>

ዕብሪት የውድቀት ምንጭ ናት ሕወሓት ይንኮታኮታል፤ የትግራይ ሕዝብ ግን ይኖራል...!!! (ኒሻን በላይ)

ዕብሪት የውድቀት ምንጭ ናት
ሕወሓት ይንኮታኮታል፤ የትግራይ ሕዝብ ግን ይኖራል…!!!
(ኒሻን በላይ)

ሕወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ነገር በፍፁማዊ የበላይነት ተቆጣጥሮ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱም ባልገመተውና ባልጠበቀው ሁኔታና ፍጥነት ተሸንፎ ወደ መቀሌ ያፈገፈገው ከልክ ያለፈ ዕብሪት አውሮት፣ የኢትዮጵያንም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተፈጠሩትን የኀይል አሰላለፍ ለውጦች መገምገም እና ራሱን ከነባራዊ ሁኔታው አንጻር ማስተካከል ስላቃተው ነው፡፡
ሮማዊያን ተቀዳሚው የውድቀት ምንጭ ከልክ ያለፈ ዕብሪት (hubris) ነው ይላሉ፡፡ ዕብሪት ራስንና የራስን ወገን፤ ብሎም ጠላትንና የጠላትን ወገን በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ለመተንተን ዐይንን ያውራል፡፡ ዕብሪት ከሕዝብ የሚቀርብ ሮሮና ብሶት እንዳይደመጥ ጆሮን ይደፍናል፡፡ ዕብሪት ሁልጊዜም ትክክል የእኛ መስመር ነው የሚል መታበይን ያመጣል፡፡
የሕወሓት ውድቀት ከዚህ ዕውነታ ጋር በእጅ የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደሚሉት “አድፋጭ” በመሆኑ ለጊዜው ዝም ቢልም ጭቆናን ተቀብሏል ማለት አይደለም፡፡ ዝምታው ዕድልና ሁኔታዎችን እስኪመቻቹለት ነው፡፡ ዕድሎች ሲመቻቹለት እንደኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶቹን ማደባየት የሚችል ሕዝብ የለም፡፡ እርግጥ ይህ የሕዝባችን አድፋጭ ባሕርይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ላይጠቅም ይችላል፡፡ አምባገነኖች እንዲፈራረቁበት ምክንያት የሆነውም ይህ ባሕርይ ሊሆን ይችላል፡፡
የሆነ ሆኖ፣ ሕወሓት በአመዛኙ በራሱ ድክመት ምክንያት አይወድቁ አወዳደቅ ወድቋል፡፡ ሕወሓት አሁን ወደ መቀሌ ሸሽቶ “የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ ነው” እያለ እንደተለመደው የትግራይን ሕዝብ መጠቀሚያ ሊያደርገው እየሞከረ ነው፡፡
ሕወሓትና የፍርሃት መንገሥ ስትራቴጂው
የሕወሓት መሪዎችን ለሥልጣን ያበቃቸውም በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ያደረጋቸውም “ፀረ ትግራዮች መጡብህ!” የሚለው ፍርሃት የማንገሥ ስትራቴጂ ነው፡፡ ፍርሃት ማንገሥ እንደ ስትራቴጅ ዋነኛው የሕወሓት መለያ ነው፡፡ ድርጅቱ ሥልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ይህን ፍርሃት የማንገሥ ስትራቴጅ በደንብ ተጠቅሞበታል፡፡ “ትምክህተኞች ሊመጡባችሁ ነው”፣ “ጠባቦች ሊበሏችሁ ነው”፣ “ኢትዮጵያ ትበታተናለች” ወዘተ… እየተባለ በስፋት ተቀስቅሷል፡፡ የማሰልጠኛ ሰነዶች ሳይቀሩ እየተዘጋጁ በየጊዜው የስልጠና መርሐ-ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ብዙ ተጽፏል፡፡ ብዙ ተነግሯል፡፡
ይህ ፍርሃት የማንገሥ ስትራቴጅ አልሠራም ማለት አይቻልም፡፡ በደንብ ሠርቷል፡፡ ስትራቴጅው በመሥራቱ ምክንያት ነው አንድ የሕዝብ ውክልና የሌለው ቡድን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የምታህል ግዙፍ አገር ሰጥ-ለጥ አድርጎ መግዛት የቻለው፡፡ ሆኖም ሕወሓት ውስጥ በገነገነው ዕብሪት ምክንያት ይህ ስትራቴጅ ስለተነቃበትና ሌላ አዲስና ዘመኑን የዋጀ ሕዝብን ሊያደናግር የሚችል ስትራቴጅ ማፍለቅ ስላልቻለ ተዋርዶ ሸሽቷል፡፡
ይህ ቡድን አሁንም ያን ያደገበትን ስትራቴጅ ነው ትግራይ ውስጥ እየተከተለ ያለው፡፡ አዲስ ነገር አላመጣም፡፡ አሁንም የትግራይን ሕዝብና ሕወሓትን አንድ በማድረግ “ልንወረር ነው”፣ “ሊዘመትብን ነው”፣ “የፌደራል ሥርዓቱ ፈርሶ አሐዳዊያን የትግራይን ህልውና ሊያጠፉት ነው”፣ “ፋሽስቱ ዐቢይ አሕመድና አምባገነኑ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ከተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ጋር ሆኖ ትግራይን እየደበደቡ ነው” ወዘተ… እያለ በሬ-ወለደ እያወራ ነው፡፡ ይህን መሠረተ-ቢስ ፕሮፓጋንዳውን በሕዝቡ ላይ ለማስረጽ ይረዳው ዘንድ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪያንን ቀጥሮ እያሠራ ሲሆን፣ ተጨማሪ የሳተላይት ቴሌቪዥኖችም ከፍቶ ጥላቻ በመዝራት ፍርሃት ሲያነግስ ቆይቷል፡፡
ሕወሓት “የፌደራሊስት ኀይሎች” ከሚላቸው ቀለብተኞቹ ጋር ለተወሰኑ ጊዜያት “አሐዳዊያን” የሚሉትን የለውጥ ኀይል ሲወነጅሉ ቢቆዩም፣ የፌደራሊስት ኀይል ነኝ የሚለው ቀለብተኛ ስብስብ ከጥቅም ውጪ የሚያገናኘው ገመድ ስለሌለ ባለፈው ሳምንት መንኮታኮቱንና ወደ እርስ በርስ መናቆር መግባቱን ታዝበናል፡፡ ስለሆነም ሕወሓት ሌሎችን ኀይሎች ለማሰባሰብ የሚያደርገው ጥረት በየጊዜው እየመነመነና እየተዳከመ መጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ አለመሆናቸውን፣ ይልቁንም ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በሰላምና በመግባባት እንዳይኖር መሰናክል መሆኑን የሚያምኑ በአረና ትግራይ፣ በትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር፣ በትግራይ ብልጽግና ወዘተ… ድርጅቶች ውስጥ የተሰባሰቡ የትግራይ ተወላጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ድጋፍ እያገኙና እየጎለበቱ መምጣታቸው አይቀርም፡፡
ትግራይ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ፀረ ሕወሓት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ እነዚህ ፀረ ሕወሓት በርካታ የክልሉ አካባቢዎች እያዳረሱና እየጎለበቱ መጥተዋል፡፡ ሕወሓትና የትግራይ ወጣት ይበልጥ እየተራራቁ መሄዳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ የማይጠቅም እጅግ ክፉ ቡድን መሆኑን ራሱ ሕዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ እየተረዳ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
ሕወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉም ነገር በእጁ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ፍርፋሪ (spoil) በማካፈል የተቃዋሚዎቹን አንደበት ሲዘጋ ቆይቷል፡፡ አሁን እሱ የለም፡፡ አሁን ሕወሓት እንደፈለገ እየዘገነ የሚሰጠው ሥልጣንም የአገር ሀብትም የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ፍርፋሪ ፈልጎ የሚጠጋውና የሚደግፈው ኀይል ሊኖር አይችልም፡፡ ጡንቻውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መሄዱንም በግልጽ እያየነው ነው፡፡ የነ አቶ ስበሐት ነጋ ቡድን ከልክ ያለፈ ዕብሪትና ሐኬት (hubris) ወጥሮት ራሱ በፈጠረው የዘውግ ፖለቲካ እየተለበለበ ይገኛል፡፡
ስለሆነም ሕወሓት የቀደመውን ሕዝባዊ የትግል ታሪክ እየጠቀሰ “ወድቀን መነሳት እናውቅበታለን!” እያለ ነጋ ጠባ ቢያላዝንም፣ ጊዜውና ሁኔታ በእጅጉ ስለተቀየረ ፈፅሞ የማይሆን ቀቢጸ-ተስፋ ብቻ ነው፡፡ የሕወሓት ነባር መሪዎች ሕፃናት የድሃ ልጆችን እንደ ሰብአዊ ጋሻ በመጠቀም ከማስጨረስ ውጪ ከዚህ በኋላ ወደ ትግል ሜዳ የሚገቡበት ዕድል የለም፡፡ ከኮክቴል ወደ ኮቾሮ የሚደረግ ሽግግር የማይታሰብ ነው፡፡ እየታየ ያለው ሐቅም እሱ ነው፡፡
ዕብሪት የውድቀት ምንጭ ናት፡፡ የሕወሓት የወድቀት ምንጭም ዕብሪት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የትግራይ ሕዝብ ዛሬም እንደ ጥንቱ ከቀረው የኢትዮጵያ እህትና ወንድሙ ጋር ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያም ትቀጥላለች፡፡
Filed in: Amharic