>
5:13 pm - Sunday April 18, 4021

የመጠፋፋትም፣ አብሮ የመኖርም ታሪክ አለን! (አሰፋ ሀይሉ)

የመጠፋፋትም፣ አብሮ የመኖርም ታሪክ አለን!

አሰፋ ሀይሉ

 

  – የጥፋቱን ታሪክ ሳይሆን፣ የሠላሙን ታሪክ ብንደግመውስ?!
የ60ዎቹ ሀገርና ወገኑን ወዳድ ጀግና ትውልድ፣ ሻዕቢያና ሌሎች የኤርትራ አማጽያን፣ ከእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንገነጠላለን፣ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ነች፣ የሠለጠነን ቅኝ ገዢ (ጣሊያንን) አባረን – ባልሠለጠነ ቅኝ ገዢ (በኢትዮጵያ) አንገዛም እያሉ፣ መሣሪያ አንስተው የኢትዮጵያውያንን ደም በግልጽና በስውር እያፈሰሱም በነበረበት ወቅት እንኳ፣ ታሪክ የማይረሳውን፡-
‹‹በኤርትራ ሕዝብ ላይ አንዘምትም!›› 
የሚል – ለዘለዓለሙ የኢትዮጵያውያንን ታላቅ ማንነት ሲመሰክር የሚኖር መፈክር አንስተው ጩኸታቸውን አሰምተዋል፡፡ ዛሬ ተረኛ ገዢ ነኝ ብሎ በነሞቲ ቢያ መጽሀፍ እያፃፈ፣ በአደባባይ አዋጅ እያስነገረ፣ አንድን ህዝብ ‹‹ነፍጠኛ›› ብሎ ፈርጆ ሰበርናቸው፣ ሰባበርናቸው እያለ በአደባባይ እየፎከረ፣ ያልታጠቁ ንጹሃንን በማረድ ጉልበቴን እዩልኝ ስሙልኝ እያለ ያለውን፣ ጦርሰራዊቱን፣ የመንግሥትን መዋቅር ሁሉ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ፣ የመጨረሻ የተረኛ አገዛዜ ተቀናቃኞቼ ይሆናሉ ያላቸውን ወያኔዎቹን፣ አብሯቸው ከነቆመው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ላይ፣ ከሌላ ጎረቤት ሀገር (ከኤርትራ) ጋር ተሻርኮ፣ በመቶ ሺህዎች የሚገመት ጦርሠራዊትና የጦርመሣሪያዎችን አሰልፎ – በገዛ ወገኖቻችን ላይ ጦርነት ሲያውጅ – ይህ ትውልድ ዳግም እንደቀደመው ትውልድ፡-
‹‹በወገኖቻችን ላይ አንሰለፍም!››፣ 
‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ አንዘምትም!›› 
ብሎ ካልጮኸ ታላቅ ታሪካዊ ስህተትን እያኖረ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ የአማራው ህዝብ – ወያኔ በትዕቢት ተወጥሮ የነጠቀውን መሬት በኃይል ለማስመለስ ከመነሳሳቱ በፊት የሚቀድሙ ብዙ መንግሥታዊ ሂደቶች ነበሩ፡፡ የቄሮው መንግሥት አንዳቸውንም ሲሰራ አልታየም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን እንደሚያመጣ አይታወቅም፡፡
ጉዳዩ ዋና ጭብጥ ሆኖ በሁለቱ ህዝቦችና በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ብዙ ሂደቶችን አልፎ መወሰን ሲገባው፣ አሁን የአብይ አህመድ መንግሥት ኦሮሚያ በሚባለው እና መሣሪያ (የመከላከያን ዕዞች መሣሪያ ሳይቀር) እስካፍንጫው ባስታጠቀው ክልል በግፍ እና በገፍ በመቶዎች እየታረዱ ባሉ የአማራ ተወላጆች ላይ በሚደርሰው ጥቃት የተነሳ የአማራ ህዝብ ሆ ብሎ ከመነሳቱ በፊት – አጀንዳ ለማስቀየር – እና የነጠፈበትን የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት – በአማራ ህዝብ ደካማ ጎን – እና በኢትዮጵያ ህዝብ የዓመታት ቂም ላይ በመቆመር – ከውጪ ኃይል (ከሻዕቢያ) ጋር ተባብሮ – የአማራም ሆነ የሌላው ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ እንደ ውጪ ጠላት በጋራ እንዲዘምት ማድረጉ – ታሪክ ይቅር የማይለው ሸፍጥና ክህደት ነው፡፡ ባንዳነትን ስንጸየፍ ኖረናል፡፡
ከወያኔዎች ታሪክ አሳፋሪው ባንዳነቱ ነበር፡፡ የአብይ አህመድ ኦነጋዊ ኃይል ትናንትም ከውጪ ኃይል ጋር ተባብሮ ሀገራችንንና ህዝባችንን ሲወጋ ነበር፡፡ ዛሬም ከውጪ ኃይል ጋር ተባብረን – ኢትዮጵያዊነታቸው ላይ እስካሁኗ ደቂቃ ጥያቄ ባላነሱት የገዛ ወገኖቻችንን ላይ እንድንዘምት አድርጎናል፡፡ እንዴት ወደ ጦርነት ሊያስገቡን ቻሉ? ለምን እርስ በርስ ያጣሉናል? የሰሜኑን የፖለቲካ ማዕከልነት አምክነን አዲስ የኩሽ አጋርነት የወለደው ደቡባዊ ፖለቲካ እናራምዳለን ሲሉ በአደባባይ ከሚቀላምዱት ጋር ስናስተውለው የዚህ ጦርነት ዓላማ ግልጽ አይደለም ወይ? እውነት ለኢትዮጵያ አስበው ነው? ለአንድነቷ ተጨንቀው ነው?
የአማራ ህዝብ ነገና ከነገ ወዲያ የወያኔ ሽማግሌዎች ሲያልፉ፣ የትግል አጋር ከሚሆነው፣ ኢትዮጵያን ማገርና ምሰሶ ሆኖ አብሮት ካቆመውና ከሚጠብቀው ከወንድሙ የትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ ለአንድ ሀገር የማይሰለፍበት ምክንያት የለም! የቁማርተኞቹ ዓላማ ገዢና ቅኝ ገዢ የሚሉትን የሰሜን ኢትዮጵያ አንዱን ክንፉን መምታትና ማኮላሸት ነው፡፡ በዚህ ሩቅ ያለመ፣ እና በውጪ ኃይሎችና ኢትዮጵያን በሚጠሉ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች አብሮ እየተጎነጎነ እዚህ በደረሰ እና  ባደረሰን ፀረ-ኢትዮጵያ ሴራ ውስጥ – ንጹሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያስበው ቀስ በቀስ እየተነዳ – ይኸው ቅልጥ ወዳለ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ ይኸው ኢትዮጵያን አልፈልግም ብሎ ከተገነጠለው ከሻዕቢያ ጋር ወግነን – ከነክህደቱምና ከነባንዳዊ ታሪኩም ቢሆን – ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር ትንሳዔውንም ሞቱንም ያደረገውን የገዛ ወገናችንን የትግራይህን ህዝብና ኃይል እየተዋጋን እንገኛለን፡፡ እንዲህ ያለ ወራዳ የባንዳ ታሪክ ፈጻሚዎች እንድንሆን ገፍተው ገፍተው እዚህ አድርሰውናል፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ነው ለነገ መንቃት፡፡ ከሆነ በኋላ ለፈሰሰ ውሃ፣ ከዘገየ በኋላ ለፈሰሰ ደም መቆጨት ዋጋ የለውም፡፡ አሁን ወያኔ ጥሩ ቅጣት አግኝታለች፡፡ መጥፊያዋ ከነበረው ጊዜ (ከሶስት ዓመት በፊት) እንድታንሰራራ አድርጎ ዛሬ ላይ ለተገኘችበት ደረጃ ያደረሳት ማን እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ያለፈ አይመለስም፡፡ የፈሰሰ አይታፈስም፡፡ ከአሁን በኋላ አዲስ የክህደትና የባንዳነት ታሪክ የምንከፍትበት ጊዜና የታሪክ ምዕራፍ መኖር የለበትም፡፡ ወያኔን መደምሰስ፣ አብሮት ያለውን ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊ ወገናችንንም መደምሰስ ማለት ነው፡፡ ሰው እያረዱ የነበሩትም ያሉትም ኦነጎቹ ናቸው፡፡ ወያኔዎቹ ሰው ሲያርዱ አልሰማንምም አላየንምም ነበር፡፡ አሁን የኦሮሞዎቹን እርድና የሰው ዘር ጭፍጨፋ ለማደባበስና ሁሉንም ሃጢያት እንደተለመደው በወያኔ ላይ ለማላከክ – ወያኔዎቹ ዘር መጨፍጨፋቸውም እየተነገረን ነው፡፡ ከሆነ ይጣራ በዓለማቀፍ ገለልተኛ አጣሪ፡፡ የሚገባቸውና የተሳተፉት ህጋዊ ዋጋቸውን ያግኙ፡፡
እነሱ ብቻ ግን አይደሉም፡፡ የአማራን ህዝብ በጅምላ ሲያርዱና ሲያሳርዱ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ተብዬው ሰዎችና አራጆችም በተመሳሳይ ዓለማቀፍ አጣሪ ወንጀላቸው ተጣርቶ ለፍርድ ሊቀርቡና ቅጣታቸውን ሊያገኙ ይገባል፡፡ አለዚያ የአማራው ህዝብ በዚህ በኩል በእርድ፣ በዚያ በኩል በጦርነት እየተባለ በዚህች ሀገር ላይ እንደ ጦስ ዶሮ በያቅጣጫው ደሙ እንዲፈስ እየተሰራ ያለው ዘግናኝ ሀገራዊ ድራማና ሴራ አሁኑኑ ማቆም አለበት፡፡
ወያኔንም ሆነ፣ አንድ ነኝ ብሎ አብሮት የቆመውን የትግራይ ህዝብ ማጥፋት (ወይም በወታደራዊ ቋንቋ ‹‹መደምሰስ››) የአማራም ሆነ የሌላው ኢትዮጵያዊ ህዝብ ዓላማም ግብም አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ወያኔን ላጠፋ ነው የተነሳሁት ያለ አካል ሄዶ ራሱ ያጥፋው፡፡ የትግራይ ህዝብ ጠላቴ ነው ያለ አካል ካለ ራሱ ሄዶ ይቀጥቅጠውና ይፍጀው፡፡ የአማራ ህዝብ፣ እና የቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከገዛ ወገኑ ጋር የሚያጣላው ጉዳይ – ከእንግዲህ በኋላ – ከንግግርና ከሰከነ ውይይት ያለፈ አጀንዳ እንደማይሆን – ማንም ዓይኑን የጨፈነ አያጣውም፡፡
በተረፈ ግን – አንዲትን ክልል እና ያለ ኮሽታ የሚያስተዳድራትን አካል (ወያኔም ሆነ ማን) – የመላ ሀገሪቱን የጦር ሰራዊት አዝምቶ በማይመጣጠን ጉልበት ከመቀጥቀጥ አልፎ፣ ጭራሽ የጎረቤት ሀገር ጦር ጭምር አዝምቶ – ትክክልም ይሁኑ ስህተት – በጉልበት አንንበረከክም ባሉ ወገኖቻችን ላይ የመጨረሻውን እልቂትና ጥፋት ለማድረስ መቋመጥ ከጤነኛም፣ ከሀገር ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ከዚህ በኋላ ከወያኔዎች ጋር በሚደረግ ድርድር የበላይነቱን የሚይዘው ወገን የትኛው እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እዚህ ድረስ መቋቋም ማሳየታቸው ራሱ አንድ ነገር ሆኖ፣ ከዚህ በኋላ ግን ‹‹ካላጠፋናቸው አንመለስም›› ብሎ መድረቅ – ኢትዮጵያዊ ታሪካችንን የሚያጠለሽ፣ አዲስ ባንዳዊ ታሪክ የሚያስፅፍ፣ እና ለነገ መጪ ትውልድ ትናንት ካደረው ቂምና ቁርሾ በላይ ጨምረን ማውረስና ለነገ የግጭት ረመጥን አኑረን ማለፍ ነው፡፡ ስለዚህ፡-
‹‹ጦርነት በቃን!››፣ 
‹‹በትግራይ ህዝብ ላይ አንዘምትም!›› 
የማለቻው ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው፡፡ ወገንን ከወገን አጥፊ፣ እና ሀገርን አውዳሚ የሆነውን የወገን ጦርነት በቃ የማለቻ ጊዜው አሁን ነው፡፡ አሊያ ግን መቼም አይደለም፡፡ ብዙው ሰው ወደ ቀልቡ ከተመለሰ – ከብዙ ቀረርቶና ፉከራዎች ባሻገር አስተውሎ እንደሚረዳው – በአሁኑ ሰዓት ወዶም ሆኖ ተገዶ ወደ ድርድር የሚመጣ ጠላትነትን ተላብሶ የቆመ ኃይል እንጂ፣ የምናጠፋው እውነተኛ ጠላት የሆነ ህዝብ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ህዝብና ህዝብ መቼውኑም ጠላት ሆኖ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያውያን ቢፋጩም ቢቆራቆዙም መልሰው ለመታረቅና ይቅር ለመባባል የሚቀድማቸው የለም! ይህን ታሪካችንን የሚቀይር ምንም ምድራዊ ሀቅ የለም፡፡
ለሠላም ሥፍራ የሌለው፣ በጦርነትና በጦርነት ብቻ የተለከፈ አዕምሮ ጤነኛ አዕምሮ አይደለም፡፡ ካለ ጦርነት ሞቼ እገኛለሁ ማለት፣ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀልነት ነው፡፡ ስለነገው የማያስብ አህያ ብቻ ነው፡፡ ሳይመሽብን፣ እና የወገናችን ደም በሺህዎች ሳይፈስ፣ የሀገር ሀብትና ንብረት ሳይወድም፣ አዲስ ደማቅ የባንዳነት ታሪክ ሳናፅፍ በፊት ጦርነቱ ይብቃን! ሠላምን ሁላችንም ከልባችን እንሻ! ሁላችንም አሁኑኑ ለሠላም ዘብ እንቁም! ለሀገራችን ስለሚበጃት አኳኋን ሁሉም ወገን ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ የነገውን ትውልድ እያሰበ ይምከር፡፡ ይህ እንዲሆን ሁላችንም በጋራ ልባችንን አጠንክረን እንነሳ!
ሀገር የምትቆመው እንዲህ ነው፡፡ ህዝብ የሚፀናው በእንዲህ መንገድ ነው፡፡ ወገን ከወገኑ ጋር የሚኖረው በዚህ ሄድ መለስ የማለት – ላለመጨከንና ላለመጨካከን በሚደረግ የወንድማማቾች ግብግብ ነው፡፡ በመጠፋፋት አይደለም፡፡ አንዱ ሌላውን በመደምሰስ ፈጽሞ አይደለም፡፡ በመነጋገር፣ በመደማመጥ፣ በመተዛዘንና ያንን ይቅር ለእግዜር፣ ይሄን እስቲ በዚህ ቢሆን… በሚል ጥበብ ጭምር ግን ነው፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡
ኢትዮጵያ በአይበገሬ ልጆቿ ኅብረት፣ የተባበረ ክንድ፣ እና ጥበብ፣ ደምቃና ታፍራ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic