“ለአማራ ህዝብ ትንሽ ነገር እየሰራሁ ከሆነ እስርም ሆነ ሰማዕትነት ተፈልጎ ማይገኝ ክብር ነው!”
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
የበለፀጉት ብአዴናዊያን ከሰልፉ ቀን ዋዜማ ጀምረው እኔን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶችን ለማሰር የእስር ማዘዣ አውጥተው እየፈለጉኝ እንደነበር ወዲያውኑ
ማዘዣ እንዳወጡ ከ3 አስተማማኝ መረጀዎች ደርሶኝ ነበር።
እኔም ከየቦታው እየተደወለ የሚነገረኝንና ጤናና ደስታየን የነሳኝን በየቦታው የሚፈፀመውን ተከታታይ የአማራ ጭፍጨፋና ዘር ማጥፋት በሰልፉ ላይ ተገኝቼ ሳላወግዝ፣ ብሶታቸውን ሳላስተጋባና ድምጽ ሳልሆናቸው እንዳልታሰር ብየ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጌ አመሸሁ። ምሽቱንም በየአካባቢው ካሉ ወጣቶች ጋር የሰልፉን ደህንነትና የሚተላለፉ መልዕክቶችን እየተመካከርሁ አምሽቼ ልተኛ ወደ
መኝታየ ስሄድ ድርጅታችን አብን ሰልፉን ከመምራት አልችልም ወደ ሰልፉ መሰረዙንና አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በሰልፉ መሳተፍም ሆነ ማስተባበር አትችሉም የሚለውን ውሳኔ እኩለ ሌሊት ላይ ማውጣቱን ሳይ በጣም አዘንሁ።
የድርጅቴን ውሳኔ ባከብርም በግሌ ሰልፉ መደረግ እንዳለበት ይሰማኝ ስለነበር ግራ ተጋባሁ ። (ንቅናቄያችን የሚመሩ ወንድሞቼን ብቃትና ውሳኔ አንድም ቀን ተጠራጥሬ አላውቅም፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ብዙ ክርክርና ፍጭት ተደርጎባቸው ባብላጫ ድምጽ ስለሚወሰን ዛሬም ለወደፊትም አከብራለሁ)።
የድርጅቴን ውሳኔና የውስጤን በሰልፉ ላይ የመገኜት ፍላጎት ለማስታረቅ ከራሴ ጋር ስሟገት ሌሊቱ ተጋመሰ። መጨረሻም የመጣው ይምጣ ብየ ሰልፉ ላይ ለመገኘት ባስብም የድርጅቴን ውሳኔ ወደ ጎን ትቼ ሰልፉ ላይ ብገኝ ሊፈጥር የሚችለውን ብዥታ፣ ፓለቲካዊ ጉዳትና እንዴት እንደሚተረጎም/ለትርጉም
ተጋላጭ እንደሚሆንና ሌሎችንም ተያያዥ ነገሮች ሳስብ ደግሞ ከመቅረት ውጭ አማራጭ እንደሌለኝ ተረዳሁና ከፍተኛ መደበት ውስጥ ገባሁ። እንቅልፍ የለም ሳላሸልብ ነጋ።
በጠዋት ባህር ዳር ሰልፍ የወጡት እነ ምስጋናው መደብደባቸውን ሳይ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሀዘን፣ ውርደትና ተያይዞ የቁጭት ስሜት ተሰማኝ።
ዛሬ ደግሞ የምስጋናው መደብደብ አልበቃው ብሎ መታሰሩን ሰማሁ። በአዴት፣ በእንጅባራ፣ በዳንግላ፣ በቆቦ (የጀግኖቹ ጢነኛ አመራሮች)፣ በመርዓዊ፣ በባህር ዳር፣ በእብናት፣ በአጣየ፣ በቡሬ፣ በአቸፈርና በምዕራብ ጎንደር ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ወጣቶች፣ የአብን አመራሮችና የከተማ ነዋሪዎች ታስረዋል።
በልፃጊዎቹ ብአዴናዊያን በእስር አማራን ማሸነፍ እንደማይችሉ ከ2 ዓመት በፊት ህዝብ ያስተማራቸውን ረስተውታል። ተመልሰው ይቅር ያላቸውን የአማራን ህዝብ በዚህ ፍጥነት ወደ መናቅ ውስጥ ይገባሉ ብየ አልጠበቅሁም ነበር።
በኔ በኩል ወዳጆቼ አታስቡ። እኔ እንኳን እስር ሞትንም ንቄ ነው ወደዚህ ትግል የገባሁት። በየቀኑ ዋስትና በሌለበትና ወጥተን ተመልስን መግባታችን
በማናውቀው ሁናቴ ነው ይህን ወደ 3 አመት የሚደርስ ጊዜ ያለነው። እንኳን እስር ሞት እንኳ ቢመጣ ለአማራ ህዝብ ትንሽ ነገር እየሰራሁ ከሆነ ሰማዕትነትና ተፈልጎ ማይገኝ ክብር ነው!