>
5:26 pm - Sunday September 15, 9337

ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የጋራ ም/ቤቱ ጠየቀ!!! (በሜሮን መስፍን)

ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የጋራ ም/ቤቱ ጠየቀ!!!

በሜሮን መስፍን

በፌዴራል መንግስት እና በጽንፈኛው ህወሓት መካከል የተፈጠረው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም እና ሁለቱ ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ፡፡
ምክር ቤቱ ከግጭቱ ሁለቱም ወገኖች የሚያተርፉት ነገር የሌለ ከመሆኑም ባሻገር ሃገሪቱን የሚጎዳ በመሆኑ የተፈጠረው ግጭት እንዲቆም ጠይቋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ የፊታችን ቅዳሜ ሃገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ህወሃትን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ውይይት ለማድረግ እቅድ ይዞ እንደነበርም በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በተለይም በመንግስትና በጽንፈኛው ህወሃት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት አጀንዳ ቀርጾ ከማዘጋጀቱም ባሻገር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቱን ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ጉዳዩ ወደ ግጭት በማምራቱ እቅዱ ሊሳካ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡
ግጭቱ እንደ ሃገር ዋጋ እንደሚያስከፍል የጋራ ምክር ቤቱ ገልጾ ችግሩን በውይይት ለመፍታት አሁንም አለመርፈዱን ጠቁሟል፡፡
በአለም የፖለቲካ ታሪክ ተደርጎና ተሰምቶ የማያውቅ ተግባር በህወሃት በመፈጸሙ ወደ ግጭት መገባቱን የገለጸው የጋራ ምክር ቤቱ ያም ቢሆን ግን ወደ ውይይት ለመምጣት ሰፊ እድል አለ ብሏል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ሁለቱ ወገኖች በአስቸኳይ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚጠይቅ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህ ይበል እንጅ የፌደራል መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለወራት ያህል በትእግስት ተሞክሮ ባለመሳካቱ ጦርነቱም የመጨረሻ አማራጭ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
ህወሃት የአገሪቱን ሕገ መንግስት በመጣስ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የፌዴራል መንግስት በአገሪቱ ሕገ መንግስት መሰረት የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራን እየሰራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
ቡድኑ  ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተለያዩ ቡድኖች ድጋፍ በማድረግ አገርን የማተራመስ ተግባር ላይ ተጠምዶ የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን በትዕግስት ሲከታተል መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል መንግስቱ ህወሃት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የሪፎርም አካል እንዲሆን የውይይት፣ የድርድርና የጋራ መግባባት እድሎች ተከፍተው ሁሉም የሰላም አማራጮች የተጠቀመ ቢሆንም ቡድኑ ባሳማራቸው የጥፋት ኃይሎች  አማካኝነት በምዕራብ ጎንደር፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጉራ ፈርዳ እንዲሁም በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ጥቃት መፈጸሙን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በተናጠል በሰጧቸው መግለጫዎችና በተለያዩ መንገዶች የምክር ቤቱ መግለጫ የጋራ አቋማቸውን የሚያንጸባርቅ አለመሆኑም እየተገለጸ ይገኛል።
Filed in: Amharic