>

ዳግም አሽከርነት/ሎሌነት (“Recycled Servants/Retainers”) [ከይኄይስ እውነቱ]

ዳግም አሽከርነት/ሎሌነት

(“Recycled Servants/Retainers”)

ከይኄይስ እውነቱ


የአገዛዞች አንድ ቋሚ ገጽታ ታማኝ አሽከሮችን/ሎሌዎችን መፍጠር ነው፡፡ በዘመኑ ቋንቋ ካድሬ የሚባለው (ቢያንስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዐውድ) በነዚህ ታማኝ አገልጋዮች ውስጥ የሚካተት መጠሪያ ነው፡፡ ሎሌነት ሰውነትን ማቆም ነው፡፡ ሎሌነት ከኅሊና መፋታት ነው፡፡ ሎሌነት የማሰብ ሥራ የግል መሆኑን ማቆም ነው፤ ሎሌ ጌታው ያሰበለትን ሳይጠይቅ የሚፈጸም፤ ጌታው የተናገረውን እንደ በቀቀን የሚያስተጋባ ነው፡፡ ሎሌ እንደ ታማኝ ውሻ በበላበት የሚጮኽ ነው፡፡ ሎሌዎች የሚጠብቁት እሤት፣ የሚቆሙለት መርህ፣ የሚሞቱለት ዓላማ የላቸውም፡፡ ሎሌነት በገዛ ፈቃድ ራስን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ሎሌነት በገዛ ፈቃድ ወደ ከብትነት መቀየር ነው፡፡ ባጭሩ ሎሌነት ታሕተ ሰብእነት ነው፡፡ ሎሌዎች ራሳቸው ተዋርደው ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብን፣ ኅብረተሰብንና አገርን የሚያዋርዱ ቀሊላን ናቸው፡፡ ሎሌ ግለሰብ፣ ቡድን እና ድርጅትም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚጠበቅበት ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት ማለትን ብቻ ነው፡፡ በተለይም አንዱ አገዛዝ አልፎ ሌላው ሲተካ እየተገለባበጡ ለአሽከርነት የሚሽቀዳደሙትን ነው በዚህ ጽሑፍ ዳግማዊ ሎሌዎች (recycled retainers/servants) ያልዃቸው፡፡ በነገራችን ላይ አድርባይነትም የሎሌነት አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ስለሆነም አድርባዮችም አልተነሳንም ብላችሁ ቅር እንዳትሰኙ፡፡ 

አገዛዞች ሎሌዎችን የሚፈልጉባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም፣ ለአብነት ያህል የጋራ የሆኑትን ዋና ዋና ነጥቦች ለማንሳት እሞክራለሁ፤

1) የሕዝብን ተቃውሞ እና ስሞታ መከተር/ማፈን፤

2) ሕጉን፣ መዋቅሩንና አሠራሩን ሁሉ ለአገዛዞች መሣሪያ በማድረግ ለባርነት ምቹ መደላድልን መፍጠር፤

3) በተቻለ መጠን ከሕዝቡ መካከል አብዛኞችን ለአገዛዙ በሎሌነት ማሳደር ወይም ማደንዘዝ፤

4) ጭቆናን/ግፍን እና ውሸትን ማለማመድ፤

5) ባገዛዞች የተሳሳት ዓላማ ዙሪያ ሕዝብን ማስተባበር፤ የእምቢታ አዝማሚያ ሲኖር በጉልበት ማስገደድ፤

6) ሆን ብሎ የውሸት መረጃዎችን (disinformation) ማሰራጨት፤ይህንን ተከትሎ በሚፈጠር ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ (misinformation) ሕዝብን ማመስ ማተራመስ፤

7) የሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየር ወይም ከዐቢይ ጉዳይ ማናጠብ፤

ስለ ሎሌዎች በመግቢያነት ይህን ያህል ካልኹ፣ የዛሬው አስተያየቴ ትኩረት የሲዳሞ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት፣ በኦሕዴድ መራሹ ኢሕአዴግ ቊ.2 (የብልጽግና ፓርቲ) እና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ ያለውን ‹ጦርነት› አስመልክቶ በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ ይመለከታል፡፡ ርግጡን ለመናገር መግለጫው በማዕከላዊነት ከዐቢይ ወርዶለት በገደል ማሚቶነት ያስተጋባው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ጽ/ቤቱ ኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ካወጣው መግለጫ ለዚህ አስተያየት አግባብነት ያለውን ክፍል እንደሚከተለው እጠቅሰዋለሁ፤

‹‹በዚህ ጊዜ በሀገራችን እየተካሄደ የሚገኘው ሕግን የማስከበር ተግባር የሀገርን አንድነት፣ የሕዝቦችን አብሮነትና የሕግ የበላይነት ለማስከበር እንጂ በይደር የቆዩ አጀንዳዎችን ማሳኪያ ተደርጎ መወሰድ የለባቸውም፡፡ በፌደራል መንግሥቱና በጁንታው የሕወሓት ቡድን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የተወሰነ ኃይል እያካሄድ ያለው ትግልም አይደለም፡፡ የዚህ ማሳያው በኅብረ ብሔራዊነት የተደራጀው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት … ትግሉን በተዛባ መልኩ ለመተርጐም የሚደረጉ የተሳሳቱ ትርክቶችን በጋራ በመታገል …›› እያለ ከፕሮፓጋንዳነት ያልዘለለውን ዝባዝንኬ ይቀጥላል፡፡

እንደማናቸውም በጐሣ የተዋቀረ ‹የፖለቲካ ማኅበር› የሲዳሞ የጐሣ ‹ፓርቲዎች› የክፍለ ሀገርነት ደረጃ ካገኙ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ ኦሮሙማን ለሚያስፈጽመው የዐቢይ አገዛዝ በመገበር እንደ ሌሎቹ የኢሕአዴግ ቊ.2 ጭፍሮች ሎሌነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ቊ.1 ሕወሓት እንደሆነ ሁሉ ቊ.2 ደግሞ ኦሕዴድ መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ የሲዳሞ የጐሣ ድርጅቶች ወያኔ ‹ክልል› ብሎ ያዋቀረው ‹የአገር-አከል› መዋቅር ይገባናል በማለት ተጨቁነናል/ተበድለናል ብለው (ሕወሓት የተከለውን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት›፣ የጐሣ ፖለቲካና የውሸት የጐሣ ፌዴራሊዝም ተቃዋሚዎች ባይሆኑም) እንዳልጮኹ ሁሉ፣ ዛሬ በመግለጫቸው ዐቢይ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ከሕወሓት ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ (‹ትግሉን በተዛባ መልኩ ለመተርጐም› የሚለው አባባል አገዛዙና አፈ ቀላጤዎቹ ጦርነቱ ስለሚካሄድበት ዓላማ ከነገሩን የተረዳን ሲሆን፣ ወደፊት ደግሞ በውጤቱ የበለጠ ገሀድ ይሆናል) በፊት ረድፍ ተሰልፈው የሕይወት መሥዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ የአማራ ሚሊሻዎችና ወጣቶች ነፃ ያወጧቸውን የጎንደር (ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ጸለምት) እና የወሎ ግዛቶች (የራያ ርስቶች) ተመልሰው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር እንዲቆዩ ከመናገር አልፈው ‹አሳዳሪያቸው› እንዳለው የግዛት ጥያቄዎቹ በአገር አውዳሚው የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› መሠረት የሚታዩ እንጂ አጋጣሚው (ጦርነቱ) በይደር የቆዩ አጀንዳዎች ማሳኪያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም በማለት ለአማራ ሕዝብ ያላቸውን ጥላቻ በዚህም ድንቁርናቸውንና ነውረኛነታቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ጦርነት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የተወሰነ ኃይል በማለትም የአማራውን ሚሊሻ ኃይል በሾርኒ አንስተዋል፡፡ 

ሕወሓት፣ ጐሠኛነትን እና ይህም አስተሳሰብ ባገር ህልውና ላይ ያስከተለውን መዘዝ አጥብቀው የሚጸየፉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠላት መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ይህ አሸባሪ ድርጅት እስከ ሰይጣናዊ አስተሳሰቡ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ የማይፈልጉ አገር አጥፊውን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› እና የጐሣ ፖለቲካው እንዲቀጥል የሚሹ ጐሠኞች ብቻ ናቸው፡፡ የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› እስከ ዘረጋው መዋቅር እንዲቀጥል በመፈለግ ረገድ የኦሮሙማ አራማጆች፣ ሌሎች ጐሠኞችና ሕወሓት መካከል ልዩነት የለም፡፡

የሲዳሞ የጐሣ ድርጅቶች የ‹ክልል› ይገባናል ጥያቄ ሲያነሱ በጀዋርና ኦነግ አስተባባሪነት የሽብር ቡድን አስነስተው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣ በቤተክርስቲያኒቱ እና በአማራ ተወላጆች ላይ ያደረሱት ግፍ ሳያንስና ሳይዘነጋ፣ የአማራው ሕዝብ በወረራና ዘር በማጥፋት የተወሰዱበትን ግዛቶች ሕይወቱን ከፍሎ ሲያስመልስ ተገቢ አይደለም ማለት ከሕወሓት ጋር ባንድነት መቆም ብቻ ሳይሆን ከሕወሓት ጋር እየተጋደሉ ውድ ሕይወታቸውን ያጡትን ኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነት ከንቱ ከማድረግና ሎሌ ለጌታው ያለውን ታማኝነት ለማሳየት የሚሄድበትን ርቀት ከሚያረጋግጥ በቀር ሌላ ትርጕም የለውም፡፡ 

በመሠረቱ የትኛውም የጐሣ ድርጅት እንኳን የሕዝብ የጐሣው ወኪል ነኝ ብሎ መናገር አይችልም፡፡ ከመነሻውስ የጐሣ አባላቱን ማን ጠይቆአቸው/አማክሮአቸው? ይህ ባይሆንማ ኖሮ ለአንድ ጐሣ በርካታ የጐሣ ድርጅቶች ማቋቋም ባላስፈለገ ነበር፡፡ አማራጮችን ለማቅረብ እንዳይባል የጐሣ ድርጅት መሠረቱ አጥንት ጕልጥምት ነውና፡፡ የቅርጫና ቅርምቱ ዒላማ ሥልጣን ብቻ በመሆኑ እንጂ፡፡ ለዚህም ይመስላል እንደ ገዢው ኦሕዴድ ዛሬ የሲዳሞ ሕዝብ ጠበቃ መስላችሁ የቀረባችሁ አንዳንዶች፣ ወያኔ ደቡብ ብሎ በሰየመው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በነበራችሁ ሥልጣንና ኃላፊነት ለወያኔ ታማኝ ሎሌ ሆናችሁ የግዛቱንና የራሴ የምትሉትን ሕዝብ በግድያና በዝርፊያ ቁም ስቅሉን ስታሳዩ አልነበረም? በቅርቡ እንኳን የወላይታ ሕዝብ፣ የጉራጌ ሕዝብ ‹ከክልላችን› ይውጣልን ስትሉ አልነበረም? ደርሶ ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ አብሮነት ስትሉ አታፍሩም!?፡፡ የታይታ ጠበቃ መሆን ያስተዛዝባል፡፡ ተዉ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ የሲዳሞ ሕዝብ በተለይ ይታዘባችኋል፡፡ ነግ በኔን ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ መተሳሰቡና አብሮነቱ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ሕወሓት ለመፋለም የተንቀሳቀሰው እኮ ሽመልስ አብዲሳ ከ30 ዙር በላይ ያሠለጠነው ልዩ ኃይል አይደለም፡፡ ወይም አትድረሱብኝ በሚባሉት በሌሎች ‹ክልሎች› የተደራጁት ልዩ ኃይሎች አይደሉም፡፡ ዐቢይ ለሥልጣኑ ማስጠበቂያ ሲል በጐሠኛነት አስተሳሰብ እና የራሴ በሚለው ጐሣ የበላይነት ያደራጀው ‹መከላከያ ኃይል› እና በማንነቱና በሃይማኖቱ የዘር ፍጅት እየተፈጸመበት ያለው ኢትዮጵያዊው የአማራ ደሀ ገበሬና ወጣት ነው፡፡ እናስተውል! ለሥልጣን፣ የማይገባ ጥቅም ለማጋበስና ኃላፊ ለሆነ የፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል ዘላቂውን ያገር ጉዳይ በጊዜያዊው ባንለውጠው መልካም ይመስለኛል፡፡ ማስተዋሉን ይስጣችሁ፡፡

Filed in: Amharic