>

"የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ በቀጥታ ተሳትፏል!!!"  ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) - ኢዜአ

“የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ በቀጥታ ተሳትፏል!!!” 

ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)
ኢዜአ

* ወሓት በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያመረተውን የኤርትራ ሰራዊት መለዮ ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች አድርጎ ሕዝቡን እያደናገረ ነው”
ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥት መካከል አየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል ሲሉ የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ተናገሩ።
የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት ግን በትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት በኩል የቀረበውን ክስ ሐሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ፕሬዚዳንቱ በዛሬው ዕለት ህዳር 1/2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ከፍተኛ ድብደባ ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።
“በትናንትናው ዕለት የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመወገን በሁመራ በካባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈፅመዋል” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በዛሬው ዕለት ድንበር ጥሰው በባድመ በኩል በመግባት ጦርነት ከፍተዋልም ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ያከሉት ደብረፅዮን የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ ተሳታፊ መሆን፣ ጦርነቱን “ወደተለየ ምዕራፍ አሸጋግሮታል” ብለዋል።።
“አሁንም ተመልሰን ወደዚህ ጦርነት መግባታችን ያሳዝናል። ባለፈው ይብቃ- ብለን ነበር። ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግረናል። ትግራይ ላይ ትልቅ ክህደት ተፈጽሞባታል” ብለዋል።
“ኤርትራውያን ይሄ ሁኔታ እንዳይፈጠር ብዙ ጥረት አድርጋችኋል። አመስግነናል። አሁንም እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ ከዐብይና ከአሃዳዊ ኃይሎች ጋር በመወገን የጀመርነውን ራሳችንን የመከላከል ዘመቻ ሊያከሽፍ መጥቷል። ይህንን ያደረገው በጦርነቱ የኛን የበላይነት አይቶ ነው” በማለትም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በጦርነቱ የኤርትራ ሠራዊት አባልት በቀጥታ ተሳትፈዋል ስለመባሉ ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።
ሆኖም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ይህንን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትን ክስ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
“ይሄ ውስጣዊ ግጭት ነው። እና የግጭቱ አካል አይደለንም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በስልክ እንደገለጹለት ሮይተርስ ዘግቧል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት በኤርትራ ወታደሮች ጥቃት ስለመፈጸሙ በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የተሰጠው መግለጫ “ፍፁም ሐሰት” መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ አቅጣጫዎች ዘመቻ እያካሄደ የሚገኘው የፌደራል መንግሥት ሠራዊት በምዕራብ የሚገኘውን የሁመራ አየር ማረፊያን መቆጣጠሩን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ማክሰኞ ጠዋት ዘግበዋል።
“የሕወሓት ጁንታ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያመረተውን የኤርትራ ሰራዊት መለዮ ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች አድርጎ ሕዝቡን እያደናገረ ነው”
ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
“ሁመራና አካባቢው ሙሉ ለሙሉ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ውሏል” ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አስታወቁ።
ሰራዊቱ በአሁኑ ሰዓት ከሁመራ እስከ ሽራሮ ያለውን ቦታ በማጥቃት የተለያዩ ስፍራዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ የእርዳታ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተነጋግረው ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የህወሃት ጁንታ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትን መለዮ በማዘጋጀት ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች በመግለጽ ህዝብን እያደናገረ እንደሆነም ገልጸዋል።
በዚህ የተቀናበረ ድራማ ህዝቡ ሳይታለል ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
Filed in: Amharic