>
5:01 pm - Monday December 3, 7562

ጠቅላዩ የበሉት የዲፕሎማሲ ቁማር...!!!  (ሙሉአለም ገብረመድህን)

ጠቅላዩ የበሉት የዲፕሎማሲ ቁማር…!!!

 ሙሉአለም ገብረመድህን

 

አራት ጉዳዮች እናንሳ:-
~
፩ ራያ ዳግማዊ ደብረታቦር ?
በፌዴራሉ እና በከሃዲው ቡድን በተመሳሳይ፣ ራያ ላይ የሰፈረው የሠራዊት መጠን ግዝፈቱ ታሪክን የኋሊት ለማየት ያስገድዳል። (ታሪኩ የሚታወቅ በመሆኑ ማብራሪያ አያስፈልገውም) በአጭሩ በሁለቱም በኩል ያለው አሰላለፍ የ1983ቱን የደብረታቦር_ጉና ውጊያ የሚያስታውስ ነው። መልክዓ-ምድሩ በራሱ የውጊያውን ባህሪ የሚወስነው በመሆኑ ‘የጠቅላይ ሰፈር’ የጦር መሀንዲሶች ውሳኔ የውጊያውን ውጤት ይወስነዋል። በከተሞች ያለው የመንደር አሰፋፈርና ጥግግት ተስፋ ለቆረጠው ከሃዲው ኃይል ንጹሃንን ይዞ ለመጥፋት ዕድል እንዳይሰጠው ያሰጋኛል።
፪  ኢሕዴን Vs ትሕነግ
ከሃዲው ትሕነግ መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባ፣ በቅራቅር በኩል ደግሞ የአማራ ሕዝብን በከባድ መሳሪያ ፊት ለፊት መውጋት ከጀመረበት ደቂቃ ጀምሮ ጥቃቱንና የመልሶ ማጥቃቱን ውጊያ በየ አቅጣጫው ለመከታተል ሞክሬለሁ። ወታደራዊ ስምሪቱና አሰላለፉ አስገራሚ ስዕል ሰጥቶኛል። ማጣራት ከቸገረኝ የባድመ ግንባር በስተቀር በሁሉም ግንባሮች (Active War Zones & Standing for Command Zones) አዋጊ ሆነው የተሰለፉት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የመስመር ኃይሎች የኢሕዴን ታጋዮች ናቸው። (ስም መዘርዘሩ ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም)
በሌላ በኩል በአማራ ልዩ ኃይል በብርጌድ፣ በሻለቃና በሻምበል ተዋረዳዊ የዕዝ ሰንሰለት ያሉት አመራሮች አብዛኞቹ የኢሕዴን ፍሬዎች ናቸው። ያው በከሃዲው ቡድን በኩል ያሉ አዋጊዎች የሚታወቁ የትሕነግ ነባር ታጋዮች ናቸው። ዋናዎቹ ሜ/ጀኔራል ታደሠ ወረደ፣ ብ/ጀኔራል ምግበ ኃይሌ እና ሜ/ጀኔራል ኃይለሥላሴ ይገኙበታል። በአጭሩ ውጊያው በኢሕዴን እና በትሕነግ ወታዳራዊ አመራሮች እየተመራ የሚካሄድ ነው።
ከሃዲው ትሕነግ በአገዛዝ ዘመኑ፣ የኢሕዴን ወታደራዊ ታጋይ የነበሩና ድኀረ ደርግ መከላከያ ሠራዊት ሲዋቀር ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀሉ ታጋዮችን መርጦ ሲፈጽምባቸው የኖረው ከሞት የከፋ በደል የአደባባይ ምስጢር ነው። ዛሬ እንኳንስ መከላከያ ሠራዊቱ እንደ ተቋም ክህደት ተፈጽሞበት፤ ያ ቅራኔ  ቁጭትና እልህ አሳድሮባቸው ኑሯል። እናም የኢሕዴን ፍሬዎች የሚያደርጉትን ያውቃሉ። በነገራችን ላይ የኢህዴን የፖለቲካ ክንፍ እንጅ ወታደራዊ ክንፉ ለአማራ ጠላት አልነበረም። የፀረ-ደርግ ትግል ፍሬው የባከነ በፖለቲካ አመራሩ ክህደት ነው። መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩ/ ያሉ የኢሕዴን ታጋዬችን በተመለከተ ስለ ዓላማ ቁርጠኝነታቸው ጀኔራል ተፈራ ማሞን እያሰብክ እነሱን ሳላቸው፤ አሁናዊ ስሜታቸው የተፌ ካርቦን ኮፒ ናቸው። የድል ጉዞው ፍጥነት ምንጩ ተገለጠልህ?
 
፫ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ቁማር
ከሃዲው ቡድን ጥቃት ከፈፀመበት ሠዓት ጀምሮ
 የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ ለማስከበር የከፈተውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጉዳዩን በምን መልኩ ያየዋል የሚለው ጉዳይ ለብዙዎቻችን አሳሳቢ ነበር።
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕረቡ ረፋድ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ለአሜሪካ፣ እንግሊዝና እስራኤል ኢምባሲ የደህንነት አታሼዎች ወሬው እንዲደርስ አደረጉ። በተመሳሳይ ለአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር ወሬው እንዲደርስ ተደረገ። ነገርዬው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ  ያፈተለከ መረጃ በሚል ነበር የተበነው። መረጃው ዕረቡ ረፋድ ወጥቶ በአማካይ ከስምንት ሰዓታት በኋላ አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ  ማይክ ፖምፒዮ፣ እንግሊዝ በኢንባሲዋ በኩል ለፌዴራሉ መንግሥት የወገነ መልዕክት አስተላለፉ። (‘We are deply concerned …Bla Bla ‘ የሚለው መንደርደሪያቸው ‘Only Fire on your Target’ ብለህ ተርጉመው) ሌላ ነጥብ ላመላክትህ ያ አፈትላኪ መረጃ ወጣ በተባለ ከ24 ሰዓት ቆይታ በኋላ እስራኤል (ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም) የአንበጣ መንጋ ወረራን ለመከላከል በሚል ሽፋን የአገር ውስጥ ምክትል የደህንነት ሹሙን ጋዲ ይባርክን ላከች። የትውልደ ኢትዮጵያዊው  ጨዋታ  የተቋጨው ጠቅላዩ ቢሮ ውስጥ ካሉ የደህንነቱ ሹማምንት ጋር ነው። የእስራኤልን የውግንና መልዕክት ይዞ የመጣው ወሳኝ ሰው፥  ከመጣሁ አይቀር በሚል እግረ መንገዱን አቶ ደመቀ መኮንን ቢሮ ጎራ ብሎ ፎቶ ተነስቶ የዜና አቅጣጫ ቀይሮ ወጣ። ጨዋታው እንዲህ ነው፦ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የላከችውን ሠላም አስከባሪ ጦር ብታስወጣ አከርካሪው የተሰበረው አልሸባብ ተመልሶ ያንሰራራል። ከዚህም አልፎ ከመካከለኛው ምስራቅ ነጻ ቀጠናዎች ጠበውባቸው መላወሻ አጥተው ድምፃቸው የጠፋው አልቃይዳይ እና አይ.ስ በአፍሪቃ ቀንድ ነጻ መሬት እንዲያገኙ በር ይከፍታል።
 ኢጋድ፣ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ተመድ፣ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሜሶም) ያለ ኢትዮጵያ ሰራዊት እገዛ የሶማሊያን ጉዳይ ሊፈቱት አይችሉም።  የዛች መከረኛ አገር የፀጥታ መሻሻል፣ የአልሸባብ አከርካሪ ለመሰበሩ የኛ ሠራዊት ትልቅ አቅም ሆኖ አገልግሏል። እናም የአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ቁልፍ የተረከበ ሁሉ ይህችን ካርታ መሳቡ ይጠበቃል።
መለስ በለው ኃይለማርያም ይሄን አጀንዳ እየሳቡ ብድርና ዕርዳታ አግንተውበታል። ዐቢይ አህመድ ደግሞ ‘ጦር ሰሪ ነን’ ባዮን ከሃዲ ቡድን  ለመደምሰስ ተጠቅሞበታል። አሁን በየ አቅጣጫው ‘ሁሉን አቀፍ ድርድር’ በሚል በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩ የትኞችም አካላት የመንግሥትን እጅ የመጠምዘዝ አቅም የላቸውም። የአውሮፓ ሕብረት ጉትጎታ ለከሃዲው ትሕነግ ፍቅር ኑሮት ሳይሆን፣ ጦርነቱ በሚፈጥረው ሰብዓዊ ቀውስ የስደተኞች ቁጥር ጨምሮ የሕብረቱ [አውሮፓ] አባል አገራት ተጨማሪ ዕዳ ይሆናሉ በሚል ነው። ወደ አውሮፓ ከሚጓዙ የአፍሪቃውያን ስደተኞች አብላጫው መነሻቸው ከአፍሪቃ ቀንድ ነው። ጦርነቱ ተራዛሚ ከሆነ ከእስካሁኑ የበለጠ ስደተኛ ያጠለቀልቀናል የሚል ስጋት ይዘው ጥዋት ማታ ድርድር እያሉ በማላዘን ላይ ናቸው።
የፌዴራሉን መንግሥት ሕግ የማስከበር ዘመቻ በለሆሳስ ከደገፉትም ሆነ አሳስቦኛል በሚል ካለፉት የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ አካላት ጋር የአውሮፓ ሕብረት በአንድ ነገር ይስማማል ፦ ጦርነቱ መራዘም የለበትም! በፍጥነት ተቋጭቶ ወደ ኖርማላይዜሽን ተመልሶ ማየት ይፈልጋሉ።
ይህ ጦርነቱ በሚፈጥረው መፈናቀል የተሰጋውን የስደተኞች ቁጥር ወደ 0 % ያወርደዋል ብለው ያምናሉ። እነዚህን ነጠብጣቦች ስናገናኛቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ቁማር ስለመሳካቱ እንረዳለን። ይሁን እንጅ ለፌዴራሉ መንግሥት ጊዜ ‘ጠላት’  ሆኖ ይታያል። ከሃዲው ቡድን ጊዜ ባገኘ ቁጥር ሰብዓዊ ቀውሱ እየከፋ ስለሚሄድ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በኩል እየታዬ ያለው የይስሙላ ጫና ወደ እውነተኛ ግፊት ሊቀየር ይችላል። በአፍሪቃ ቀንድ የተለያዬ ፍላጎት ይዘው የተሰለፉ የክፋት ተፎካካሪዎች  (Bitter Rivals) ሚና ይዘው እጃቸውን ሊያስገቡበት ይችላሉ። ውጊያው ተራዛሚ ከሆነ ይህ የማይቀር ነው። ሶማሊያ ላይ የተፈራው የአልሸባብ ማንሰራራት ኢትዮጵያ ውስጥ በትግረኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሊገለጥ ይችላል።   እናም የተከዜውን ድል በፍጥነት አሻግሮ ራያ ላይ መድገም የግድ ይላል። በጊዜ የለንም መንፈስ መገስገስ  ብቸኛውፃ አማራጭ ነው። ከማናችንም በላይ ይህ ለትግራይ ተወላጆች የብስራት መንገድ ይሆናል። ነጻነቱ ለነሱም ነውና!!
፬ አንባቢ ሆይ ምን ትፈልጋለህ? 
ብረት አከሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባቡር ፍጥነቱ ሃዲዱ ከሚሸከመው በላይ ሆኗል። የሰሜኑ እቡይ  የባህሪ ውክልና ከታሊባን ወደ ታሚል ታይገር ስለመዞሩ በቂ ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው።
~
ይህ ወቅት ለመጭዎቹ ከ 50-100 ዓመታት አገራዊና ቀጣናዊ የይዘት ለውጦች የሚታዮበት መሆኑን እያሰላሰልን፣ ለምንታመንለት የሕዝባችን ‘ኮዝ’ አለን!! ከመቸውም ጊዜ በላይ ጊዜው ሕዝባዊነትን የሚጠይቅ ነው።
ጥቂት ሠዓታት ረፍት አለንና፣ አንባቢ ሆይ በምን ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ትፈልጋለህ? ያው ከሃዲውን ቡድን በተመለከተ ከሰጠነው ትንተና፣ ካስነበብናቸው የቢሆን ዕድሎች የጎደለ/የከሸፈ አለመኖሩን መስካሪው ብዙ ነው ብንል ግነት ያለበት አይመስልም።
ከምንም በላይ መንግሥት በዚህ ሊንክ ላይ 
 
 
የቀረበውን ጥቆማ ተቀብሎ ቢሆን የሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው አያሌ መስዋዕትነት ክሱት ባልሆነ ነበር። 
የሆነው ሆኖ ዛሬም ሆነ ነገ ሕዝባዊ ውግንናችን ጠብቀን  ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅመውን፣ የፀጥታና የሴኩሪቱ ጉዳዮችን እናደርሳለን።
ለሁሉም አንባቢ ምን ይፃፍልህ? አጠቃላይ ስሜቱን አንብበን የምንለው ይኖረና።
Filed in: Amharic