የህወሃት አመራር ሀገር የማተራመስ ተግባር ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይገባል!
አበጋዝ ወንድሙ
ህወሃት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ህዝብን ለ 27 ዓመት ቀጥቅጦ ለመግዛት ሁነኛ መሳሪያው በሀገሪቱ ትልቁን ቁጥር የያዙትን የአማራና የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት እርስ በርስ እንዳይተማመኑና በጥላቻ እንዲተያዩ በማድረግ እንደነበር ሁላችንም የምንገነዘበው ሀቅ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ፣ ኢህአዴግ በሚል ጭምብል በውስጡ ያቀፋቸውን ሶስት ድርጅቶች በቀጥታና በእጅ አዙር አመራሮቹን በመቆጣጠር ፣ ትናንሽ ፍርፋሬዎች የማግኘት ዕድል ቢኖራቸውም፣ከዚያ ውጪ ግን በአስተማማኝ ደረጃ የህወሃትን ፍላጎት ማሳኪያ መሳሪያዎች አድርጎ እንዳደራጃቸውም የሚታወቅ ነው። በለውጡ ማግስትም የ የድርጅቶቹ መሪዎች ወከልን ለሚሉት ህዝብ ሳይሆን ለ 27 ዓመት ‘የህወሃት ተላላኪ ‘ ሚና ሲጫወቱ እንደነበር ያመኑት ሀቅ ነው።
በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በአራቱ ድርጅቶች ያልታቀፉትን የክልል አመራሮች ደግሞ ‘ተስፈኛ ኢህአዴግ ‘ በማድረግ ‘አጋር ፓርቲዎች‘ በሚል ፈሊጥ፣ የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ እስከሆኑ ድረስ በክልሎቻቸው ያሻቸውን እንዲያደርጉ በመፍቀድና የአብዲ ኢሌ አይነት ጨቃኝ ‘መሪ‘ በማፍራት ፣ለህዝብ እሮሮ ለሀውሃት ግን ተደላድሎ የመግዛት ዘመን እንዲሆን ያስቻለ ስርዓት ተዘርግቶ ነበር ።
ለህወሃት አንድ ሰው አንድ ድምጽ የሚለው ዴሞክራሲያዊ መርህ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር አዋጭ ስላልሆነ ከጅምሩም ከቶም ሊቀበለው ያልፈለገው እንደሆነና፣ የአገዛዝ እድሜውን ለማራዘም ከላይ የተጠቀሱትን አካሄዶች መጠቀም ብቸኛ አማራጩ እንደነበርና ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ ‘የሚል ማደናገሪያውም ይሄንን እውነታ ለመሸፈን የተጠቀመበት መሳሪያም እንደነበር ማወቅም አስፈላጊ ነው ።
ድርጅቱ ከጽንሱ በሀገራዊ እሳቤ ላይ ሳይሆን የ አንድ ብሄረሰብ ‘ነጻ መውጣት‘ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑም ከዚህ ውጭ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሄን ሀቅም ለረጅም ጊዜ የፌዴራል ስልጣን ተቆናጦ አዲስ አበባ የነበረውና አሁን መቀሌ የመሸገው ጀነራል ተክለብርሃን በቅርቡ በግልጽ ለመገናኛ ብዙሃን የሰጠው አስተያየት ያረጋግጣል ።
በሀገራችን የነበረው መንግስታዊ አወቃቀርና አስተዳደር እንደዚህ ስለነበርም፣ በልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍል የተካሄደው ትግል የተሰበጣጠረ እንዲሆን ቢገደድም ፣ በሂደት የተራዘመ ሃገራዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለመሆን በቅቶ ነበር። ህወሃት ያለውን ሁሉ ሃይል ቢጠቀምም ይሄንን ህዝባዊ ትግል ለመግታት አለመቻሉንና፣ ህዝባዊ ትግሎቹም የአጋርነት አዝማሚያ ማሳየታቸውን እንደ አመላካች ነጥብ በመውሰድ ለወትሮው ‘ተላላኪ‘ የነበሩት ብአዴንና ኦህዴድ ወኔ አግኝተው በማበራቸው፣ ህወሃትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስልጣን ማማ አውርደው ድርጅቱን መቆጣጠር አስችሎአቸዋል ።
ህወሃት ይሄንን ሽንፈትና ድንገቴ ከስልጣን ማማ መውረድ ለጊዜው የተቀበለው ቢመስልም ግን ፣ ከአብይ ስልጣን መውጣት ማግስት ጀምሮ ነው ወደ ቀድሞው የበላይነት ለመመለስ አቅጣጫ ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው።
በአብይ የሚመራው ‘የለውጥ ቡድን‘ ስልጣን እንደያዘ ያገኘው ህዝባዊ ድጋፍ ያስበረገገው የህወሃት አመራር ጠቅልሎ ይዞ የነበረውን የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊነት በስነስርዓት ሳያስረክብም ጭምር ነው በተዝረከረክ መንገድ ወደ መቀሌ ያፈገፈገው።
የህወሃት አመራር ሃሳብ የነጠፈበት ስብስብ እንደመሆኑ፣ ወደ ስልጣን ዳግም ለመመለስ የነበረውና ያለው ብቸኛ አማራጭ፣ ለ 27 ዓመት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሀገሪቱን የደህንነትና የመከላከያ ተቅዋማት ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት በየክልሉ የመለመላቸውን ቅጥረኞች በማንቀሳቀስ የማያቋርጥ ብጥብጥ በመፍጠር ነው።
የአብይ መንግስት ተረጋግቶ የመግዛት አቅሙን እንደ እሳት አደጋ፣ እነዚህ የህወሃት ጥቅም ተጋሪ ስብስቦች የሚፈጥሩትን ቀውስ ለማምከን እንዲባዝንና ፣ ይሄም በህዝቡ መሃል የአብይ መንግስት አገር ለማረጋጋትና ለመምራት አቅም ይጎለዋል የሚል እምነት በማሳደር የሚመጣውን ክፍተት በመጠቀም፣ ዳግም ወደ ስልጣን የመምጣት ስልት እንደሆነ ባለፉት ሁለት አመታት በግልጽ የታየ ጉዳይ ነው።
የአብይ መንግስት ከህዝብ ባገኘው ጊዜያዊ ድጋፍ በመስከርም ይሁን ውስጡ የተሰገሰጉ አፍቃሬ ህወሃትነት ያልተላቀቃቸው ‘ተላላኪዎችን‘ ማጥራት ባለመቻሉ ፣ ለቡድኑም ሆነ ለሀገር ህልውና ዋና አደጋ ሊሆን የሚችለውን ሃይል በችልተኝነት በመመልከት በጊዜው አስፈላጊና ወሳኝ እርምጃዎች ለመሰድ ባለመቻሉ ሁኔታዎች ተባብሰው ዛሬ የደረስንበት አስከፊ ደረጃ ላይ ልንደርስ ችለናል።
መስቀል አደባባይ የጀመረ ሽብር ቡራዩ ደርሶ አዲስ አበባን ፣ሻሸመኔን፣ዝዋይን፣ ጌዴዎን፣ጉጂን…ወዘተ ብሎ አማራ፣ቤንሻንጉል፣ ኦሮሚያ ፣አፋርና ሶማሌ ክልል ዞሮ ተመልሶ ደግሞ ሰሞኑን የሰማነውን በኦሮሚያ ክልል የተካሄደ፣ማንነት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ ላይ ስንደርስ፣ ከመንግስት በኩል ተደጋጋሚ የሃዘን መግለጫና እርምጃ ይወሰዳል ከሚለው ቃል በስተቀር፣ በተግባር የታየ የችግሩን ግዝፈት የሚመጥን ይሄ ነው የሚባል እርምጃ በነዚህ የሽብር መልክተኞች ላይ ተወስዶአል ለማለት የሚያስችል ነገር አልታየም።
መንግስት እነዚህን ሽብርተኞች ማስቆምም ሆነ ማስታገስ እስካልቻለ ድረስ ሃገራዊ ሰላምም ሆነ እድገት የሚታሰብ አይደለም። የመንግስት ዋናና ተቀዳሚ ተግባርም የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ መሆኑን ለአፍታ እንኳን ቢሆን፣ የመንግስት ስልጣን የያዘው ሃይል ሊዘነጋው የማይገባ ጉዳይ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት አመታት በሀገራችን ያለማቋረጥ በሚካሄዱ ህዝባዊ ሰቆቃዎች ምክንያት ልናስታውሰው እንገደዳለን ።
መቀሌ በመሸገው የህወሃት አቀነባባሪነት ኦነግ ሸኔን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች በህዝብ ላይ የሚያካሂዱትን፣ ማንነት ላይ ያጠነጠነ የጥፋት እርምጃ በጊዜ ካልተገታ፣ ሀገራችንን ወደ የርስ በርስ ጦርነትና ሃገርን ወደ ማፍረስ እርምጃ ስለሚሸጋገር ፣ መንግስት ግልጽነት በተሞላበትና የጥፋት ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ ፣ ሆኖም የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት ታሳቢ ያደረገ ቁርጠኝነት የተላበሰ እርምጃ መውሰጃው ጊዜ ትንሽ የረፈደ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ አልመሸምና ጊዜ ሳያባክን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው።
የመንግስት በጊዜ እርምጃ አለመውሰድ ሽብርተኞችን የልብ ልብ ሲሰጥ፣ በአንጻሩ ህዝብ መንግስት ላይ ያለውን እምነት እየሸረሸረ ይሄዳል። ማናቸውም የመንግስት እርምጃ ደሞ የህዝብ አመኔታና ትብብር ከሌለው ከግቡ ሊደረስ ስለማይችል መንግስት ለነገ ሳይል ህዝብን ከጥቃት ሰለባ ለማዳን አጣዳፊና አስተማማኝ እርምጃ እንዲወስድ ይገዳዳል።