>

ተመልሰናል!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ተመልሰናል! 

አቻምየለህ ታምሩ
የፋሽስት ወያኔና የናዚ ኦነግ የማኅበራዊ ሜዲያ ሠራዊት ባደረገብን ዘመቻ ተገትቶ የነበረው የሀሳብ መስጫ መድረካችን በሙሉ አቅም  ሀሳብ ማቅረቡን ሊቀጥል  እነሆ አገታው አብቅቶ ተመልሰናል። ፋሽስት ወያኔና ናዚ ኦነግ ኢትዮጵያን ያዋቀሩበት ርዕዮተ ዓለም ተወግዶ ኢትዮጵያ በቀደመ እውነቷ እስክትድን ድረስ ተጋድሏችን ይቀጥላል።
በቅድሚያ አማራ በመሆናችሁ ብቻ በጠላትነት ተፈርጃችሁ ከርስታችሁ በግፍ እንድትፈናቀሉና ተነግሮ የማያልቅ  የፋሽስት ወያኔ የጭካኔ ተግባር መለማመጃ ሆናችሁ     የመላውን አማራ የፍዳ፣ የመከራ፣ የሰቆቃ፣ የግዞትና የሰቆቃ  ቀንበር ተሸክማችሁ ለአርባ ዓመታት እንድትሰቃዩ ተፈርዶባችሁ የኖራችሁ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ እንዲሁም የራያ አማሮች እድለኛ በመሆን በሕይዎት ያላችሁና በተዓምር ተርፋችሁ ዛሬን ለማየት የበቃችሁ ወገኖቼ  ሁሉ እትብታችሁ የተቀበረበትንና ያያት ቅድመ አያቶቻችሁን ቀዬ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለመርገጥ በመብቃታችሁ እንኳን ለዚህ ቀን አበቃችሁ እላለሁ። ይህንን ስል አንዳንዶች እንደሚሉት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሁመራና ራያ ትግል  አልቋል አያልሁ አይደለም። ትግሉ ተጀመረ እንጂ  ፍጻሜ የደረሰ፤ ተቋማዊ የሆነ ነገር ገና አላስመዘገበም። የትግል ፍጻሜ የሚሆነው የትግሉ ፍሬ በመዝገብ ገብቶ ሕጋዊና ተቋማዊ ሲሆን ብቻ ነው። ይህ እስኪሆን ድረስ ፍትሐዊው ተጋድሎ መቀጠል አለበት።
ቀጣዩ ወሳኝ ተጋድሎ ፋሽስት ወያኔ  እነወልቃይትንና ራያን ወደ ትግራይ በቅኝ ግዛትነት ያካተተው በ1968 ዓ.ም. ባወጣው ማኒፌስቶ እንጂ በሕገ መንግሥት ተብዮው መሰረት ባለመሆኑ ሕገ መንግሥት ተብዮውን መሰረት አድርጎ የተቋቋመው የወሰንና የማንነት ኮሚሽን የነወልቃይት ጉዳይ እንደማይመለከተው በጽናት ማሳወቅ፤ በቅኝ ግዛት ስር የነበረ ነጻ ይወጣል እንጂ ወደ ቅኝ ግዛት መመለስ ስለሌለበት በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራና ራያ ምድር የተጫነው የፋሽስት ወያኔ የቅኝ ግዛት ቀንበር ሙሉ በሙሉ እንዲሰበር ማድረግና  ተነግሮ የማያልቅ ግፍ የፈጸሙት ወያኔዎች አንዳቸውም ሳይቀሩ በአለማቀፍ ወንጀለኛነታቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ነው። እነዚህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ባለፉት አርባ ዓመታት በፋሽስት ወያኔ የተፈጸመው አይነት ግፍና መከራ በመጪው ትውልድ  ላይ ሊፈጸም እንዳይችል ማድረግ አይቻልም።
ሕወሓት የሚባለውን የኢትዮጵያ ካንሰር ለማስወገድ የሚደረገውን ቅዱስ ተጋድሎ  ፋሽስታዊ ድርጅቱ እስኪፈርስ ድረስ መቀጠል አለበት። በአለም ታሪክ እንደ ሕወሓት ያሉ ከሬት አብልጦ የሚመር መከራ በአማራ ላይ ለመፈጸም የተቋቋሙ የፋሽስትና የናዚ ድርጅቶች የከሰሙበት ሌላ መንገድ በታሪክ ውስጥ ስለሌለ ሕወሓት የሚባለውን ለወንጀል የተቋቋመ የኢትዮጵያ ካንሰር ለማስወገድ የሚደረገው ቅዱስ ጦርነት ሰላም ለማግኘት የሚደረግ ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ተጋድሎው በተባበረ ክንድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
በርግጥ በጣም አድርጎ የሚኮመዝዘውን፤ ከሬትም የሚመረውን ሕወሓት የሚባለው ፋሽስታዊ የወንጀል ድርጅት የፈጸመውን መከራ ያልቀመሰ፤ የሕዝባቸውን አለኝታነትና አደራ በኃላፊነት መንፈስ መሸከም ያቃታቸው፤ ምርጫ ያላቸውና የግፉ ግንባር ቀደም ቀማሽ ያልሆኑ፤  ራሳቸውን የሞራል ጉምቱ አድርገው የቆለሉ፣ ተምረናል ብለው የሚያስቡ፣ አንድ እግራቸውን በፈረንጅ አገር፣ ሌላ እግራቸውን ደግሞ ከየመጣው ጋር አሰላለፋቸውን እያስተካከሉ ባገር ቤት አንፈራጥጠው እንደፈለጉ ተንደላቅቀው የሚኖሩ አንዳንዶች ይህን አይረዱ ይሆናል። ለወንጀል የተቋቋመው ድርጅት ግንባር ቀደም የገፈቱ ቀማሽና የግፍ አርጩሜው ያረፈብን ግን ሕወሓት የሚባለውን የወንጀል ድርጅት ለማስወገድ የሚደረገውን ጦርነት ብቸኛው የሰላም ማግኛ በር አድርገን እንመለከተዋለን።
ታዲያ እኛ እንዲወገድ የምንታገለው ሕወሓትን እንደ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ሕወሓት የቆመላቸውን የአፓርታይድ አስተሳሰቦች፣ ሕጋዊ ያደረጋቸውን ደንቦች፣ ኢትዮጵያን ያዋቀረበትን ሕገ መንግሥት የሚባለውን የወንጀል ሥነ ሥርዓትና  መዋቅር የዘረጋላቸውን የአፓርታይድ አሰራሮች ሁሉ ነው። ለዚህ አላማ ተሰልፈው ፋሽስታዊውን ድርጅት እስከ መጨረሻ ምሽጉ ድረስ ሲፋለሙ በጀግንነት ለተሰውና ለሚሰው ያገሬ ልጆች መስዕዋትነታቸው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ፤ ለትውልዳቸው ኩራትና ለነሱም ሐውልት ሆኖ መቼውንም ቢሆን ሲያስታውሳቸው የሚኖር  የታሪክ አምድ ነው።
ድል ጨካኙን ዘንዶ ለምትፋለሙ ጀግኖች!
Filed in: Amharic