>
5:28 pm - Saturday October 10, 2150

"በትግራይ ክልል የጀመርነው ሕግን የማስከበር ርምጃ ሁለተኛ ምእራፍ ተጠናቅቋል። አሁን በመጨረሻውና በሦስተኛው ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንገኛለን!!!" (ጠ/ሚ አብይ አህመድ)

“በትግራይ ክልል የጀመርነው ሕግን የማስከበር ርምጃ ሁለተኛ ምእራፍ ተጠናቅቋል። አሁን በመጨረሻውና በሦስተኛው ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንገኛለን!!!”
ጠ/ሚ አብይ አህመድ

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች:-
እየወሰድን ያለነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ሦስት ምእራፎች እንዳሉት ቀደም ብለን የገልጸን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምእራፍ፥ በገዛ ወገኑ የተጠቃውን የመከላከያ ሠራዊታችንን አሰባስበንና አጠናክረን፣ ተቋርጦ የነበረውን የእዝ ሰንሠለቱን ወደ ቦታው መልሰን ግዳጁን እንዲወጣ ማስቻል ነበር። በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በከፍተኛ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ ከገጠመው አደጋ በፍጥነት አገግሞ፣ የሕዝቡን ከፍተኛ ድጋፍ በልቡ ይዞ የሀገር ክህደት የፈጸመውን የሕወሐት ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሷል።
የርምጃው ሁለተኛ ምእራፍ ዋና ዓላማ፥ የሕወሐትን ጁንታ ከየአካባቢው እያስለቀቀ፣ ዐቅሙንም ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ ሕዝቡን ከዚህ የክህደት ቡድን ይዞታ ነጻ በማድረግ፣ የመሸገበትን የመቀሌ ከተማ መክበብ ነበር። ከመቀሌ ውጭ ያለውን ሕወሃት የያዘውን ቦታ ነጻ በማውጣት፤ የተዘረፉ ትጥቆችንና ካምፖችን መልሶ በመያዝ፤ የክህደት ቡድኑ የዘረፋቸውን ስትራቴጂያዊ የሆኑ መሣሪያዎችን ለውድመት ሳያውላቸው በፊት ከጥቅም ውጭ ማድረግ፤ በግዳጅ የያዛቸውን የሠራዊታችን አባላት ማትረፍ፤ የተሠውትን መቅበር እና አደጋ የሚደርስባቸውን ዜጎች መታደግ የሁለተኛው ምእራፍ እርምጃ ዝርዝር ዓላማዎች ነበሩ።
በዚህ መሠረት በዳንሻ፣ በሑመራ፣ በሽሬ፣ በሽራሮ፣ በአክሱም፣ በአድዋ፣ በአዲግራት፣ በአላማጣ፣ በጨርጨር በመሖኒ፣ በኮረምና በሌሎችም ቦታዎች በተወሰደ ርምጃ ሠራዊታችን ሕዝብ እየታደገና ድል እያደረገ ተጉዟል። ሕዝብ ለመታደግ በነበረው ዓላማ በተቻለ መጠን ሕግ የማስከበር እርምጃው በከተሞች አካባቢ ጥፋት እንዳያስከትሉ እና ሰላማዊ ዜጎች ዒላማ እንዳይሆኑ፤ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሃይማኖት ቦታዎች፣ የሕዝብ መገልገያዎች፣ መሠረተ ልማቶች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመሳሰሉት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ምንም እንኳን የክህደት ቡድኑ የጥፋቱ ደረጃ ሰፊ እንዲሆን ቢፈልግም፥ በሕግ ማስከበር እርምጃችን ወቅት፥ የአየር ኃይል አውሮፕላኖቻችን ለሕዝቡ በነበራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ወደ ዒላማዎቻቸው የቀረበ አንድም ሰው እንኳን ከገጠማቸው የታጠቁትን ትጥቅ ይዘው እስከ መመለስ ደርሰዋል።
በዚህም፥ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማው ቡድኑ በሃይማኖት ተቋማትና በቅርሶች አካባቢ ተኩስ እንዲኖር የነበረውን ፍላጎት፣ በሠራዊቱ ተልዕኮን በጥበብ የማከናወን ችሎታ አማካኝነት የቡድኑ ፍላጎት ሊመክን ችሏል። ነጻ በወጡ አካባቢዎች በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ሕዝቡን መልሶ እንዲደራጅ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ አማካኝነት የተጎዱ ወገኖቻችን እንዲደገፉ፣ ሕዝቡ የተፈጸመውን ነገር በትክክል እንዲረዳና ራሱን የሂደቱ አካል ለማድረግ ተችሏል። የተበላሹና የተበጣጠሱ ማኅበራዊ ተቋማትን፣ የመገናኛና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመጠገን፣ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።
ሁለተኛው የርምጃው ምእራፍ ሕዝቡን የታደገ፣ የጁንታውን አከርካሬ ሰብሮ አቅሙን ወደ መቀሌ ማጥበብ ተችሏል።
አሁን የቀረው ጉልበት መቀሌ ላይ ያደራጀው ምሽግ እና አልፎ አልፎ የሚያሰማው ከንቱ ፉከራ ነው። በዚህ ሕግን የማስከበር እርምጃ ወቅት ሕዝባችን ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ሕወሃት ስለ መከላከያ ሠራዊቱ የነዛው ፕሮፓጋንዳም ስሕተት መሆኑን የትግራይ ሕዝብ በዓይኑ ለማየት ችሏል። የሠራዊቱን ደግነትና ከጥፋት ለመታደግ የከፈለውን መስዕዋትነት ሕዝቡ ራሱ መመስከር ጀምሯል። በየአካባቢው ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ለሠራዊቱ በማብላት፣ የክህደት ቡድኑ የሚሄድባቸውን መንገዶች በመጠቆም፤ የተደበቁ መሣሪያዎችንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በማጋለጥ ከሠራዊቱ ጎን ሆኖ የሚያስደንቅ ተጋድሎ ፈጽሟል። በዚህም የትግራይ ሕዝብ ቀድሞም በሕወሃት የጥፋት መንገድ ምን ያህል እንደተንገሸገሸ በግልጽ አሳይቷል።
ሠራዊቱ ሽሬ በገባበት ጊዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሆታ ከመቀበሉም በላይ፣ ጁንታው ያስታጠቀውን ከ200 በላይ መሣሪያ ሰብስቦ ለመከላከያ አስረክቧል። ሠራዊታችን አክሱም በደረሰም ጊዜ ሕዝቡ ራሱ በክህደት ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የዋሉ የሠራዊት አባላትን ነጻ አድርጎ፣ የቆሰሉትን አክሞና ተከባክቦ፣ በክብር ለመከላከያ ሠራዊቱ አስረክቧል። የአክሱም ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱ ከእርሱ ጋር እንዲሆን ከመጠየቁም በላይ አብሮ ተሠልፎ የሕግ ማስከበሩ ዳር እንዲደርስ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በተመሳሳይ ሠራዊታችን አዲግራት ሲገባ፣ ሕዝቡ ራሱ የተደበቁትን የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት እየያዘ ለመከላከያ አስረክቧል።
በተቃራኒው የቆመው የክህደት ቡድን ስንትና ስንት የሀገር ሀብትና ጉልበት የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን እያፈረሰ፣ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ፣ መንገዶችና ድልድዮችን እየደረማመሰ ሸሽቷል። የታሪካዊቷ አክሱም የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጭምር ውድመት በማድረስ የቀጣይ ዓመታት የቱሪዝም እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። የክልሉ ነዋሪ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያደርግባቸውን መንገዶች በዶዘር ማፈራረሱ ሳይበቃው፥ የመቀሌ ከተማን ልክ እንደ ጦርነት አውድማ ለማድረግ በመዛት ቅንጣት ታህል ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
አሁን ሕግ የማስከበር ርምጃው ወደ ሦስተኛውና ወሳኙ ምእራፍ ተሸጋግሯል። ሦስተኛው ምእራፍ በመቀሌ የሚካሄደውና የክህደት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ የሚደረግ የመጨረሻው እርምጃ ነው። የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጥበብ፣ ጥንቃቄና ትእግሥት የሚፈልግ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ይህ የክህደት ቡድን ለምንም ነገር ደንታ እንደሌለው፥ ለሕዝቡ፣ ለታሪኩ፣ ለባህሉ፣ ለቅርሱና ለእምነቱ ቅንጣት ርኅራሄ እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል። ሁሉም ነገር ጠፍቶ እርሱ ብቻ ቢተርፍና ከሕግ ቢያመልጥ ደስተኛ ነው። በዚህም የተነሣ በመቀሌ ከተማ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ሆቴሎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ የሕዝብ መኖሪያ መንደሮችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ቅርሳ ቅሶችንና መካነ መቃብሮችን ሳይቀር እንደ ምሽግ ተጠቅሞባቸዋል። መጥፋቱ ላይቀር ብዙዎችን ይዞ ለመጥፋት ተዘጋጅቷል። ልክ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚታዮት የሽብር ቡድኖች፣ ለሕዝብና ለሀገር ምንም ደንታ የሌላቸው አሸባሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ይሄ የጥፋት ቡድን መቀሌን እንደ ሕዝብ መኖሪያነት ሳይሆን እንደ ጦር አውድማነት ቆጥሯታል።
በዚህ ቡድን ምክንያት እንዲሞቱ የተገደዱት ነዋሪዎች ዜጎቻችን እንደመሆናቸው መጠን እና የሚወድመውንም ከተማ ነገ መልሶ ለመገንባት ዞሮ ዞሮ የእኛው ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን በመቀሌ የሚኖረን የሕግ ማስከበር ርምጃችን፥ ጉዳትን እጅግ በቀነሰ መልኩ መከናወን እንዳለበት እናምናለን። ስለዚህም፥ የመቀሌ ከተማን ከከፋ ጉዳት ታድገን ዘመቻውን በድል የምናከናውንበትን መንገድ እንደምንከተል ለመግለጽ እወዳለሁ። መንግሥት ይሄንን የሚያደርገው በዚህ የክህደት ቡድን የተነሣ ሕዝብና ሀገር እንዳይጎዳ ከመፈለግ ነው።
በመሆኑም፤
አንደኛ፡- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች፥ በጀመርነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ቁልፍ ተዋናዮች እንድትሆኑ፣ ከሠራዊታችን ጎን በመቆም ይሄንን የክህደት ቡድን አባላት ለፍርድ በማቅረብ ወሳኝ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን። ለጥቂት ስግብግብ ጁንታዎች ሲባል አንድም ሰው መሞት፣ አንዲትም ንብረት መውደም የለበትም።
ለዚህም የእናንተ ትብብር አይተኬ ሚና የሚጫወትና ብዙ ጉዳቶችን እንደሚያቀል እሙን ነው።
ሁለተኛ፡- የክህደት ቡድኑን ዓላማ በማስፈጸም ላይ ያላችሁ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት፥ አሁንም ቢሆን እጃችሁን በሰላም ለመስጠት ጊዜው አልረፈደም። ሕግ የማስከበር እርምጃው የመጨረሻ ምእራፍ ላይ መሆናችንን ተረድታችሁ የማያዳግመውን ዕድል እንድትጠቀሙበት፤ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ባለው በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም ለመንግሥት እንድትሰጡ የመጨረሻ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
ሦስተኛ፡- የጁንታው አባላት፥ የጥፋት ጉዟችሁ ጀንበሯ እየጠለቀች መሆኑን አምናችሁ፣ ከማትወጡበት ቅርቃር ውስጥ መግባታችሁን ተገንዝባችሁ በቀጣይ 72 ሰዓታት ውስጥ እጃችሁን በሰላም እንድትሰጡ እንጠይቃችኋለን። የመጨረሻዋን ዕድል ተጠቀሙበት። ተጨማሪ የሕዝብ እልቂት ከመፍጠርና ከተማ ከማውደም ተቆጥባችሁ ከታሪክ ውግዘት እንድትድኑ ጥሪ እናቀርባለን።
በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው የምንፈልገው ነገር ቢኖር ሦስተኛውን ምዕራፍ የሕግ ማስከበር እርምጃ ከማከናወን ጎን ለጎን በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ወገኖቻችንን ለመመለስ፤ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም፤ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን፤ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች ወደ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በሁሉም ረገድ ዝግጅት አድርገናል። ወደ ትግበራ ስንገባ ከእጃችን እንዳያጥር እና ዐይናችንን ወደ ሌሎች እንዳናማትር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን። እኛ ኢትዮጵያውያን የቆየና የዳበረ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል ስላለን፣ የማንንም የውጭ እጅ ሳንጠብቅ ወገኖቻችንን እኛው ልናቀዋቁማቸው ይገባል። ለዚህም በመንግሥትና በተለያዩ የማኅበረሰብ አንቀሳቃሾች አማካኝነት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀሉ ስል ጥሪ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ኅዳር 13 ቀን 2013 ዓ.ም
Filed in: Amharic