>
5:28 pm - Thursday October 10, 2250

መናኙን ፖለቲከኛ እስክንድር ነጋን ጎበኘነው...!!! (መኳንንት ፈንታሁን)

መናኙን ፖለቲከኛ እስክንድር ነጋን ጎበኘነው…!!!
✍️ መኳንንት ፈንታሁን
ዛሬ ጠዋት እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም አብን ከጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ለመሳተፍ በጠዋቱ ከአንድ ወዳጀ ጋር መስቀል አደባባይ ተገኘን።ማንም የመጣ የለም።
ብቻችንን ከስቴድየም እስከ ቃሊቲ ተሰልፈን ቃሊቲ ወህኒ ቤት ወረድን።
እስክንድር ነጋን ከነ አሸናፊነት ስነልቦናው አገኘነው።
ሁሌም አሸንፋለሁ የሚል አዕምሮ፣ ከተሰቀለበት ማማ የማይወርድ ምጡቅ ስነ ልቦና አሁንም ከእስክንድር ጋር አብረው አሉ።
ግን ምን አይነት ሰው ነው በፈጣሪ?
ልንመክርና ልናበረታታው ሄደን መክሮና አበረታትቶ መለሰን አጃኢብ ነው።
ለማንኛውም ለወዳጆቸና ለአላማ አጋሮቸ  በሙሉ ሰላምታ አቅርብልኝ ብሏል ሰላምታው ይድረሳችሁ።
በርቱ ጠንክሩ ብሏችኋል።
የታገልንለትንና ወህኒ የወረድንለትን ሕዝባዊ አደራ እንዳትረሱ ብሏችኋል።
ነገር ግን ሃገርን ከዘረፈ ክንፈ ዳኛው ጋር ወገንን ከጨረሰ አብዲ ኤሊ ጋር እንዲሁም ሃገርን በሽብር ካመሰ ጀዋር ጋር እስክንድርን ሳየው ሸከከኝ።
በእርግጥ እስኬው ንጽሕናው የስነልቦና ነፃነትን አጎናጽፎት እንደ ሌሎቹ አንገቱን አልደፋም እንደተቀሩት አይሽኮረመምም አንገቱን ቀና አድርጎ በልበሙሉነት የሚፈስ ጅረት ነው።
“የስነልቦና ብርታትህ ይደንቀኛል በመከራ የማይኮሰምን በስቃይ የማይጠወልግ ጥልቅ ነው ምስጢሩ ምን ይሆን?” ስል ጠየቅሁት አስኬውን።
እንዲህ ሲል መለሰልኝ።
“እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን ሁሌም የአሸናፊዎቹ፣ በምንም ውስጥ ሆነው ከአሸናፊነት ውጭ ሌላ ሁለተኛ መንገድ የማይታያቸው የነሱ።
አንበሳ የአራዊት ንጉሥ ነው።አንበሳ ትልቁ አራዊት አይደለም ፈጣኑም አይደለም ብልሁም አይደለም ግን ንጉሥ ነው የንግሥናው ምስጢር ግን አሸናፊ ነኝ ብሎ ማሰቡ ነው። አንበሳ ዝሆንን ሲመለከተው የሚያጠግብ የሚበላ ነገር መጣልኝ ብሎ ያስባል ትልቁ ዝሆን ግን አንበሳን ሲመለከተው የሚያጠቃኝ ነገር መጣብኝ በማለት ከፍልሚያ በፊት ይሸነፋል። አየህ አሸናፊነት አዕምሮ ውስጥ የሚፈጠር የማንአህሎኝነት ስሜት ነው።”
ሃሳቡ ግርም ብሎኝ ከባለእንጀራየ ጋ ተሰናብተነው ወጣን።
Filed in: Amharic