>

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞከራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ   

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞከራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ   


ህወሓት ለ27 ዓመታት ዜጎችን በብሄር ከፋፍሎ የሀገሪቱን ንብረት እና የህዝቡን አንድነት ሲያዳክም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በህዝባዊ አመጽ ከመንበረ ስልጣኑ ተገፍቶ መቀሌ ከመሸገ በኋላም በርካታ የእኩይ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡ በሀገር መከላከያ በሰሜን እዝ ላይ የፈፀመው ማንነትን መሰረት ያደረገ አስነዋሪ ድርጊት ዘመን የማይሽረው አሳፋሪ የታሪክ ጠባሳ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ፓርቲያችን ይህን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ ያወግዛል፡፡ ታዲያ መንግስት ህግን ለማስከበር እርምጃዎችን ሲወስድ በጅምላ ብሄርን ያማከለ  አድሏዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳይፈጽሙ ፓርቲያችን ማሳሰብ ይወዳል፡፡ በማናችውም ጊዜ በሚወስዱ እርምጃዎች ንጹሀን ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከወንጀለኞች ጋር ተዳብለው የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ፓርቲያችን በጽኑ ማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዘ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዜጎቸ በነጻነት የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብቶች እየተሸራረፉ ነው፡፡ ወንጀለኞች ከሃገር እንዳያመልጡ ከፍተኛና ጥብቅ ቁጥጥር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ነገር ግን በዚህ መሃል ዜጎች በብሄራቸው ምክንያት ህጋዊ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዳይገፈፍ ፓርቲያችን ያሳስባል፡፡
የዛሬ 20 ዓመት ህወሃት መራሹ መንግስት በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት በኤርትራውያን ላይ የፈጸመው ግፍ መቼም አይዘነጋም፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ ግፍና በደል ባልሰሩ ዜጎች ላይ በደል እንዳይደርስ ፓርቲያችን በድጋሚ ያሳስባል፡፡
Filed in: Amharic