>
5:13 pm - Thursday April 20, 3572

ጦርነት አይበጀንም ሲባል… (አክመል ነጋሽ)

ጦርነት አይበጀንም ሲባል…

አክመል ነጋሽ

ኢትዮጵያ አሁን ድረስ በቀውስና አለመረጋጋት ውስጥ ያለችው አንድም በቀድሞ ታሪኳ ምክንያት ነው። በታሪካችን ውስጥ የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶች አሁንም ድረስ እረፍት ነስተው ያቆራቁሱናል። «ለውጥ መጣ» ባልነው ያለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህ መቆራቆዞች እንዲረግቡና ለአንዲት ሀገራችን በጋራ አዲስ ማኅበራዊ ኮንትራት እንድንፈርም የምር የሆነ ብሔራዊ መግባባት ማድረግ ይገባ ነበር። ይሄ ብዙዎች ጠብቀውት ግን ጠ/ሚኒስትሩና መንግሥታቸው የብዙ ነገሮችን ቅደም ተከተል አዛብተው ዛሬ የደረስንበት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
ዛሬ ደግሞ የትናንቱ የታሪክ ቁርሿችን ሳይፈታ ሌላ የታሪክ ቁርⶄ ተቦክቶ እየተጋገረልን ነው። በብልጽግና ፓርቲና በሕወሓት መካከል ቀደም ብሎ የተጀመረው የርዕዮተ ዓለም መካረር አሁን ወደ ለየለት ጦርነትና ደም መፋሰስ ተሸጋግሯል። ትናንት ሁለቱ ቡድኖች በኢሕአዴግ ጥላ ሥር በጋራ የኢትዮጵን ሕዝብ ያለርህራሄ ሲያሰቃዩና ሲገድሉ ኖረዋል።  አሁን የዚህ ጦርነት አሳሳቢም አሳዛኝም ጉዳይ ወንድማማች በሆኑ የአማራና የትግራይ ተዋጊዎች መካከልም የሚደረግ መሆኑ ነው።
አንድአንዶች «ጦርነቱ ከሕወሓት ጋር ነው የሚካሄደው» እያሉ ሊያሞኙን ይፈልጋሉ። ጦርነት ሜዳ ላይ ያሉት አቦይ ስብሀት ወይም ደብረ ጸዮን አይደሉም። የሚዋጉና የሚሞቱት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አፍላ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ አላቸው፤ እነሱ ላይ በጦርነቱ ሰበብ የሚደርስ ጉዳትና ሞት ከቤተሰብ ተነስቶ ቤተዘመድና ጎሳን አልፎ ሰፊው ማኅበረሰብ ጋር ይደርሳል። ይህ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ቂም ይፈጥራል፤ ተክሎም ጥላቻና የበቀል ስሜት አብሮ ያድጋል።
በአማራ ክልልና በመከላከያው በኩልም በተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው ተዋጊዎች እንጂ ኮረኔል አብይ አሕመድና በዙሪያው ያሉ አመራሮች አይደለም እየተዋጉ ያሉት።
 በዚህ መካከል የሚከሰት ደም መፋሰስ፣ ሞትና እልቂት የነገ ታሪካችንን እንደሚያበላሸው ለማወቅ ምሁር መሆን አይጠይቅም። በተለይ በባሕል፣ በታሪክና በሃይማኖት አንድ የሆኑት የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ወደለየለት ጦርነት እንዲገቡ የሚካሄደው የጦር አውርድ ቅስቀሳ እጅግ በጣም አስፈሪ ነው።
ይሄን ጦርነት በማካሄድ የሚፈታ ችግር አይኖርም፤ እንደውም በመካከላችን ያሉ ችግሮችን እንዲባባሱ ያደርጋሉ የምንለው ለዚህ ነው። ጦርነቱ በየትኛውም ወገን አሸናፊነት ቢጠናቀቅ ነገሮች ትናንት በነበሩበት እንደሚቀጥሉ ማሰብ አይቻልም።  በዚያ በኩል ሆነው «ውጋው! ጨፍጭፈው!» ብለው የሚቀሰቅሱ ሰዎች «ከጦርነት የማይሻል ምንም ነገር የለም፤ ጦርነቱን አቁሙልን» ብለን የጠየቅን ሰዎችን ለመዝለፍና ለመራገም የሚያባክነቱትን ጉልበት ጦርነቱ እንዲቆም በመማጸን ቢያውሉት ለሀገራችን መጻኢ እድልና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ቁም-ነገር እንደሠሩ ይቆጠርላቸው ነበር።
Filed in: Amharic