አምባቸው ደጀኔ
ሕወሓትም ትባል ትህነግ ወይም ወያኔ የቀብር ሥነ ሥርዓቷ በቀናት ውስጥ እንደሚፈጸም የብዙዎቻችን ግምት ነው፡፡ የዘራችውን እያጨደችና እየወቃች ወደ ጎተራዋም እየከተተች ነው፡፡ በርሷ ጦስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር፤ እነሱ ዕዳቸውን በጊዜ ተወጡ፤ ይብላኝ ለቀሪ! ወዮ ለኛ!
የወያኔ መደምሰስ ከኢትዮጵያ ችግሮች በዛ ቢባል 40 በመቶውን ያህል ይቀርፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስልሳ በመቶውን ደግሞ ከወያኔ ቀብር መልስ ገና ንፍሮዋንም በልተን ሳንጨርስ የምንጋፈጠው ይሆናል፡፡ መለስ ዜናዊና ግብጽን የመሰሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሕወሓት በኩል የዘሩት የክፋት ዘርና የጎሠኝነት መርዝ ከሀገራችን ተጠራርጎ እስኪጠፋ ድረስ እንዲህ በቀላሉ የነፃነት አየር እንተነፍሳለን ብላችሁ እንዳትጠብቁ፡፡ ወያኔ የምትጠፋው ባሳደገቻቸው ልጆቿ መሆኑን አንርሳ፡፡ አባቱን ገድሎ የሚቀብር ልጅ ደግሞ ብዙ ባሕርያቱን ከአባቱ እንደመውረሱ ለምን አባቱን እንደሚገድል ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡- አንድም ለውርስ ነው፤ አንድም በፖለቲካው ረገድ ካየነው እንደሶፎክልሱ ምናባዊ ፍጡር እንደንጉሥ ኦዲፐስ እናትን አግብቶ ሥልጣንን በግላጭ ለመቆጣጠር ነው፡፡ ላይ ላዩን ገራገር የሚመስለው ጠ/ሚ፣ ዶ/ር፣ ኮሎኔል፣ ሰባተኛው ንጉሥ አቢይ አህመድ ወያኔን የሚደመስስበት የ”ይደልዎሙ” ምክንያት ተዓማኒ ቢሆንምና የሚሊዮኖችን ድጋፍ ቢያገኝም በሌሎች አካባቢዎችና በሌሎች ፈርጆች እንደሚሠራቸው አግባብነት የሚጎድላቸው ወይም ከናካቴው የሌላቸው አጠያያቂ ተግባራት ከሆነ ግን ከወያኔ ውድቀት በኋላ ሀገራችንን የሚገጥማት ፈተና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ማመን ተገቢ ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የኦህዲድን ያህል የሰው ዕርድ ውስጥ አልገባችም፡፡ እነዚህ ግን ገና ሦስት ዓመት ሳይቆዩ ማንነትን መሠረት ያደረገ ስንትና ስንት ጭፍጨፋና ከሥራ፣ ከመኖሪያ ቀየና ከኑሮ የማፈናቀል ሥራ ላይ ተጠምደው እያየን ነው፡፡ ኦሮምኛ ካላወቅህ በፌዴራል መ/ቤቶች አትቀጠርም የሚሉህ ጉዶች ጋር እስከመቼ እንደምትዝልቅ አስበው፡፡ እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ የጅብ ችኩልም ዓይነት አለው እኮ፡፡ ቢያንስ ቀንድ ይነክሳል፡፡ እነዚህ እኮ ጭራም ሰኮናም አልቀራቸውም፤ እንዳበደ ውሻ ሁሉንም መልከፍን ተያይዘውታል፡፡ ይህ የዕውር ድንብር አካሄዳቸው የጤንነት አይመስለኝም፡፡
ዋና ዋና ፈተናዎችንና መፍትሔዎቻቸውን ባጭር ባጭሩ እንመልከት፡፡
‹
- ወያኔ የተከለው ህገ መንግሥት
ትልቁ የኢትዮጵያ ፈተና ይህ በወያኔ ተረቅቆ ሀገርና ሕዝብን በቋንቋና በዘር የከፋፈለ ህገ መንግሥት ተብዬ ነው – በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌለና በቀሪዎቹ የእንስሳት ዓለምም ያልታዬ ክፍፍሎሽ፡፡ በመሠረቱ ህገ መንግሥቱ ለወያኔ ሲሆን የማይሠራ፣ ወያኔ ለሚፈልገው ጉዳይ ግን እንዲሠራ የሚደረግ ዝባዝንኬ ነበር፡፡ ያን ዝባዝንኬ እንዳለ የተረከበውና ለርሱ ሲል ጦርነትም እከፍታለሁ የሚለው የአሁኑ መንግሥት ብዙ ዜጎች ያለቁበትንና ሀገርን ያወደመውን የወያኔ ህገ መንግሥት ተሸክሞ በመንከርፈፍ ላይ ነው፡፡ ይህ የይስሙላ ህገ መንግሥት እኮ ተንኮለኛው የወያኔ ቡድን መቶ ሽህ የማይሞሉና በሥልጣኔ ያልገፉ ዜጎችን በክልልነት መድቦ (ዶሮን ሲያታልሏት ዓይነት)፣ በራሱ ሰዎች የዚያን ክልል መንግሥት ሥልጣን ተቆጣጥሮ ለሆነ ዓላማው ስኬት ይጠቀምበት የነበረ ነው፡፡ ያገራችን ሰው “እንትን ላይ ተቀምጦ ፈስ ገማኝ አይባልም” ይላል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ይህን ከፋፋይ ህገ መንግሥት ለማስቀጠል ከሆነማ ያ ሁሉ መስዋዕትነት ለምን ተከፈለ? ወያኔንስ መጣል ለምን አስፈለገ? አዲስ ስቃይ ከምንለማመድ የለመድነው ስቃይ አይሻልም ነበርን? ስቃይ በዓይነትና በይዘት ቢለያይም ከአንድ የመከራና የስቃይ አዙሪት ወደሌላ የመከራና የስቃይ አዙሪት መገለባበጥ ግን ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተረኛ ዘረኞች እንደዐይናቸው ብሌን የሚያዩትን ያን የተረገመ የወያኔ ህገ መንግሥት ቀድዶ ለመጣል ብዙ ትግልንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ጥበብንና ጀግንነትን ተላብሶ ሁነኛ ትግል ከተካሄደ የማይሣካ ነገር የለምና ይህ የዳግማዊም እንበለው የሣልሣዊ ወያኔዎች ሀገር በታኝ ወረቀት ተቀዳዶ መጣሉ ግን አይቀርም፡፡
- ከህገ መንግሥቱ ጋር የተያያዙ እንደ ባንዲራ ያሉ ሀገራዊ የወል ምልክቶች
ወያኔ የትራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ለማውጣት ለ46 ዓመታት ታግላለች፡፡ ከትግሉ መልኮች አንዱ የሀገሩን ነባር ባንዲራ እንደነፍሱ ይወደው የነበረውን የትግራይ ሕዝብ አሁን የሰይጣን ዓርማ ያለበትን ቀይና ቢጫ ባንዲራ በቀሚስና በሸሚዝ ሳይቀር አሰፍተው እስከመልበስ ደርሰዋል፡፡ ይህ ነገር እውነት ወይም ውሸት፣ ካንጀት ወይም ካንገት መሆኑን ለመረዳት ትንሽ ጊዜ የሚቀረን ቢሆንም የወል ባንዲራችንን ከተጋሩ ልብ ለማውጣት ያልተፈነቀለ ድንጋይ እንዳልነበረ ግን ትግራይ ራሷ ምስክር ናት፡፡
በተጋሩ እንዲህ ከሆነ በሌላውና በተለይም በኦሮሞው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ባለፈ በግልጽ እያየነው ነው፡፡ ኦሮሞ አካባቢ ቢያንስ ሦስት ባዕዳን ባንዲራዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ሁለቱ ከግብጽ የተኮረጁ ናቸው፡፡ ግብጽና ኦሮሞ ልክ እንደጀርመንና ኦሮሞ በአንዳንድ ነገሮች የሚገናኙ ይመስላል፡፡ የሚገርም ቢሆንም ይሁን፡፡ ግን የሆነ ነገር ይሸታል፡፡ ጥሩ ያልሆነ ሽታ፡፡ የሚደንቀው ደግሞ አክራሪ ኦሮሞዎች በተረኝነት ስሜት በመስከራቸው የግብጽን ባንዲራ አፍቅረው በተለያዬ አቀማመጥ ሰድረው ማውለብለባቸው ሳያንስ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚወዱትን ንጹሕ (አረንጓዴ ቢጫ ቀይ) የኢትዮጵያ ባንዲራ እንዳያውለበልቡ መከልከላቸውና በህግ ስም ማንገላታታቸው ነው – ከወያኔ የወረሱት ጥጋበኝነት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ባንዲራችንን ከየልብሶቻችንና ግንባሮቻችን የመንጠቅና በእግራቸው የመርገጥ ወይም በእሳት የማቃጠል ዕብሪትም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወያኔዊና ኦነጋዊ ፕሮፓጋንዳ የፈጠረው ጥጋብና ዕብሪት ካልበረደ ሕወሓት ሞተች አልሞተች ዋጋ የለውም – ዋጮን እንደመገልበጥ ነው – ያው ዋጮ ነውና፡፡ ይህ ኃይል ነው እንግዲህ ሥልጣን ይዞ በኢትዮጵያ ስም የሰሜኑን ጦርነት (የሰሞኑን) በአጋፋሪነት እየመራ ያለው፡፡ “ውስጡን ለቄስ” አለች ማናት….
- ኦነግ፣ኦህዲድና ልክፍቱ
ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት እነዚህ ኃይሎች ወያኔ ዘርቶ ያበቀላቸው እሾህ አሜከላዎች ናቸው፡፡ ከወያኔ የሚሻሉት ከወገባቸው በላይ ሰው ስለሚመስሉ ነው፡፡ ከወያኔ ጋር የሚመሳሰሉት ከወገባቸው በታች እባቦች መሆናቸው ነው – እስፊንክስ ዓይነት ፍጡራን፡፡ ሲናደፉ ግን ወያኔንም ያስንቃሉ – ብልጠት ይጎድላቸዋል፤ መቼና የት ላይ፣ በምን ያህል ክረትና ፍጥነት መናደፍ እንደሚገባቸው አላውቁም ወይም አያውቁም፡፡ ማግኘት አሳብዷቸዋል፤ የበታችነት ስሜት በወለደው የበላይነት ስሜት ነብርረዋል፤ በሥልጣንና በሀብት ሙላት ናላቸው ዞሯል፡፡ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ወደ ውድቀታቸው እየገፋቸው እንደሆነ በፍጹም አልተረዱም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከወያኔ አወዳደቅ መማር ነበረባቸው፡፡ እንደ አካሄድ ኦህዲድና ኦነግ ወይም ኦብኮ አንድም ሁለትም ሦስትም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት መከላከያ በሰሜን ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ሳለ በመሀልና በዳር አገሮች ግን በነሽመልስ አብዲሣ (ኩነኔውን ለኔ ተውት!) ትዕዛዝ በተለይ አማራው እየተጨፈጨፈ ነው፡፡ ይህን የምንረዳው ከሽመልስ ንግግሮችና ከኦሮሚያ ክልል የልዩ ኃይል ሥልጠና ነው፡፡ በነሽመልስ ቤት (አስተሳሰብ) አማራን ከትግሬ አፋጅተው የአማራንና የትግሬን ኃልል “የዶጋ ዐመድ” ካደረጉ በኋላ እነሱ ትናንሽ ክልሎችን በኦሮሞ ሞልተውና የክልሎቹን ነዋሪዎች ማንነት ወደ ኦሮሞነት ለውጠው የምሥራቅ አፍሪቃን ታላቅ የኦሮሚያ መንግሥት ለመፍጠር ነው – የአባይን ግድብም ተቆጣጥረው፡፡ ቁጥር ሁለት ወይም ሦስት ወያኔ የሚያስብላቸውም ይህ ታላቅ ቅዠት ነው፡፡ ሲያምራቸው ይቀራል፤ ሂትለርም አልተሳካለት እንኳንስ በነዚህ ልበ-ሥውራን የተቀነቀነ ድውይ አስተሳሰብ ሊሰምር፡፡ ይህ ሁሉ ደባና ሤራ የሚያሣየን እንግዲህ ወያኔ ጠፋች አልጠፋች ቀድማ ያዘጋጀቸው መርዝና በጊዜ ሂደት በራሱ የሚፈነዳ ቦምብ በብዛትና በበቂ ሁኔታ እዚህም እዚያም ስለተቀበረ አሣራችንን ማሳየቱ የሚጠበቅ መሆኑን ነው፡፡ ግን ግን ሁሌ የምለውን አሁንም ልበልውና – ለሰው ጉድጓድ አትቆፍር፣ ከቆፈርክም አታርቀው … እናንተው ጨርሱት፡፡ የደርግንና የወያኔን መጨረሻ ያዬ ….
- ብአዴንና የተዞረበት ትብታብ
ብአዴን ካልተወገደ አማራም ሆነ ኢትዮጵያ ነፃ አይወጡም፡፡ አዴፓ ማለትም ብአዴን በአጋሰሶችና በአድር ባዮች እንዲሁም አማራ በተፈጥሮው “በታደለው” ሁሉን አቃፊነት የተነሣ አንድ ሰው አማራ ነኝ ካለ ምንም ስለማይጠየቅ በአማራነት ስም በተሰገሰጉና ራሳቸውን በሌላነት ፈርጀው ለሌላ አካል በሚሰሩ ሆዳሞች ስለተያዘ በዚህ ድርጅት አመራር አማራ መቃብሩ ይፋጠናል እንጂ ከገባበት አዘቅት አይወጣም፡፡ እንደዚህ ባይሆን ኖሮ ለአማራ እናስባለን የሚሉ ሰዎች ከድርጅቱ አይወጡም፤ አይባረሩም፤ አይታሰሩም፤ ከኃላፊነታቸው ዝቅ ተደርገውና ካለሙያና ችሎታቸው እንዲሠሩ አይመደቡም፣ አይገደሉምም … ነበር፡፡ ለምሣሌ ሰሞኑን በሚደረገው ጦርነት እንሳተፍ ያሉ የፋኖ ጀግች እንዳይሳተፉ ታግደዋል፡፡ በራሳቸው ጥረት የተሳተፉ ግን ውጤታማ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ የሚያሳየው ብአዴን በተረኛ ዘረኞች እስትንፋስ የሚመራ እንጂ የራሱ ኅልውና የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚደረግበት ወይም የማይደረግበት የራሱ ጊዜ አለውና ለዚያ ያብቃን…፡፡
- ከትግራይ አጎራባች ክልሎች የተወሰዱ መሬቶች ነገር
በኢትዮጵያ ምድር ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በተለይ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን ብሂል እስከጥግ በተግባር ያሳዬ ወያኔ ብቻ ነው – አሁን አሁን ደግሞ ምትኩ ኦህዲድ፡፡ ወያኔዎች ሥልጣን ከመያዛቸው ጀምሮ ዐይናቸው የገባላቸውን የአማራና የአፋር ግዛቶች በጉልበታቸውና ለዚህ ሲሉ በቀረጹት ሸፋፋ ህገ መንግሥታቸው አማካይነት ወደትግራይ አካልለዋል፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን የነዚህን የአማራና የአፋር ግዛቶች ቀደምት ነዋሪዎች በተጋሩ ለመተካት በነበራቸው ፍላጎት የተነሣ ነባር ባለይዞታዎችን በቻሉት መንገድ ሁሉ ገድለው፣ ለስደት ዳርገው፣ አሥረው፣ ጥቂቶችን ደግሞ ወደነሱ ለውጠው አካባቢዎቹን በግድ ለመቆጣጠር ለበርካታ ዓመታት ስቃይንና መከራን በማኅበረሰቦች ዘንድ ዘርተዋል፡፡ አሁን ግን ጊዜው በመለወጡ እነዚህ አካባቢዎች በባለይዞታዎቹና በመከላከያ እንዲሁም በአጎራባች ክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ርብርብ ነጻ ወጥተዋል፡፡ እነዚህን ግዛቶች በጉልበት ተወስደው በግፍ ይቀጠቀጡበት ወደነበረው ትግራይ ክልል ዳግም እወስዳለሁ የሚል ኃይል ከመጣ ጦርነቱ አርማጌዴዎናዊ ይሆናል፡፡ እንደውነቱ የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት እንደመሆኑ በቅንጭብጫቢ መሬቶች መጣላትና መወዛገብ አግባብ አይደለም፡፡ ይህ እውን ሆኖ ዜጎች ተከባብረውና “የኔ” የሚለው ተወግዶ “የኛ” የሚለው መርህ ሲነግሥ የጠብ መንስኤ አይኖርም፡፡ ለዚህ ግጭትና ጠብ ምክንያት የሆነው ህገ መንግሥት ተብዬ ተቀዳዶ ሲጣል የግጭቶች ምንጭ ሁሉ ይደርቃል፡፡ ባለው መቀጠል የሚፈልግ ኃይል ኖሮ እነዚህ ወያኔ በጉልበት የወሰዳቸውን መሬቶች ልውሰድ ቢል ግን ጠቡ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም ጋር ነው፡፡ ለሥልጣን ማቆያነትም ይሁን ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲባል ለድርድር ቢቀርቡ መዘዙ ታላቅ ነው፡፡ ያን ማድረግ በእሳት እንደመጫወት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን ያን መርዘኛ ህገ መንግሥት ተብዬ አስወግዶ ከሕዝብ ጋር በመመካከርና የሕዝብን ፈቃድ በማግኘት እጅግ ውብ የሆነች የጋራ ሀገር መፍጠር እንደሚቻል መገንዘብ ብልኅነት ነው፡፡ አዋጪው መንገድ እርሱ ብቻ ነውና፡፡ ብልጣብልጥነት ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡ የብልጦች መጨረሻ መቼም አምሮ አያውቅምና ከዚህ እንጠንቀቅ፡፡
እነዚህ ከፍ ሲል በአጭሩ የጠቃቀስኳቸው መሠረታዊ ችግሮች ካልተቀረፉ በወያኔ ውድቀት ብቻ ጮቤ መርገጥ ከንቱ ነው፡፡ መውደቃቸው እርግጥ ነው 40 በመቶውን ያህል የችግሮቻችንን መርግ ይንደዋልና እሰዬው ነው፡፡ የነፃነት ትግሉም ጀመረ እንጂ ገና አልተፋፋመም ….