አዲስ አበቤ ማለት ይሄ ነው!!!
ታምራት ነገራ
* ዛሬ ላይ ማንም ነጠላ ብሄር እየተነሳ ” ለአዲስ አበባ እዚህ ደረጃ መድረስ ምክንያት እኔ ብቻ ነኝና ፤ …. የብቻዬ ንብረትም ነች ” ማለት አይችልም!! አዲስ አበባም ሆነ አዲስ አበቤነት ስሪታቸው የጋራ የሆነ ውህድ ፣ ህብረት ነው!!!
ማንም እየተነሳ አዲስ አበባና የልጆቿ ወኔ ላይ ሲለፋደድ ስናይ እርፍና ይዞን ዝም ብንልህ ፣ለአገር የመግደልም ሆነ የመሞት የተመሰከረ የወኔ ታሪክ ስለሌለን ለሚመስልህ አንት መደዴ ፣
ስማ ፣ አዲስ አበባ ማለት በግራዚያኒ ጭፍጨፋ 20,000 ልጆቿን ገብራ መልሳ ያንሰራራች ከተማ አገር ነች!
ስማ፣ አዲስ አበባ ማለት በ1966 ዩኒቨርስቲዎቿና ሃይስኩሎቿ የነቀነቁት አብዮት በዓለም እስከአሁን ድረስ የሚጠናላት ከተማ አገር ነች!
ስማ ፣ አዲስ አበባ ማለት በነጭ ሽብር በል በቀይ ሽብር ልጆቿ በየሰፈሩ የተጋደሉላት፣ የተጋደሉባት፣ የተገረፉባት፣የገረፉባት ዘልአለማዊ የትግል ሜዳ ናት።
ስማ፣ አዲስ አበባ ማለት ወያኔ ከተማዋን ከረገጠበት ቀን ጀምሮ በየቀኑ ልጆቿን በየሰልፉ በየአፈሳው የገበረች ጀግና ከተማ አገር ናት።
ስማ፣ ምርጫ 97 ላይ ወያኔን 100% የዘረረች የአገር ኩራት እውነትም ዋና ከተማ ናት!
ስማ ፣ አዲስ አበባ ማለት እንደ ቄሮ፣ ፋኖ ምናምን ያውም መለስ ከሞተ በኋላ ያውም በኦሕዴድ፣ብአዴን ካድሬ ድጋፍ ሆይሆይታና እገዛ ተደራጅተው ሳይሆን ልባቸውንና ፈጣሪያቸውን ብቻ ተማምነው ክላሽ በድንጋይ የገጠሙ አርበኛ ልጆች ያፈራች ከተማ አገር ናት!።
ዛሬ ላይ ማንም ነጠላ ብሄር እየተነሳ ” ለአዲስ አበባ እዚህ ደረጃ መድረስ ምክንያት እኔ ብቻ ነኝና ፤ …. የብቻዬ ንብረትም ነች ” ማለት አይችልም!! አዲስ አበባም ሆነ አዲስ አበቤነት ስሪታቸው የጋራ የሆነ ውህድ ፣ ህብረት ነው!።
አዲስ አበባ የበለፀገችው ከከርሰ-ምድሯ በፈለቀ ነዳጅ ፣ ቆፍራ ባወጣችው አልማዝና ወርቅ ወይም ከሰማይ በወረደላት መና ሳይሆን አዲስ አበቤ እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላባቸውን ጠብ አርገው ባፈሩት ሐብት ነው። ከዚህ በመነሳት አዲስ አበባችን የሁሉም ሕዝብ የተጋድሎ ፣ የሐብትና የታሪክ አሻራ ውጤትም ናት ።
ከዚህ አልፎ መላው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለአለም ያበረከቷትየፖለቲካና የዲፕሎማሲም ማዕከል ናት።
በዚህ አጋጣሚ አዲስ አበባ አዲስ አበባ እንጂ በረራም ፊንፊኔም አይደለችም!!!
ልጆቿም አዲስ አበቤ ዘብሔረ ኢትዮጵያ ይባለሉ!!!