>

በኢትዮ-360 እና በርዕዮት ሜዲያዎች ላይ  የሚደረጉ የሐሰት ወሬዎችና ዘለፋዎች (ከይኄይስ እውነቱ)

በኢትዮ-360 እና በርዕዮት ሜዲያዎች ላይ  የሚደረጉ የሐሰት ወሬዎችና ዘለፋዎች

ከይኄይስ እውነቱ


ዛሬ በኢትዮጵያችን በሕዝብ ሀብትና ‹‹ባለቤትነት›› የሚንቀሳቀሱ ‹መንግሥታዊ› የመገናኛ ብዙኃኖች፣ በየክፍላተ ሀገራቱ ጐሣን መሠረት አድርገው የተደራጁ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃኖች፣ ከመንግሥት ጋር ተለጥፈው የሚንቀሳቀሱ (state-affiliated medias- እንደ ዋልታና ፋና) ሜዲያዎች፣ የግል ነፃ እና አድርባይ ሜዲያዎች እንዲሁም ነፃ እና የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ እንዲያሠራጩ በሕዝብ ሀብት ድጎማ እየተደረገላቸው የሐሰት ወሬዎችንና መረጃዎችን የሚያስተላልፉ የማኅበራዊ ሜዲያዎች አሉ፡፡ የሜዲያ ባለሙያ ባለመሆኔ ዝርዝር ሙያዊ ጉዳይ ውስጥ ልገባ አልደፍርም፡፡ ግን ፊደል እንደቈጠረ ዜጋ የራሴ የግል ትዝብቶች አሉኝ፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በሕግ ረገድ የተጣለ ገደብ (censorship) ባይኖርም የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር የተቈራኙት ሜዲያዎች ላይ ያልተጻፈ ገደብ እንዳለባቸው ግን ከዜና እወጃ ጀምሮ ከሚያቀርቧቸው ሌሎች መረጃዎች መረዳት የሚያዳግት አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ለመድረስ የሚያስብ አእምሮና የሚያመዛዝን ኅሊና ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎቹ ‹ጋዜጠኞች› አገዛዞች ከሚፈልጉት ውጪ ለማቅረብ ድፍረቱ አልነበራቸውም፣ አሁንም የላቸውም፡፡ ባድርባይነት ታማኝነትን ለማሳየት የሚደረገው ፉክክርም ቀላል አይደለም፡፡  ከዚህ ቀደም እንደገለጽኹት ባለፉት 45 ዓመታት ባጠቃላይ፣ ከዘመነ ወያኔ ጀምሮ ባለፉት 30 ዓመታት በተለይ እነዚህ ሜዲያዎች (የኤሌክትሮኒክሱም ሆነ የኅትመቱ) ከእውነት ጋር በመጣላት ሐሰትን በዐደባባይ በማንገሥ ለኅብረተሰባችን ውሸትን በማለማመድ የውሸት ባህል ሥር እንዲሰድ አድርገዋል፡፡ በዚህም በኅብረተሰባችን ለሚታየው ማኅበራዊ ድቀት ተጠያቂዎች ከሚሆኑ ተቋማት መካከል ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ 

ወደ ግሉ ሜዲያም (የኤሌክትሮኒክሱም ሆነ የኅትመቱ) ስንመጣ የአገዛዞች ጫናና ማሳደድ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጥቂቶች ለሕዝብ፣ ለሙያና ለኅሊናቸው ታምነው ቢሠሩም አብዛኞቹ ለአገዛዞች በሎሌነት ለማደር የሚሯሯጡ መሆናቸው የየዕለት ክስተት ነው፡፡ ግልጹን ለመናገር አብዛኞቹ ራሳቸውን ‹ጋዜጠኛ› ብለው ይጥሩ እንጂ ሙያው የሚጠይቀው የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድና ሥነ ምግባርም የላቸውም፡፡ ‹ወረቀቱንም› የያዙት ወይ ከአንጋፋ ቀደምቶቻቸው አይማሩ ወይ የመርህ ሰዎች አይደሉ ወይ መደበኛና ተከታታይነት ባለው ንባብ የተጠመዱ ባለመሆናቸው በቂ መረጃና ማስረጃ ሳይኖራቸው ለዝግጅት የሚሰለፉ ሆነው ይታያሉ፡፡ ስለሆነም የሙያ ውድቀቱና አድርባይነቱ የመንግሥት የግል ብለን ልዩነት የምናወጣለት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ውድቀት ረገድ በሌሎችም ሙያ ቢሆን የጎላ ልዩነት አናስተውልም፡፡ ነገር ግን ነፃነታቸው የተረጋገጠ መገናኛ ብዙኃኖች የሕግ ልዕልና ያለበት መንግሥተ ሕዝብ ለማስፈንና ቀጣይነቱንም ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ አንድ ዓምድ እና በዚህም ምክንያት በ‹አራተኛ መንግሥትነት› እንዲታዩ የሚያደርጋቸው መሆናቸው እንጂ፡፡ 

የመገናኛ ብዙኃኖችን አሠራር የበለጠ ያከፋው ደግሞ የጦዘው የጐሣ ፖለቲካ በአገዛዙ የሚደገፉና በግል ሜዲያ ስም ሐሰትን የሚነዙ፣ በፈጠራ ትርክት እና ጐሣንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ሕዝብን ለእልቂት የሚዳርጉ እጅግ አደገኛ ነገር ግን ተራ እንቶ ፈንቶዎች የሚሠራጩበት፣ የሕግ ተጠያቂነት ያለበት አገር ቢሆን አንድ ቀን ሊሠሩ የማይችሉ እንደ ኦ ኤም ኤን ዓይነት ሜዲያዎችም መፈልፈላቸው ነው፡፡ በዚህ ላይ ራሳቸውን ‹ቀስቃሽ› (አክቲቪስት) ብለው የሰየሙ አንዳንድ ወገኖች ድንገት ተነስተውና በ‹አክቲቪስትነቱ› ላይ የ‹ጋዜጠኝነት› ካባ ደርበው በየቦታው ቃለ መጠይቅ አድራጊዎች ሆነዋል፡፡ ሥርዓት ያጣ አገር፡፡

ነገሬን ለማሳጠርና ወደተነሳሁበት ርእስ ለማለፍ ባለፉት 30 ዓመታት ሜዲያዎች በአመዛኙ የፕሮፓጋንዳና የትግል መድረኮች በመሆናቸው (የመንግሥት፣ ተለጣፊዎቹና የግል አድርባዮቹ የፕሮፓጋንዳ፤ ለመንግሥት ያላደሩትና በዋናነት በውጭ የሚገኙት የትግል) እንደ ተራ ዜጋ ሚዛናችን እውነቱን/ጥሬ ሐቁን በመረጃና ማስረጃ አስደግፈው ማቅረባቸው፣ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት ማንፀባረቃቸው፣ የአገር አንድነትንና ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደማቸው፣ ከጭፍን ጥላቻና ዘረኛነት መራቃቸው ይመስለኛል፡፡ ባንፃሩም እውነትና ትክክለኛነት፣ ነፃነት፣ ሚዛናዊነት/ከአድልዎ መራቅ፣ ሰብአዊነት (ሰዎችን ላለመጉዳት ጥንቃቄ ማድረግ) እና ተጠያቂነት ወይም በኃላፊነት ስሜት መሥራት የሚባሉት መሠረታዊ የጋዜጠኝነት መርሆዎች በአብዛኛው ሜዲያዎች ይጠበቃሉ ለማለት አልደፍርም፡፡ 

በዚሁ መሠረት ‹ኢሳት› የሚባለውና አሁን አገር ውስጥ ጭምር የሚንቀሳቀሰው ሜዲያ የወያኔን አገዛዝ መታገያና በአፈናው ዘመን ‹የሕዝብ ልሳን› በመሆን ትልቅ አገራዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቶ ዐቢይ ከመጣ ወዲህ ‹ባለቤቶቹ› ለዐቢይ በማደራቸው በአሁኑ ጊዜ ለአገዛዙ ‹የጭን ገረድ› ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ 

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከኢሳት ተገፍቶ የወጣው ‹ኢትዮ-360› እንዲሁም በቴዎድሮስ ጸጋዬ የሚመራው ‹ርዕዮት› ኢትዮጵያዊነትን ከሚያራምዱ የግል ሜዲያዎች መካከል ጉልህ ሥፍራ ያላቸውና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ ባንፃራዊነት ስለ ብሔራዊ ፈትለ ነገሮች የተሻለ ሐቅና ትንተና የሚሰጥባቸው ሜዲያዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በሚያቀርቡት ተግዳሮት ከአገዛዙና አገራችንን በሽብር እየናጡ ካሉ ኃይሎችና ለፕሮፓጋንዳ ሥራ ካሰማሯቸው ተከፋዮቻቸው ቀላል የማይባል ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ስድብና ዘለፋ እየደረሰባቸው መሆኑን እናውቃለን፡፡ 

እነዚህ ሜዲያዎች በሚሰጡት ትንተናና በሚይዙት አቋም ሁሌም እንስማማለን ማለት ግን አይደለም፡፡ በሜዲያዎቹ ከሚንፀባረቁት የኢትዮጵያ ታሪክ አረዳድ፣ አገራችን የፋሺዝምና የናዚዝም ባሕርያትን በተላበሱ አገዛዞች የገጠማትን የህልውና ችግር በመረዳትና ዐበይት ሳንካዎችን ነቅሶ በመለየት ረገድ፣ ከችግራችንም መውጫ መንገድ በመጠቆም ረገድ፣ በኃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ ረገድ፣ የአገዛዙንም ሸፍጥ ከሥር ከሥሩ እየተከታተሉ በማጋለጥ ረገድ፣ አዳዲስ መረጃዎችን በመስጠት ረገድ፣ በዚህም ሕዝብን በትክክለኛ መረጃ በማስታጠቅ የሚያደርጉት የማስተማር/የማንቃት ጥረት እንዲሁም መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እያደረጉ ያሉት እገዛ እጅግ የሚያስመሰግናቸው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ 

በመሆኑም የሚደርስባቸው ፈተና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ፣ ተጽእኖ ፈጣሪና መልካም ውጤት እያስገኘ በመሆኑ እንኪያ ሰላንቲያ ውስጥ ሳይገቡ (አንዳንዱ ዘለፋ የግል ሰብእናን የሚጎዳ መሆኑ ቢሰማኝም) ሥራቸውን በተሻለ ጥራትና ትጋት እንዲሠሩ የሚያበረታታ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በኢትዮጵያዊነት አቋማቸው እስከቀጠሉ ድረስ ከጎናቸው መሆናችንንም ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም ጽሑፌን ከርእሴ ወጣ ባለ ጉዳይ እቋጫለሁ፡፡ በቅርቡ ኦሕዴድ በሚመራው አገዛዝና በወያኔ መካከል ‹ጦርነት› እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡ ዜጎች በተቀሰቀሰው ‹ጦርነት› ረገድ የተለያየ አመለካከትና አቋም እንዳላቸው ይገባኛል፡፡ ይህንንም አከብራለሁ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ስለ ‹ጦርነቱ› ‹‹ትርጕም የሌለው ‹ጦርነት› ›› በሚል የግል አስተያየቴን ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ https://www.ethioreference.com/archives/25012 ምክንያቴንም ለማብራራት ሞክሬአለሁ፡፡

በጽሑፌ ያቀረብኹት አቋም እንዳለ ሆኖ፣ የዐቢይ አገዛዝ ‹ጦርነቱ›ን የሚያካሂድበት ዓላማዬ ብሎ በገለጸው ውስጥና በተከታታይ በራሱም ሆነ በባለሥልጣናቱ በሚሰጠው መግለጫ ወያኔ/ሕወሓትን እንደ ድርጅት መደምሰስና አሸባሪ አድርጎ የመፈረጅ (የግብር ወንድሙን ኦነግንም ይመለከታል) አቋም አልሰማሁም፡፡ ሕወሓት እንደ ድርጅት እንዲደመሰስና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕገ ወጥ ተደርጎ መታገድ አለበት የሚለው አቋሜ ጽኑና የቆየ ነው፡፡ አገዛዙ በዚህ ‹ጦርነት› የወገኖቻችን (በየትኛውም ወገን ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ማለቴ ነው) ሕይወት ተገብሮና ሀብት ወድሞ ቢያንስ ሊያደርግ የሚገባው ነገር ሕወሓትን መደምሰስ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ የ‹ጦርነቱ› ዓላማ የበለጥ ገሃድ ይወጣል፡፡ ቀጣዩን ሂደት መክሮ ለአገሩ ህልውና የሚበጀውን መወሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም ሕዝብ የማወቅ መብት ስላለው አገዛዙ የተቋረጡ መገናኛዎችን እንዲቀጥሉ አድርጎ ስለ ‹ጦርነቱ› ትክክለኛና የተጣራ መረጃ እንድናገኝ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

 

 

Filed in: Amharic