>

የ‹‹ጁንታ›› ምሥጢሩ ምንድን ነው? (ከይኄይስ እውነቱ)

የ‹‹ጁንታ›› ምሥጢሩ ምንድን ነው? 

ቀሪውን ሕወሓት ንጹሕ ለማድረግ የታለመ ነው?

ከይኄይስ እውነቱ

ሰሞነኛው ‹ጦርነት› በዐቢይ አገዛዝና በወያኔ/ሕወሓት ከተጀመረ በኋላ አገዛዙ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን በስሙ ከመጥራት ይልቅ ጁንታ የሚል ቃል መጠቀምን መርጧል፡፡ የአገዛዙ ደጋፊዎችና ያሰማራቸው የሜዲያ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሕዝብም ይህንን ቃል በጭፍን ሲያስተጋባ ይደመጣል፡፡ እስከ መቼ በስሜት እንነዳለን፡፡ አገዛዙ ለምን ይህንን ቃል መረጠ? ዓላማው ምንድን ነው? ከአገዛዙ በተቃራኒ በ‹ጦርነቱ› የተሰለፈው ሕወሓት እንደ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጉልበትም ቢሆን የትግራይ ክ/ሀገርን የሚያስተዳድረው ወያኔ/ሕወሓት ነው፡፡ እንደ አገዛዙ አስተሳሰብ ከወያኔ ድርጅት (ሕወሓት) ጥቂት ስብስቦችን/ግለሰቦችን ብቻ መርጦና ‹ጁንታ› በማለት የ‹ጦርነቱም› ዓላማ ይህን ቡድን ብቻ በቁጥጥር ሥር ለማዋል መሆኑን ይናገራል፡፡ ለምን?

በቅድሚያ ጁንታ የሚለው ቃል ከስፓኒሽ ቋንቋ በውሰት የተወሰደ ሲሆን፣ ስብሰባ÷ ኮሚቴ/ደርግ ማለት ነው፡፡ አመጣጡም እአአ በ1808 ናፖሊዎን በስፔን ላይ ያደረገውን ወረራ ለመቋቋም በብሔራዊና አካባቢያዊ ደረጃ የተደራጀ ቡድን መጠሪያ ሆኖ ነው፡፡ አሁን ባለው አጠቃቀሙ የሚከተሉትን ሃሳቦች ይገልጻል፤

  1. አብዮትን ተከትሎ የመንግሥትን ሥልጣን በመቆጣጠር አገርን የሚመራ ወታደራዊ ቡድንን ይመለከታል፤ ወታደራዊ ጁንታም ተብሎ ይጠራል፡፡
  2. በስፔን እና በላቲን አሜሪካ አገራት የአስተዳደር ምክር ቤትን ወይም ሕግ አውጪ አካልን ይመለከታል፡፡
  3. የወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ገዢ መማክርትን ይመለከታል፡፡
  4. የፖለቲካ አሻጥር ለመሥራት የተሰባሰበ ቡድን በተለይ የመንግሥት ግልበጣን ተከትሎ የተደራጀ ወታደራዊ ቡድንን ይመለከታል፡፡
  5. በተለይ በስፔን ሸንጎ፣ የዳኝነት አካል፣ ምክር ቤት ማለትም ይሆናል፡፡ (ምንጭ፤ ኢንተርኔት)

ከነዚህ ሃሳቦች በመነሳት የዐቢይ አገዛዝ ቃሉን በተራ ቊ.4 በተመለከተው ትርጕም (የፖለቲካ አሻጥር ለመሥራት የተሰባሰበ ቡድን) የተጠቀመበት ይመስላል፡፡ ሕወሓት ግን ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት በጉልበት ሲገዛ የነበረ፣ ባለፉት 3 ዓመታት ገደማ ደግሞ ለማዕከላዊው ‹መንግሥት› አልታዘዝም ብሎ የትግራይ ክ/ሃገርን በጉልበት እያስተዳደረ ያለ የአሸባሪዎች ቡድን ነው፡፡ በእኔ አረዳድ በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት አለ ከተባለ የዐቢይ አገዛዝ የሚመራው አንድ ማዕከላዊ መንግሥት እንጂ የ‹ክልል መንግሥታት› የሚባል ነገር የለም፡፡ በየግዛቱ ያሉት የግዛት አስተዳደሮች እንጂ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ለወደፊቱም በኢትዮጵያ የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ተቀዳዶ አዲስ ሕገ መንግሥት ሲጻፍና የጐሣ አገዛዝ ሥርዓቱ ሲቀር፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዐላዊ አገር የሚኖራት አንድ ማዕከላዊ መንግሥት እና የክፍላተ ሀገራት አስተዳደሮች እንጂ መንግሥታት ይሆናሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡ 

ለማንኛውም ወደ ቀደመ ሃሳባችን ስንመለስ፣ ሕወሓት/ወያኔ ኢሕአዴግ በሚባለው ግንባር የጐሣ ፖለቲካ እና ‹ክልል› የሚባል በቋንቋና ጐሣ ላይ የተመሠረተ መዋቅር ተክሎ፣ የአማራ ሕዝብንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ጠላት አድርጎ ፈርጆ የተነሳ፣ ኢትዮጵያን ሲያምስ ሲያተራምስ የኖረ የወንጀለኞች ስብስብ ነው፡፡ የ‹ጦርነቱ› ዓላማ ይህንን ስብስብ ከፋፍሎ ከውስጡ ጥቂት ግለሰቦችን መርጦና ‹ጁንታ› የሚል ስያሜ ሰጥቶ በመምታት የቀረውን እሱ ባደራጀውና ‹ብልጽግና› በሚለው የጐሣ ድርጅት ውስጥ አስገብቶ ለማስቀጠል የሚደረግ ሙከራ ከሆነ አሻጥረኛው ቡድን የዐቢይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ሊለው ይገባል፡፡ በማይካድራ በንጹሐን ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ፣ በሰሜን ዕዝ አማራ በሆኑ የሠራዊቱ አባላት ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ የጦር ወንጀል፣ ባጠቃላይ ሕወሓትን እንደ አሸባሪ ድርጅት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ውድ ሕይወታቸውን ለኢትዮጵያ ብለው በጦር ግንባር እየገበሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኃይሎችን መሥዋዕትነት ከንቱ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ የአገዛዙ ድብቅ ዓላማ ይህ ከሆነ የሚያቀባብረን አይደለም፡፡ ጁንታ የምንለው ሕወሓትን ባጠቃላይ ከሆነ (የጐሣ ጁንታ መሆኑ ስለማይካድ) ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

ይሁን እንጂ የአገዛዙ ዓላማ ወያኔን ለራሱ አስገዝቶ አገር አጥፊውን የኦሮሙማ ፕሮጀክት ለማስቀጠል ከሆነ አገራችንን ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ እልቂት ውስጥ እንደሚከታት አልጠራጠርም፡፡ በየትኛውም መልኩ የዚህ ‹ጦርነት› ፍጻሜ ሕወሓት የሚባል ድርጅትን በመደምሰስ፣ ከግብር ወንድሙ ኦነግ ጋር በሽብርተኝነት ተፈርጆ ለፍርድ እንዲቀርብ ማድረግ ለመሆኑ አገዛዙ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ ቋንቋ መግለጽ ይኖርበታል፡፡ የእስካሁኑ መግለጫና ፕሮፓጋንዳ ይህንን አያመለክትም፡፡ ሕወሓትን አንበርክኮ ‹ብልጽግና› በሚለው ማጭበርበሪያ ውስጥ አባል በማድረግ ‹‹ኢሕአዴግ›› ቊጥር 2ን ለመፍጠር የታሰበ ከሆነ የዐቢይ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከነዚህ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ባንድነት ግልጽ ጦርነት እንዳወጀ እንቈጥረዋለን፡፡ 

ወገኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ብለህ ጁንታ ጁንታ እያልህ ከማስተጋባት የዐቢይ አገዛዝ ፍላጎትን በውል ልታውቅ/ልትረዳ ይገባል፡፡ ከአብራክህ የተከፈሉ ልጆች በጦር ግንባር እየተሠዉ ያሉት ለምን ዓላማ ነው የሚለውን በማስተዋል ልትከታተል ይገባል፡፡ በተለይም በማንነትህ የዘር ፍጅት እየተፈጸመብህ ያለው የአማራው ሕዝብ፡፡ አሁን ካልባነንህ መቼም ሊሆን አይችልም፡፡ ‹ጦርነቱ› ሕወሓትን የማያጠፋ እና ከኦነግ ጋር በሽብርተኝነት የመፈረጅ ውጤት ከሌለው ለሥልጣን ጥመኞች መሣሪያ መሆንህን ልታውቅ ይገባል፡፡ ባንፃሩም በሕወሓት በኃይል ወረራና የዘር ማጥፋት ተፈጽሞ የተወሰዱ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ጸለምት እና ራያ ግዛቶች ዐቢይ የወሰንና ድንበር ኮሚሽን የሚለውና ለፖለቲካ ፍጆታ ያቋቋመው የፌዝ ኮሚሽን የነዚህ ግዛቶችን ጉዳይ ለማየት በሕግ ሥልጣን እንደሌለውና ከተከዜ ወዲህ ‹ምዕራብ ትግራይ› የሚባል ግዛት አለመኖሩንም በሚገባ ተረድተህ የ‹ጦርነቱ› ውጤት እነዚህን ግዛቶች ለባለርስቶቹ ማስመለስ መሆኑን ሌላው ሁነኛ መለኪያ ልታደርገው ይገባል፡፡

ሦስተኛው ዐቢይ ‹ጁንታ› ካለው ቡድን ውጪ ያለው ሕወሓት ጋር  በራሱም ሆነ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚደረግ የ‹ድርድር› ሃሳብ በየትኛውም መመዘኛ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚያስገኘው ፋይዳ ስለማይኖር የሚደገፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የዐቢይ አገዛዝ እላይ የገለጽነው ግምታችን ትክክል ከሆነ ጥሉ ከሕወሓት ጋር ሳይሆን በውስጡ ካሉ ጥቂት ግለሰቦች ጋር በመሆኑ ‹የትግራይ ብልጽግና›ን አካትቶ ድጋፍና ሽፋን የሚያደርግለትን የኦሮሙማ ፕሮጀክት ማራመድ በመሆኑ፡፡ 

በአራተኛ ደረጃ የሚነሳው ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብትን በመዝረፍና ሕገ ወጥ የሀብት ዝውውር በማድረግ በኢትዮጵያ ኪሣራ ላይ የተቋቋሙትና የወንጀል ፍሬ የሆኑት የኤፈርት ድርጅቶች ዕገዳ እንደተደረገባቸው ዐቢይ ገልጾአል፡፡ ይህንን ጉዳይ ገና ከማለዳው ዐቢይ ወደ ሥልጣና በመጣ ማግስት ባገር ውስጥና በውጭ የምንገኝ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን ጠይቀናል፡፡ የዐቢይን አገዛዝ ትክክለኛ ገጽታ ካየን በኋላ መልስ እንደማናገኝና የወር ተራ ጉዳይ መሆኑንም ተረድተናል፡፡ አሁንም የተወሰደውን ርምጃ በበጎነት ብናየውም (ዓላማው በጠላትነት የተሰለፈውን የሕወሓት ኃይል አቅም ለማዳከም እንደሆነ ይገባናል)፣ መጨረሻውን ሳናውቅ  ከወዲሁ የምናጨበጭብለት ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሀ) የኤፈርት ሀብቶች ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀሙ በመሆናቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተወርሰው ለባለቤቱ መመለሳቸውን የሚያረጋግጥ፣ ለ) ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በወያኔ አገዛዝ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን የሚካሡበት፣ ሐ) ቀረው ሀብት ብሔራዊ ካዝና ውስጥ የሚገባበት፣ መ) በዝርፊያው ሕገ ወጥ ሞኖፖሊ ያቋቋሙ፣ ንቅዘትን ተቋማዊ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ አፓርታይድ የፈጠሩና ብሔራዊ ኢኮኖሚን ያኮሰመኑ አመራሮችና ግለሰቦች በአገር ኢኮኖሚና ጥቅሞች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች መጠየቃቸውን እና ሠ) አሁንም ተረኞች ነን በሚሉ ኃይሎች ተመሳሳይ አቅጣጫ እያቆጠቆጠ በመሆኑ ይህን ሊያስቀር የሚችሉ፣ ውሳኔዎች መወሰዳቸውን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ግን ምንም ዓይነት ዋስትና የለም፡፡ የዐቢይ አገዛዝ የኋላ ታረክ በተቃራኒው እንድናስብ የሚያስገድደን ይመስላል፡፡ አሁን ያለው አገዛዝ እንደ ሕወሓት የዘር መድልዎ የነገሠበት ላለመሆኑ በምድር ላይ ያለው ጽድቅ አያሳየንም፡፡ ምናልባትም ርግጡን ለመናገር የከፋ ይመስላል፡፡

ለማጠቃለል ከፍ ብለን የዘረዘርናቸውን አገራዊ ጥፋቶች ወያኔ ሕወሓት እንደ ድርጅት የፈጸማቸው ናቸው፡፡ ‹ጁንታ› የተባለው ተጠያቂ፣ ከፊሉ ሕወሓት ደግሞ ንጹሕ የሚባል ነገር የለም፡፡ በጋራና በተናጥል ውሳኔዎች ሁሉም በተሳትፎው መጠን ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ዐቢይ ባያደርገው እውነተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲመጣ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ባገርና በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀል እስከ መቃብር ተከትሎ ይሄዳል፡፡ የንጹሐን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርምና፡፡ 

ርእሰ ጉዳያችን ‹ጦርነት› እያካሄደ ያለውን ወያኔን የሚመለከት ስለሆነ እንጂ የእሱ የእጁ ሥራዎች የሆኑት (ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ደሕዴን እና ‹አጋሮቹ›) ድርጅቶች ባገራዊ ውድመቱ (በግድያና በዝርፊያው) እስከ አንገታቸው የተዘፈቁ በመሆናቸው ሁሉም በተሳትፎአቸው መጠን በግለሰብና በድርጅት ደረጃ ተጠያቂ መሆናቸውን በደማቁ ሳላሰምርበት አላልፍም፡፡

Filed in: Amharic