>

ምን ሆነን ነው? የሆነ ያስነኩን ነገርማ አለ! (አሰፋ ሀይሉ)

ምን ሆነን ነው? የሆነ ያስነኩን ነገርማ አለ!

አሰፋ ሀይሉ

ሁልህም በየወገንህ፣ በየጎሳህ፣ በየነገድህ ግባ ሲባል – እንግዲህ ካልቀረልን ብለን የተጠለልንበት የነገድ ምሽግም በራሱ – ራሱን በቻለ አስተዛዛቢና አስደንጋጭ እውነቶች የተሞላ ሆኖብናል፡፡ በዘመኑ ፖለቲካ መነፅር ከታየ – በእውነቱ ያለንበት ሁኔታ – በሎሬት ጸጋዬ ስንኞች ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ‹‹እሸሸግበት ጥግ አጣሁ›› ያሉትን የፋሺስት ኢጣልያን አገዛዝ ዳግም እየኖርነው እንደሆነ አስታዋሽ ነው፡፡ የፋሺስቱ ቀለም ተለዋወጠ እንጂ በገዛ ምድራችን ያንኑ አያቶቻችን የተፋለሙትን የግዞት ኑሮ እየደገምነው ሳንሆንማ አንቀርም፡፡
አሁን አሁን ‹‹አከርካሪውን ሰብረነዋል! ረምርመነዋል! ረጋግጠነዋል! አኮላሽተነዋል! …›› ሲሉን የኖሩት የሥርዓቱ አጋፋሪዎች እውነታቸውን ሳይሆን ይቀራል ወይ? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ‹‹እሳት በሌለበት ጭስ አይጭስም›› እንደሚባለው – ያለ ምክንያትማ ፉከራው አልመጣም፡፡ እያልኩ አስባለሁ፡፡ ትኩስ ትንፋሼ ሽቅብ እየተትጎለጎለ በንዴት መነፅሬን እያዳመነ፡፡
የአማራ ህዝብ በታሪኩ እንዳለፉት 30 ዓመታት አድርባይነት መለያው ሆኖ አያውቅም፡፡ የአማራ ህዝብ እንዳለፉት 30 ዓመታት በፍርሃት ተሸብቦ አያውቅም፡፡ የአማራ ህዝብ በዘመናት ታሪኩ እንዳለፉት 30 ዓመታት ደሙን ሲያፈስ ለኖረ ፋሺስታዊ ሥርዓት በጅምላ እያሸበሸበ ተጎናብሶ በውርደት መኖር የመረጠበት ዘመን የለም፡፡
አትንኩኝ ባይነትና ተኳሸነት የዘመናት ባህሉ የሆነው የአማራው ሀዝብ አሁን ከከብት ጋር ሲላፉ ዕድሜያቸውን በሚጨርሱ እንኩቶዎች እጅ ዋጋውን እያገኘ፣ ደሙ እየተንዠቀዠቀ፣ አጥንቱ እየተከሰከሰ – እንዲያም ሆኖ – ባለቤቷን እንዳየች ውሻ ለሥርዓቱ ጭራውን እየቆላ በሚያደገድግ መስሎ-አዳሪ ፓርቲ ተወክያለሁ ብሎ መብቱንም ነፃነቱንም ሁሉነገሩንም አሳልፎ ሰጥቶ በሰላም ተኝቶ ማደር እንዴት መረጠ? የሆነ ነገርማ አስነክተውናል!
ገፍቶ ከመጣበት አጥቂ – ሀሞትን አኮሳትሮ – ልብን አጀግኖ መዋጋት – ለህልውና ደረትን ሰጥቶ መቆም – የአማራን ህዝብ ያስፈራበት ዘመን እንዳሁኑ ዘመን በየትኛውም ዘመን የለም፡፡ ለአማራ ሕዝብ ጦርነት ጀግና የሚለይበት፣ ወንድነት የሚመሰከርበት፣ በደሙ ውስጥ የተዋሃደ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል ነው፡፡ ‹‹የአጥቂነት ጠላት ነን!›› እንዲል የኮርያ ዘማቾች ኒሻን፡፡ የአማራው ህዝብ የአጥቂም የአጥቂነትም የጥቃትም ጠላት ነበር፡፡
ዛሬስ? ዛሬ የአማራው ህዝብ በታሪካቸው ‹‹ጦርነት›› የሚለውን ቃል ሰምተው በማያውቁ፣ ጀግና በዞረበት ዞረው በማያውቁ ግሪሳዎች ከእግር እስከ ራሱ እየተቀጠቀጠና እየታረደ – እንደ ባሪያ እየተሰደበና እየተንቋሸሸ – ሰብዓዊ ክብሩ ተዋርዶ – የአካል ደህንነቱና የመኖር መብቱ ተነፍጎ – በገዛ ሀገሩ ሶስተኛ ዜጋ ሆኖ የሚኖረውን ኑሮ – አሜን ብሎ ተቀብሎት ለዚህ ወደ ባርነት ላወረደው ሥርዓት እጅ እየነሳ – ከሰውነት በታች በሆነ በተናቀ ህይወት መኖሩን ትልቅ ጥበብ አድርጎ ኑሮውን እየገፋ ነው የሚመስለው፡፡
የዛሬው የአማራ ህዝብ – የሌት ተቀን ውርደት የማይሰለቸው – አስገራሚ ህዝብ ሆኗል፡፡ የዛሬው የአማራ ህዝብ መረገጥና መገፋት የማያስከፋው ህዝብ ሆኗል፡፡ የዛሬው የአማራ ህዝብ መታረድና መተልተል የማያንገበግበው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አንዳንዴ ይሄን ይሄን ሁሉ እየተንገበገብኩ ሳስበው በአንድ ወቅት ከራሳቸው ከጤና ባለሙያዎቹ አንደበት የሰማሁት ‹‹አማራን የማምከን›› የሥርዓቱ ፕሮጀክት ደጋግሞ ፊቴ ድቅን ይልብኛል፡፡ ፋሺስታዊው የዘረኝነት ሥርዓት – ባለፉት 30 ዓመታት ቆይታው – የሆነ ነገርማ የአማራን ህዝብ ቢረጭበት ነው እንጂ!!??
ይሄ ፋሺስታዊ የዘረኞች ሥርዓት የሆነማ የአማራውን ህዝብ ያስነካው ነገር አለ፡፡ የሆነ በምኑም በምኑም አድርጎ የነሰነሰበት፣ የበተነበት፣ ያጎረሰው፣ ያጠጣው፣ በኪኒን ያዋጠው፣ ወይ በመርፌውም፣ በክትባቱም፣ በምኑም አድርጎ የጠቀጠቀው የሆነማ አፍዝ አደንግዝ ነገር አለ፡፡ እንጂ – በእውኑ – የአማራ ህዝብ – እንዴት እንዲህ ማንም እየተነሳ እንደ ከብት የሚያርደውና እንደ ዝንብ ‹‹እሽ!›› እያለ የሚያበርረው – የማንም ሙታን ፈቃጅና ከልካይ መዘባበቻ ሆኖ ይቀራል? የሆነ ነገርማ ሆኗል! የሆነ ነገርማ ሆነናል! እነ ‹‹አከርካሪውን ሰብረነዋል›› የሆነ የሰበሩብን ዕቃማ ቢኖር ነው! እንጂ – በጤና እንዲህ በቁማችን አደንግዘው አቀርዝዘው አላስቀሩንም!
አበስኩ ገበርኩ! አንዳች ነገር መጥቶ ከዚህስ ግዞት፣ ከዚህስ የቁም ሞት ይቀስቅሰን፡፡ ይገላግለን፡፡ ጨርሶ ይማረን፡፡ እና እንደ ሙሉ ሰው በክብር እንነሳ፡፡ ሰብዓዊ መብቶች እንዳሉት ሙሉ የሰው ልጅ ተነስተን ለህልውናችን ለመቆም ያብቃን! የዘጋብንን አፍዝ አደንግዝ ይግለጥልን! እነ አጅሬ የሰለቡብንን ቆራጡን ማንነታችንን – እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን – በአንዳች ተዓምሩ ፈጣሪ አምላክ ይግለጥልን!
እንጂ ሌላ ምን ይባላል? 
እያለን የለንም እኮ!!
Photo: Zhukov – the military history of the Abyssinian emporium.
Filed in: Amharic