>
5:13 pm - Saturday April 19, 3090

በሁመራ ጉዳይ… ከየትኛ የስክነት ደረጃ የStatus Quo እንነሳ? (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

በሁመራ ጉዳይ… ከየትኛ የስክነት ደረጃ የStatus Quo እንነሳ?

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

 

በምዕራብ ትግራይ ተብሎ ተከልሎ የነበረው መሬት፤ አሁን በመከላከያ እና በልዩ ኃይል አማካኝነት ከህወሃት አገዛዝ ነጻ ሲወጣ፤ የነዚህ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼን እንባ እና ሃዘን ስለማውቀው፤ “እንኳን ደስ አላቹህ” ለማለት ስልክ የደወልኩላቸው ሰዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ የትላንቱን ድካም እና ጭንቀት ረስተው፤ የድል ምስራች ጫፍ ላይ ደርሰው ሌላ አለም ውስጥ ሆነው አገኘኋቸው። እናም “ምነው ምነው የትላንቱ ተረሳ?” በሚል ለስሜን ቤጌምድር ሰዎች ይቺን ማስታወሻ ለመጻፍ ወደድኩ። እናም አሁን እያወጋን ስላለው ወግ ስንል፤ ከተከዜ ወዲያ ያለውን ትግራይ እና ከተከዜ ወዲህ ያለውን የሁመራ መሬት በሃሳብ መቃኘት የግድ ያስፈልጋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰዎችን ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ያገኘሁት፤ ኮለምበስ ኦሃዮ በነበርኩበት ወቅት ነው። በብዙ ነገሮች ላይ አብረን በመስራታችን፤ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ አቀረቡኝ… ቆይተው ደግሞ በጉዲፈቻ እንዳደገ ሰው፤ የወልቃይት ቤተሰብ አድርገውኝ፤ በሃዘን እና በደስታ… አንድ ማዕድ አብረን ቆርሰናል። አብረን ከመቆየት ብዛት አንድ የተማርኩት ነገር ቢኖር፤ የዚያን አካባቢ ህብረተሰብ ጽናት ነው። ወልቃይት ጠገዴዎች ለጠላት የማይንበረከኩትን ያህል…. ለወደዳቸው ደግሞ ልባቸውን ይሰጣሉ። እነሱ ግን ከመውደዳቸው ብዛት…. ልባቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ልብሳቸውን፣ ገንዘባቸውን ሰጡ። በመጨረሻም ህዝባቸውንም መሬታቸውንም አጡ።
እውነት እውነት እላችኋለሁ። እነዚህ ሰዎች በደርግም በኢህአዴግም ዘመን ከፍተኛ በደል የደረሰባቸው ግፉአን ናቸው። በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ አይተውና ሰምተው የማያውቁት ግፍ እና በደል ነው የደረሰባቸው። ሴቶች እህቶቻቸውን በወያኔ ተቀምተዋል፤ ወንዶቹን በሞት ተነጥቀዋል። የእንባቸው ፅዋ ሞልቶ ፈስ’ሷል። ከጠገዴ እስከ ሰቲት ሁመራ፣ ከጠለምት እስከ ወልቃይት እጅግ ብዙ ያልተጻፉ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ሌላው ቀርቶ…. ከመሬታቸው ተነቅለው በሱዳን አድርገው… ስደተኛ ካምፕ ገብተው ያሳለፉት መከራ፤ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ እና ተተርኮ የሚያልቅ አይደለም።
ሌላው ቀርቶ… ስሜን ቤጌምድር ወይም ስሜን ጎንደር በህወሃት አስተዳደር ስር በወደቀበት ወቅት፤ ስሞታቸውን እና ቅሬታቸውን ማሰማት የሚችሉት፤ መቀሌ በመሄድ ብቻ እንዲሆን ተደረጉ። ቋንቋቸው ጉልፍ ትግሪኛ የጠራ አማርኛ በመሆኑ፤ በመቀሌዎች ዘንድ ወልቃይቴን ቁም ነገር የሚለው የለም ነበር። ነገራቸውን በአማርኛ አሳምረው፤ ጉዳያቸውን አማራ ክልል ላይ ሲያቀርቡ፤ “እዚያው ለክልላቹህ ለትግራይ መንግስት አቤት በሉ” ይሏቸዋል። አዲሳባ ድረስ ሄደው ለፌዴራል መንግስት ሲያለቅሱ፤ “መቀሌ ሄዳቹህ ቅሬታችሁን አሰሙ” ይባላሉ። መቀሌ ሲሄዱ ደግሞ፤ ከሚደርስባቸው ሽሙጥ እና ስድብ በተጨማሪ ታፍኖ መወሰድም ያጋጥማቸዋል፤ በዚህ አይነት ተወስደው የት እንደገቡ ሳይታወቅ የቀሩ፤ ብዙ ብዙ ታሪኮች አላቸው።
ከዚህ ርዕስ ውጪ ቢመስልም፤ ይሄ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ በጠለምት የሆነውን ታሪክ ጠቀስ አድርጌ ልለፈው። ጠለምት እና ፀለምትን ወይም ጨለምትን የማታውቁ ትኖራላቹህ። እነዚህ ቦታዎች ከተከዜ ወዲህ ከትግራይ በታች የሚገኙ ናቸው። ድሮ ቦታው ጠለምት ተብሎ ይጠራ ነበር። ሆኖም ወደ ትግራይ ወደሚጠጋው ጠለምት ያለው ስፍራ ለም ቢሆንም፤ የተወሰኑ ባላባቶች ናቸው የሚያርሱት እና የሚያሳርሱት። ሆኖም ከድሮ ጀምሮ እነዚህ ባላባቶች ሊያርሱ ወይም ሊያሳርሱ በወጡበት ሳይመለሱ ይቀራሉ። ብዙ ጊዜ አስከሬናቸው እንኳን አይገኝም። የዋሁ የጠለምት ሰው ደሞ…
“ኧረግ ይሄን ሰው ምን ዋጠው?” እያለ ከመገረም ውጪ ብዙም የሚያረገው የለም ነበር።
ይሄ እንደወጡ የመቅረቱ ነገር እየበዛ፤ የሟቾቹንም ሚስቶች የማዶ ሰዎች እያገቧቸው፤ መሬቱንም እየወሰዱ፤ የሚወለደውም ልጅ በአባቱ የማዶ አገር ሰው ልጅ እየሆነ… ብዙ አመታት አለፉ። እናም ከነዚህ ብዙ አመታት በኋላ ይሄ ከትግራይ አጠገብ ያለው ጠለምት፤ በሂደት በትግርኛ ተናጋሪዎች ተሞላ። ቀስ በቀስ ህወሃት ይህን አካባቢ በራሱ ሰዎች እያሰፈረ፣ ወታደሮቹን እያስቀመጠ… ስሙንም ከጠለምት ወደ ፀለምት ቀየረው።  አካባቢውንም ወደ ትግራይ ከለለው። ለአካባቢው ህዝብ “እህ?” ብላቹህ ጆሮ ከሰጣቹህ፤ በጣም አስገራሚ እና ለማመን የሚከብድ ታሪክ ልትሰሙ ትችላላቹህ።
በነገራቹህ ላይ የአካባቢው ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ፤ ወደባህርዳር፣ ጎንደር እና አስመራ የተተኮሱት ሮኬቶች፤ ከ’ነዚህ የፀለምት ተራሮች በአንደኛው ላይ ከተሰናዳ የትግራይ ጦር ካምፕ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።
አጋጣሚውን በመጠቀም አንዳንድ ታሪኮችን እንጨምር። ብዙ ሰዎች የዚህን አካባቢ ታሪክ… ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት፤ ከ1983 ዓ.ም ጀምረው ይተርካሉ። እንደእውነቱ ከሆነ ከ1983 እና ከመጀመሪያው ምርጫ በኋላ አካባቢው ህጋዊ ባልሆነ የህግ መንገድ ወደ ትግራይ እንዲከለል ሆነ እንጂ፤ ነገሩ የተበላሸው ከዚያ በፊት ነው። በሌላ አነጋገር… ከ1983 በኋላ የሆነው ነገር… ሰነድ የሚያውቀው እና ጸሃይ የሞቀው ጉዳይ ስለሆነ እንጂ፤ ይህ አካባቢ በህወሃት ቁጥጥር ስር መሆን የጀመረው በዘመነ ደርግ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ሆኖም ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ የሆነውን ነገር ማወቅ የግድ ስለሆነ፤ ይቺን እውነት ላጋራቹህ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ… ቦታው ከደርግ ቁጥጥር ውጪ ሆኖ፤ በራስ መንገሻ ስዩም የሚመራው የኢዲዩ ኃይል በበላይነት አካባቢውን ተቆጣጥሮት ነበር። ከኢዲዩ እጅ ፈልቅቀው መውሰድ ያቃታቸው የህወሃት አመራሮች… የኢዲዩ ሰዎችን “እንታረቅ” በማለት፤ ከህወሃት መካከል ያን ጊዜ መስራች እና አመራር የነበረው ገሰሰው አየለውን ጨምሮ በርካታ የህወሃት ሰዎች የእርቅ ጥሪ አደረጉ።
የኢዲዩ ሰዎች ደግሞ ከተከዜ ወዲህ ሆነው በሬዎች አርደው በፍቅር የድግሱን ስጋ እና መጠጥ ያወራርዳሉ። በዚህ መሃል ወያኔዎቹ ከበሮ እየመቱ ዘፈን ጀመሩ። “ብላዕ ትሳትብዕላ” እያሉ።
“ብላዕ ትሳትብዕላ” ማለትም፤ በአማርኛ ሲተረጎም “ብላ ትበላለህ!” እያሉ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ማንም ይገድሉናል ብሎ አልገመተም። ትንሽ ቆይቶ ግን ለእርቅ የተጠሩትን የኢዲዩ ሰዎች ገደሏቸው። ጥቂት ያመለጡ የኢዲዩ ሰዎች እነይርጋ፣ እነሲሳይ መርሻ፣ ሺሻዬ እና ስባጋዲስ እየተዋጉ ሲያፈገፍጉ፤ ከመጀመሪያዎቹ የህወሃት መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ገሰሰው አየለ፤ በመልሶ ማጥቃት ግንባሩን ተመትቶ ተከዜ ላይ ወደቀ። የሚገርመው ህወሃት ስለገሰሰው አየለ ምንም ሲሉ ሰምተን አናውቅም።
በሌላም ተመሳሳይ ታሪክ እንደዚሁ “እንታረቅ” ብለው አብረው በልተው እና ጠጥተው ሲያበቁ፤ ለሊት ሁሉም ሲተኛ፤ እነስዩም መስፍን የነበሩበት የህወሃት ቡድን ለሊት ተነስቶ፤ ቀን ላይ አብረው የበሉ እና የጠጡ ኢትዮጵያዊያኖችን በተኙበት ገደሏቸው። ይሄን ታሪክ ዛሬም ድረስ በህይወት ያሉ ሰዎች፤ በቁጭት ሲያነሱት… ህወሃት ደግሞ በዚህ የጭካኔ ተግባር ይኩራራል፤ እንደጀብዱም ያወራል።
እናም ህወሃቶች የኢዲዩ ሰዎችን በዚህ አይነት የጭካኔ መንገድ እና በኋላም ጦርነት እያደረጉ ካዳከሟቸው በኋላ፤ የኢዲዩ ይዞታ የነበረውን ቦታ የመውረስ እንቅስቃሴ ጀመሩ። ስለዚህ ወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው ከኢዲዩ ይዞታነት ወደ ሽምቅ ተዋጊው የተሃት ወይም የህወሃት ኃይል  በሃሳብ ሰነድ በማዛወር፤ የሁመራን መሬት ወደ ሱዳን መሻገሪያነት፤ እህል ውሃ፤ መጠለያ እና መሸሸጊያ ባስፈለገም ጊዜ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጉያ ውስጥ መመሸግ የዘመኑ የውጊያ ስልት ሆነ።  (ቀደም ሲል ተከዜ ላይ ድግስ ሲደረግ ከኢዲዩ ወገን ስባጋዲስ ብለን ጠቅሰን ነበር። በዚህ አጋጣሚ ስለስባጋዲስ ጥቂት እንበል። ስባጋዲስ የትግራይ አዲግራት ልጅ ነበር። ሆኖም ከህወሃት አፈንግጦ ይዋጋቸው ስለነበር ቂም ይዘው ቆይተዋል። በኋላ ሁሉም ነገር ከተረሳሳ በኋላ አገሩ ገብቶሳለ፤ የራሱ ሰዎች ጠቁመው አስያዙት። ወያኔዎችም አስረው ከወሰዱት በኋላ በትግራይ ውስጥ በሁሉም ስፍራ እያዞሩ፤ ሃጢያቱን እያበዙ… ወያኔዎቹም “ይገደል ይገደል” እያሉ፤ በየቦታው ካንከራተቱ በኋላ መቼ እና የት በማን እንደተገደለ ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ ቀረ።)
በደርግ የመጀመሪያ ዘመን፤ ሁመራ እና አካባቢው በኢዲዩ ሰዎች ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም፤ ቀስ በቀስ ወደ ህወሃት ይዞታነት በድብቅ ተዛወረ። ሆኖም ህዝቡ ይህን አካሄድ አልተቀበለውም። ስለዚህ በአካባቢው ለአማራው ህዝብ መብት እንደቆመ ተደርጎ የሚወሰደው የኢህአፓ አንደኛው ክፍል ኢህዴን እንደአስታራቂ ሆኖ ህወሃት እና ህዝቡን ውስጥ ለውስጥ ሲያደራድር ኖረ። በኢህአፓ ወገን ሆነው መሬቱን ህወሃት እንዲወስደው ያስማሙት እነታምራት ላይኔ፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምኦን፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ህላዌ ዮሴፍ… እነዚህ ሁሉ በህይወት የሚገኙ ሰዎች ስለሆኑ፤ የኢዲዩ መሪ የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩምም በህይወት ስላሉ፤ የህይወት እና የዘመን ምስክርነት ቃላቸውን ለህዝቡ ሊሰጡ ይገባል። ይህ ከሆነ… በጨለማ ውስጥ የተዳፈነችው እውነት ትበራለች።
ይህ ካልሆነ ግን የግድ የታሪክ ሰነድ ማገላበጥ ይኖርብናል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከዘመነ መሳፍንት በፊትም ሆነ በኋላ፤ ሰነድ የያዘው ብዙ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል። ከዚያም በነራስ አሊ፣ በነአጼ ቴዎድሮስ፣ በሁሉም ዘመን ያለውን የተጻፉ ታሪኮች ብንመለከት ስሜን ቤጌምድር በትግራይ ክልል ስር የሆነበት ምንም ታሪክ የለንም። በቅርብ ጊዜ በሚታወቁት… የነፊታውራሪ ጎላ፣ የነደጃዝማች አያሌው ብሩ፣ የነቢትወደድ አዳነ መኮንን አስተዳደር የሚያሳየን ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ስር ስትተዳደር አይደለም። እንኳንስ የአካባቢው ነዋሪ ቀርቶ በዘመኑ የትግራይ አስተዳዳሪ የነበሩት፤ የአጼ ዮሃንስ የልጅ፣ ልጅ ልጅ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም “የትግራይ ድንበር ተከዜ ነው።” በማለት… ምዕራብ ትግራይ የሚባለው ቦታ የትግራይ ሆኖ እንደማያውቅ መስክረዋል። እንግዲህ ፍርድ የምንሰጥ ከሆነ፤ ከተጻፉ የታሪክ መዛግብት በተጨማሪ በህይወት ያሉ ሰዎችን የምስክርነት ቃል መስማት የግድ ይሆናል።
እኛም ጣልቃ የገባነው…. ይሄን ታሪክ መናገር የነበረባቸው፤ የአካባቢው ተወላጆች ድምጻቸው ቢጠፋብን ጊዜ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ሁመራ እና አካባቢው ከህወሃት አመራር ነጻ መሆኑ ብቻውን ትልቅ ድል አይሆንም። ከዚህ ስፍራ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ሊካሱ ይገባል። ህወሃት ብዙ የድሮ መንደር እና ስሞችን ቀይሯል። ሰቲት ሁመራ የሚለውን ስም ሳይቀር፤ ቀፍታ ሁመራ በሚል ሌላ ስም ሰጥተውታል። ስለዚህ የዘመኑ ሰዎች ትንፋሻቸው እያለ እነዚያ የድሮ ስያሜዎችን ማስመለስ አለባቸው። አደባባዮች እና መንገዶች በታዋቂ ሰዎች ስም መሰየም አለባቸው። በግፍ ለወደቁት ሃውልት ሊቆምላቸው ይገባል። በማይካድራ እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ለተሰዉ ሰዎች የመታሰቢያ ሃውልት፤ ወይም ት/ቤት ወይም ቤተ እምነት እንዲሰራላቸው ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ መጣል ያለብን አሁን ነው።
ይህ አካባቢ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንደመሆኑ መጠን፤ በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት መተዳደሩ አይቀርም። ይህ በእንዲህ እንዳለ “በአማራ ወይም በትግራይ ይተዳደር?” የሚለው ክርክር ከቶ የማይቀር ነው። ሆኖም ነገሮች ከተበላሹ ሰነባብተዋልና ነገሮችን በግብታዊነት ሳይሆን በተረጋጋ ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ህወሃት ከሁመራ እና ከራያ ውጪ ምንም ናት። ነገር ግን ማየት ያለብን ህወሃትን ሳይሆን ህዝቡን ነው። ነገሮችን አርቀን በማሰብ፤ ስለኢትዮጵያ ጥቅም ሃሳባችንን መቁረጥ አለብን። ስለዚህ በአካባቢው ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ህገ መንግስታዊ ዋስትና መስጠት ተቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል። ይህን ማድረግ ከቻልን… እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብታቸውን ስናከብር፤ እነሱም ለአካባቢው ነዋሪዎች ቅድመ ታሪክ እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ። ለሚኖሩበት አገር ህግ እና ደንብም ተገዢ ይሆናሉ። ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርተን… በግብታዊነት እና በብሽሽቅ መንፈስ “እናንተ የወያኔ ርዝራዦች” ብለን ጨዋታ ከጀመርን ግን ውጤቱ ጥሩ አይመጣም። አንድ ማስታወስ ያለብን ነገር እነዚህ ሰዎች ከአርባ አመታት በላይ የክፋት ስራቸውን ሲሰሩ ነበር፤ ይሄ የክፋት ተራራ እየተናደባቸው ሲመጣ በንዴት እና በእብደት ብዙ ጥፋት ሊያደርሱ እንደሚችሉ  ማስተዋል የግድ ነው።
እናም አባባቢው “በአማራ ወይም በትግራይ ስር ይተዳደር?” የሚለው ጥያቄ ጊዜውን የጠበቀ ቢሆንም፤ ከክርክሩ ይልቅ ርክክቡ ስክነትን ይጠይቃል። ይህ ካልሆነ እንኳንስ ርክክቡ ክርክሩም የዜሮ ብዜት ውጤት ሊሆን ይችላልና …ለኛ ብቻ ሳይሆን የነገውን የልጆቻችንን እድል በማሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። ስለዚህ ከብዙ ምርጫዎች መካከል አንደኛው አማራጭ መሆን ያለበት፤ በብዙ አወዛጋቢ ቦታዎች ላይ በጥቅም ላይ የሚውለው የ Status Quo አሰራርን መከተል ነው። ስለዚህ የውዝግቡ ክርክር ከመከፈቱ በፊት አካባቢውን ወደቀደመው የስክነት ደረጃ ወይም Status Quo መመለስ ያስፈልጋል። “ነገር ግን ወደየትኛው የስክነት ደረጃ Status Quo እንመለስ? ከስሜን ቤጌምድርነቱ እንጀምር? ስሜን ጎንደር በተባለበት ዘመን ያለውን እናንሳ? ወይስ ምዕራብ ትግራይ ከተባለበት ዘመን እንጀምር?” የሚለውን ጥያቄ አስቀድመን መመለስ የግድ ነው።
እንግዲህ ለነዚህ ጥያቄዎች ሁሉም በየግሉ የየራሱን ሃሳብ እና አስተያየት ሊሰጥ ይችላል። ያሻውንም ሊመርጥ መብቱ ነው። እኔ በዚህ ጉዳይ ብጠየቅ ግን፤ በቅድሚያ አካባቢውን ወደ ቀድሞ ማንነቱ “ስሜን ቤጌምድር” የስክነት ደረጃው Status Quo በመመለስ፤ ከዚያም ለምን ስሜን ጎንደር እንደተባለ፤ እንዴትስ ወደ ምዕራብ ትግራይነት እንደተቀየረ ነገሮችን በእርጋታ በመመርመር ፍርድ እሰጣለሁ። የ’ናንተም ፍርድ የጅምላ ወይም የችኮላ እንዳይሆን፤ “ነገርን ከስሩ…” መመርመር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው፤ ለዚያ አካባቢው ዘላቂ ሰላም የምናመጣው። ይህን ማድረግ ካልቻልን፤ በግብታዊነትና በአሸናፊነት እብሪት ተሸናፊውን መኮርኮም ከጀመርን፤ ቀጣናው የሰሜን ግዛት ኤኬልዳማ ሊሆን ስለሚችል፤ ውሳኔ ስንሰጥ የአባት አያቶቻችንን ሰነድ ፈትሸን፤ የአሁኑን ብልሽት አክመን ሊሆን ይገባል። እንዲህ በማድረግ
የችግሩ ሳይሆን የመፍትሄው አካል እንሁን።
በአጭሩ… ፍርድ ከመስጠታችን በፊት፤ በቅድሚያ ነገሮች ከመበላሸታቸው በፊት ወደነበረበት የስክነት መጠን ወይም Status Quo መመለስ አለብን። እስከዚያው ግን… ሁኔታዎችን በተረጋጋ መንፈስ ማየት እንጂ፤ በግድ እና በጭንቅ ወደ ድምፀ ውሳኔ መሄድ ወይም ወደ መሬት ባለቤትነት ውዝግብ ማምራት ማለት፤ የህወሃትን መንገድ መከተል ይሆናል። ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለደቂቃዎች ባሉበት ሆነው በጽሞና ሊያስቡበት የግድ ነው።
Filed in: Amharic