>

የማንጨርሰውን አልጀመርንም...!!! (ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ)

የማንጨርሰውን አልጀመርንም…!!!

ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ

1) በፖለቲካ ትግል ውስጥ በተለይም በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የዴሞክራሲ ጭምብል ያጠለቁ ውስጣቸው በጭቆና የተደመደመ አካላትን እውነተኛ ማንነት በገሀድ እንዲወጣ ማድረግ እጅግ አድካሚ ተልእኮ ነው። «ሕዝብን እስከማምለክ የደረሰ ፍቅር አለን፤ አገርንም የመሞሸሪያ ጫጉላው የእኛው ልዩ ነው» የሚሉ አካላትን ለሕዝብ ኃቁን አውቆ እንዳይዘናጋ ማስረዳትን ያከለ ከባድ ሥራም የለም። ይኼን ሁሉ የጨቋኞች  አስመሳይነት ግን ልባሞች በምድር፤ እግዜሩም  በሰማይ፤ «ይበቃል» ሲሉ፥ ሁሉም ይነቃል። በዚህ ሰሞን የሆነውም ይኸው ነው። አሁን ሁሉም ሰው እንዴት ጭቆናን አስወግደን ዴሞክራሲን እንተካለን በሚለው ላይ ብቻ ነው፤ ውይይቱ። ጨቋኞቹን እርቃን አስቀርቷቸዋል።  ከባዱ ቀላል ሆኗል!
2) ቀጣዩ ምእራፍ ሁሉንአቀፍ ውይይት ይሆናል። ይህ ውይይት የዴሞክራሲ ኃይሎች የሚሳተፉበት፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት የሚይዙት፣ የሚመሩት፣ የሚፈፅሙትና የሚከታተሉት ሆኖ ለእያንዳንዱም ተጠባቂ ሚናውን የሚለይ ነው። ውይይቱ በሚወልዳቸው ተሻጋሪ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መሰረት ምጥ ላይ ካለቺው እናት አገራችን ፍትኅን፣ እኩልነትንና ነፃነትን እናዋልዳለን። የጭቆና የሽርት ውኃ የሚወለደውን ነፃነት እንዳያፍን፤ የጭቆና የደም አበላም እናት ኢትዮጵያችንን በምጥ እንዳያስቀራት፤ የጭቆና ልምድ አዋላጆች የሚወለደውን ፍትኅ ቀብረው የተለመደ እንግዴያቸውን እንዳያስታቅፉን፤…የዴሞክራሲ ኃይሎች ብርቱ ጥንቃቄ፣ የበዛ ትእግስትና ጥበብን መላበስ ይኖርብናል። እኛ ስንተባበር ፈጣሪም ይረዳናል። እኛ ለእውነት ስንቆም ጨቋኞች በራሳቸው ውሸት ይፈራርሳሉ።
3) ስንደማመጥ፣ ስንከባበርና ስንተማመን ከባዱ ቀላል ይሆናል፤ እየሆነም ነው!
4) ውቅያኖስ በሚያክል ጥረት ውስጥ የየድርሻችን አንዲት ጠብታ ካዋጣን የዴሞክራሲ ተክል ሲለመልም የጭቆና ትል  ይጫጫል።
የማንጨርሰውን ብቻ ሳይሆን አሸንፈን በድል የማንሞሸርበትን ትግል አልጀመርንም!
Filed in: Amharic