>
5:26 pm - Wednesday September 15, 2506

ያብይ ጦርነት (መስፍን አረጋ)

ያብይ ጦርነት

መስፍን አረጋ


በሰሜናዊ ጦቢያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተመለከተ አበክረው ሊጠየቁ /የሚገባቸው/ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄወች አሉ፡፡  የመጀመርያው ጥያቄ፣ ዐብይ አህመድ ወያኔን ሊወጋት ፈልጎ ከሆነ፣ ሊወጋት የፈለገው ለምንድን ነው የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ ወያኔን የሚወጋት እንዴትና በማን ነው የሚለው ነው፡፡

የደርግን አስከፊ አገዛዝ በጽኑ ያወግዙ የነበሩ ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች)፣ እይታቸውን ደርግ ላይ ብቻ በማድረግ ‹‹ደርግ ይውደቅ እንጅ …›› በሚል እሳቤ ወያኔን በከፍተኛ ደረጃ ይደግፏት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡  ወያኔ ግን ደርግን ነቅላ ምን እንደተከለች የምናውቀው ነው፡፡  

አሁን ደግሞ ‹‹ወያኔ ትደምሰስ እንጅ …›› በሚል እሳቤ ያብይ አህመድን ጦርነት የሚደግፉ ጦቢያውያን እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ አንዳንደቹ ደግሞ ያብይ አህመድን ጦርነት በወያኔ ላይ የሚደረግ ጦርነት እንደሆነ አድርገው በመውሰድ ፍትሐዊ ጦርነት ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡  በርግጥም ያብይ አህመድ ጦርነት በወያኔ ላይ የሚደረግ ጦርነት ነውን?  ከሆነስ ለምን? 

ዐብይ አህመድ ወያኔን ሊነቅላት የፈለገው፣ በምትኳ ኦሮሙማን ተክሎ በመላው ጦቢያ ላይ አንዳችም ተገዳዳሪ የሌለው አዛዥ ናዛዥ ለመሆን ከሆነስ?  ያብይ አህመድ ዋና ዓላማ ለሃያ ሰባት ዓመታት አማራን ከገረፈው የወያኔ ወላፈን በላይ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት አማራን የለበለበውን የብልጽግናን እሳት፣ አማራን በሚለመጥጥ የኦሮሙማ ረመጥ ለመተካት ከሆነስ? 

አብይ አህመድ ማለት እኮ፣ አፍንጫው ሥር አማሮች እንደ ከብት ሲታረዱ ለይምሰል እንኳን ሐዘኔታ ያላሳየ፣  ቡራዩን እንደ መቀጣጫ በመጠቀም፣ ዝንቤን እሽ ብትሉ መቶሺወቻችሁ ትታረዳላችሁ በማለት ባዲሳባ አማሮች ላይ የዛተ፣ የፀራማራው የወያኔ አገዛዝ ዋና ተዋናይ የነበረ የወያኔ ኮለኔል ነው፡፡  ስለዚህም ይህ በወያኔ ቤት ደቁኖ፣ ከጳጳሱ ከስብሐት ነጋ በላይ የቀሰሰ የወያኔ ቄስ፣ ያሳደገችውን ወያኔን ለመንከስ የተነሳሳው፣ ወያኔ በሰሜን እዝ ያማራ መኮንኖች ላይ ባደረገችው ጭፍጨፋ ሳቢያ ነው የሚባለው ትርክት ሐሰት ብቻ ሳይሆን ቧልት ነው፡፡  በመሆኑም ያብይ አህመድን ጦርነት ትክክለኛ ምክኒያት በትክክል ተረድቶ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ በተጠንቀቅ መጠባበቅ ብልህነት ነው፡፡  ያልጠረጠረ ተመነጠረ፡፡

ሕገመንግሥት የሚባለውን የወያኔና የኦነግ የስምምነት ሰነድ ቀይሮ በብሔር መደራጅትን በመከልከል ብቻ ያለምንም ጦርነት ወያኔን ማክሰም ሲቻል፣ ዐብይ አህመድ ጦርነት ለምን ተመረጠ?  

ሻሸመኔ የታረዱት አማሮች ደም ሳይደርቅ ሽመልስ አብዲሳን ካባ ለማልበስ የተጣደፈው ተመስገን ጡሩነህ፣ ደብረጽዮንን አፈር ለማልበስ ለምን ተጣደፈ?

ቀጥለን ደግሞ ሁለተኛውን መሠረታዊ ጥያቄ እናጢን፡፡  ዐበይ አህመድ ወያኔን የሚመታው የኦሮሙማን ልዩ ኃይል ከኋላ አሰልፎ ያማራን ገበሬወች ፈንጅ ረጋጭ በማድረግ ከሆነ፣ የወያኔ መመታት ላማራ የሚበጀው እምኑ ላይ ነው?  አማራ ከሞተ በኋላ ጠላቱ ወያኔ ብትሞት ላማራ ምን ይተክርለታል?  እየሞተች ያለችው ወያኔ ነፍሷ እንዲወጣ የተፈለገበት ዘዴ አማራንና ትግሬን ሕዝብ ለሕዝብ ደም የሚያቃባ ከሆነ፣ (ወያኔ ጉዳት እንዳታደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ) የተፈጥሮ ሞቷን እስክትሞት መታገስ አይሻልም ወይ?  በአነሯ በወያኔ ላይ ጉልበትን ከማባከን፣ ትኩረትን ከመበታተን ይልቅ፣ በጅቡ በኦነግ ላይ ሙሉ ኃይልንና ትኩረትን በማዋል ባንድ ዲንጋ ሁለት ወፍ መምታት አይቻልም ወይ?  

ወያኔ የአማራ መሠረታዊ ጠላት ናት፣ ምንም ጥያቄ የለወም፡፡  ኦነግ ደግሞ ከወያኔ የከፋ ያማራ መሠረታዊ ጠላት ነው፣ ይሄም ምንም ጥያቄ የለውም፡፡  ስለዚህም ላማራ የሚበጀው ሁለቱም መሠረታዊ ጠላቶቹ ሲራኮቱ ከዳር ቁሞ እየታዘበ፣ ጉልበቱን ቆጥቦ በተጠንቀቅ መጠባበቅ ነው፡፡  በሁለቱ መሠረታዊ ጠላቶቹ መራኮት የትግራይ ሕዝብ የሚጎዳ ከሆነ ደግሞ ወንድሙን የትግራይን ሕዝብ አለሁልህ በማለት ሐበሻዊ አንድነቱን ማጠናከር ነው፡፡ 

ሁሉም የጦቢያ ጠላቶች ጦቢያን ለማጥቃት ሁልጊዜም የሚጠቀሙበት ዘዴ አንድና አንድ ነው፡፡  እሱም አማራንና ትግሬን አቃርኖ ሐበሻን መከፋፈል ነው፡፡  ባዕዶቹ ቱርኮች፣ ግብጾችና ጣልያኖች የተጠቀሙት እሱን ነበር፡፡  ባንዳዋ ወያኔ በደደቢት ማኒፌስቶዋ ላይ በግልጽ አስቀምጣ በተግባር ያዋለችውም እሱኑ ነው፡፡  ኦሮሙማውያን ደግሞ አንድ ጊዜ ኦሮማራ፣ ሌላ ጊዜ ኦሮትግሬ የሚሉት፣  አማራና ትግሬን አቃርነው አንዱን ባንዱ ለመምታት ብቻና ብቻ ነው፡፡  ዐብይ አህመድ ደግሞ የጦቢያውያን ሳይሆን የኦሮሙማውያን መሪ መሆኑን ባመራሩ በግልጽ አስመስክሯል፡፡

 

ያገራችን ጦቢያ መሠረተ ችግር

ያበሻ መዳከም እንጅ በመቃቃር

መቸም ሁኖ አያቅም የጠላት መጠንከር፡፡

ሐበሻ ተባብሮ ባንድነት ካደመ

ኦነግ አለቀለት አበቃ አከተመ፣

የገዳው ታማሚ በግዱ ታከመ

ዓይኖቹን ገለጠ ቅዠቱን አቆመ፡፡

 

    መስፍን አረጋ 

    Email: mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic