገሪቱ ሳይፈሉ ፣ ታጥቀው የሸሹ ታጋዮች ትጥቅ አንፈታም ሳይሉ ፣ ቄሮዎች ሳይፀነሱ ፋኖ ዘርማና ኤጀቶ ለትግል ሳይነሳሱ እንደካህን ፍቅርን ሰብኮ “ፍቅር ያሸንፋል” ያለ ለትውልዱ ጭቆናን በአንደበቱ የታገለ. . .ይህ ሰው ነበር!!!
 
መታደል እኮ ነው ጎበዝ! አትግደል ብሎ ሲጽፍ ገዳይ ካህን እንዳየ አጋንንት እንዲህ ሲጮኽ ማየት! ኧረ ምኑን ሞገስ ቢሰጠው ነው..? እንደው ምኑን ግርማ ቢያለብሰው ነው..? ተው ሲል ሺ የሚንጫጫለት..?
*   *    *

አናኛቱ! – እኔን ይብላኝ!

ከብሄርተኛ ጋር ፈጽሞ መግባባት አይቻልም። ብሄርተኞች ድምጻቸውን ከቆርቆሮ በላይ አስጩኸው  የራሳቸውን ድምጽ ብቻ እያዳመጡ ሌላውን የሚያደነቁሩ ድኩመ ሀሳብ ናቸው።
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ዛሬ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት ከልክ ማለፉን በመግለጽ መንግስት ዋና ተግባሩ የሆነውን ህዝብን የመጠበቅ ተግባሩን እንዲወጣ አሳስቧል።
ይህን በየወቅቱ ጊዜና ሁኔታዎች ሲጠይቁት እየወጣ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን የሚያሳየውን እንቁ ድምጻዊ እንደምንም ብለው የብሄር ጥግ ለማስያዝ “ኦሮሞ ሲገደል ዝም ብሎ….” የሚል ልጥፍ ይዘውለት ተነስተዋል።
እንዳልኳችሁ ብሄርተኛ ከራሱ ውጪ ለመስማትና ለመረዳት የሌላውን ለመቀበል የማይችል አንካሳ በመሆኑ እንጂ ቴዲ አፍሮ በስቃዩ ዘመን፣ ፖለቲከኛው እንኳ ለመናገር በሚሳቀቅበት ወቅት ኦሮሞ የደረሰበትን ግፍና መከራ እያመሰጠረ በመከራ ድምጽ፣ ልቅሶ በቀላቀለ ሲቃ “አ ና ኛ ቱ ” (እኔን ይብላኝ) ሲል አቀንቅኗል።
ምን ዋጋ አለው ያኔም ቢሆን እናኛቱ ሲሰማ ቴዲ ላይ በመሳለቅ ለህዝብ ተቆርቋሪነቱን ጭቃ ለመቀባት ያልተባለ ያልተነገረ ነገር አልነበረም። ዛሬ ተመልሰው ሲወቅሱት “ያኔ ምን ብለን ነበር?” ብለው ለማስታወስ እንኳ ብሄርተኝነቱ አቅላቸውን አስቷቸዋልና አልቻሉም። የኦሮሞ ህዝብ ግን እውነቱን አሳምሮ ያውቃል። – አናኛቱ ! እኔን ይብላኝ!
*     *    *

ብላቴናውን የምንወደው በምክኒያት ነው

 
ለማንኛውም አስታዋሽ ያሻቸዋልና ከስድብ ውጪ እንዲያው እንደ ቆርቆሮ ከመጮኽ ባለፈ ለወገናቸው ቅንጣት ታክል ውለታን ላልዋሉ ግለሰቦች /ቆርቆሮዎች/ ይኼንን ፅሑፍ ጀባ ለማለት ወደድኩ..!
ቴዲ አፍሮ ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸውን ተግባሮች ፈፅሞም ያልፈፀመ ያህል የሚሰማው ሩሩህ ሰው ነው። የቴዲ አፍሮ ገንዘቦች በተለያዩ ቦታ ተበልተው የሚቀሩ ሲሆኑ ከኮንሰርት ስራ አንስቶ እስከ ሲዲ አከፋፋዮች ድረስ በአግባቡ ገንዘቡን ከፍለውት አያውቁም። ይኼም ሆኖ ቴዲ አፍሮ ለገንዘብ ብሎ ፍርድ ቤት መቆምን የማይወድ ሰው ነው። ሌላው የቴዲ አፍሮ አስደናቂ ነገር በአጋጣሚዎች የተቸገሩ ሰዎችን ሲያገኝ ከ10 ሺ እስከ 100 ሺ ብር በቼክና በጥሬ ተቆጣሪ ገንዘቦችን ሸጎጥ አድርጎ የመሄድ ብዙ ልምድ አለው። ብዙ ብዙ ያልተሰሙ ለመፃፍም አመቺ ያልሆነ ቸርነቶችን አድርጓል። እስኪ ከብዙ በጢቂቱ እንመልከታቸው…
✔ ሐምሌ 30,1998 ዓ.ም በድሬዳዋ ደርሶ
በነበረው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ30 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።
✔ ጥቅምት 1,2002 Elshaday Relief and Development ባዘጋጀውና ከ50 ሺህ በላይ ህዝብ በተገኘበት የአዲስ አበባ ስታዲየም ኮንሰርት ከ 1 ሚሊየን ብር በላይ
አሰባስቦ ሙሉ ገቢውን ለእርዳታ ድርጅቱ ገቢ ያደረገ ሲሆን በእለቱ ለአበበች ጎበና ሕፃናት ማሳደጊያ 100 ሺህ ብር እና ለታላቁ ደራሲ ለይልማ ገ/አብ የወርቅ ብዕር ሸልሟል።
✔ጥቅምት 23,2002 በህመም ላይ ትገኝ ለነበረችው ማንአልሞሽ ዲቦ መታከሚያ ይሆን ዘንድ 20 ሺህ ብር አበርክቷል።
✔ ጥቅምት 17,2004 የወጣት አስመሮም ኃይለ ሥላሴን ነፍስ ለማዳን ለሶማሊያ ሽማግሌዎች 700 ሺህ ብር ከፈሎ የወገኑን ህይወት አተረፈ። ይህ ወጣት 700 ሺ ብሩን ካልከፈለ ስቅላት ተፈርዶበት ነበር። ቴዲም መረጃውን በመፅሄት ላይ ነበር አንብቦ ፈጥኖ የደረሰለት። እጅግ አስደናቂው ነገር ደግሞ እጁ ላይ የነበረው ገንዘብ እጅግ ጥቂት ከመሆኑ የተነሳ ከጓደኞቹ ተበዳድሮ ነው ብሩን ያሟላው።
✔ጥቅምት 17,2004 ለኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበር የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎ ለማህበሩ ያለውን አጋርነት አሳየ። ማህበሩም የምስጋና ምስክር ወረቀት
ሰጥቶታል።
✔የአራት ኪሎ ወጣቶች ከአልባሌ ሥፍራ ይርቁ ዘንድ በአባቱ ስም ተቋቁሞ ለነበረው የእግር ኳስ ቡድን ለአራት አመታት በየአመቱ ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
✔በራሱ አነሳሽነት ለአበበ መለሰ ኮንሰርት በማዘጋጀት የአርቲስቱን ህይወት ከህልፈት ታደገ።
✔ጥቅምት 2005 ቀድሞ ይማርበት ለነበረው ቤቲልሄም ት/ቤት የኮምፒውተር እና የሙዚቃ መሣሪያ ድጋፍ አደረገ።
✔በተለያየ ግዜያት በተዘጋጁ ዝግጅቶች ላይ እንደዚሁም እዛው ድረስ በመሄድ ለወ/ሮ አበበች ጎበና ህፃናት ማሳደጊያ ከመቶ ሺ ብር በላይ የገንዘብ እርዳታ በተደጋጋሚ አበርክቷል።
✔ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ባስመረቀችው አረንጋዴ መሬት ዶክመንተሪ ፊልም ምርቃት ላይ በእንጨት ለቀማ ይተዳደሩ ለነበሩ እናት የ 20ሺብር ቼክ ሰጧቸዋል።
✔እንደዚሁም ለተለያዩ ድምፃዊያን ግጥም እና ዜማ በነፃ አድሏል።
✔መስከረም 10,2011 ዓ.ም ከቡራዩ የተፈናቀሉ ወገኖችን ሄዶ በመጎብኘት የ1 ሚሊዮን ብርም ድጋፍ አድርጓል።
✔ከሶስት አመታት በፊት ሊቢያ ላይ በአሸባሪው isis ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወገኖቻችንን ቤተሰቦች ከባለቤቱጋ ለቅሶ በመድረስ የብርም ድጋፍ አድርጓል።
✔በሰለሞን ቦጋለ እና በሳምሶን /ቤቢ/ ለሚመራው “ህብረት ለበጎ ለአንድነት” ለተሰኘው የመረዳጃ ማህበር ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ አበርክቷል።
✔በአዲስ አበባ በተለይም የኳስ ሜዳ ልጆችን እና የሌላ አከባቢ ስራ አጥ ወጣቶችን አሰባስቦ በማደራጀት ስራ የሚጀምሩበትን ግማሽ ሚሊየን ብር አብርክቶላቸዋል።
✔አርቲስት ጌዲዮን ዳንኤልን እና የደጃች ባልቻ ቤተሰቦችንም በገንዘብ እረድቷል።
✔በጥር ወር 2010 ዓ.ም ባህር ዳር ላይ ኮንሰርቱን ለማቅረብ ባቀና ጊዜ ገዳማቶችን ሲጎበኝ ለገዳሙ ገንዘብ አበርክቷል። እንዲሁም በዚሁ አመት ከባለቤቱ ጋ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በማቅናት 100 ሺ ብር ሰቷል።
✔በ2010 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ በዕለተ ትንሳኤ /ፋሲካ/ በዳግማዊ አጤ ምኒልክ ሆስፒታል ታመው የተኙ ወገኖችን ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ በመሄድ የገንዘብ እርዳታ አድርጓል። ሁለቱ ህፃናት ሳይቀሩ ብር እና ፍራፍሬዎችን ለታማሚዎቹ በማበርከት በዚህ የመልካም ምግባር ላይ ተሳትፈዋል።
✔ቴዲ አፍሮ ለአድናቂዎቹም ቢሆን የኮንሰርት መግቢያ ትኬቶችን በገንዘቡ ገዝቶ /ከ200/ በላይ የሚያበረከት ነው። ይኼም አሁን በዋለው ገበያ ከ100 ሺ ብር የማያንስ ነው።
✔️የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ 1.2 ሚሊዮን ብር በድጋፍ ለዘመቻው ለተቋቋመው ኮሚቴ አስረክቧል።
✔️ የካቲት 14 በመስቀል አደባባይ ከታሪካዊው ግዙፍ ኮንሰርት ከተገኘው ገቢ አዲስ አበባ መስተዳድር ለሚያደርገው በጎ ተግባር እንዲውል ሙሉ የኮንሰርት ገቢውን ድጋፍ አድርጓል።
✔️ ከቡራዩ ለተፈናቀሉ የጋሞ ህዝቦች የተጠለሉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
እነኚህ በመጠኑ ያስታወስኳቸው ሲሆኑ ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት ቴዲ አፍሮ ብዙ ያልተሰሙ ግለሰቦች ብቻ የሚያውቋቸው እርዳታዎችን ያደርጋል። ለዛሬ በዚኽ እንቋጨው እና ሌሎች ቴዲ አፍሮ በህይወቱ የዋላቸውን መልካም ምግባሮች ለመዳስስ እንሞክራለን። ቴዲ አፍሮን የምንወደው በምክኒያት ነው። ይኼንን ሁሉ ሲያደርግ ብሔር አይቶ አልነበረም። ሰብዓዊነት አስገድዶት እንጂ! አሁንም ነገም ለህዝብ ድምፁን ያሰማል ያለውን ይሰጣል..!
Filed in: Amharic