>

ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

       በሰሜን ተመድቦ የአገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ ዘብ የቆመውን ሠራዊትና በሥፍራው ያሉትን ሠላማዊ ሕዝቦች የሕውሐት ሀይል በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፉና የሰማዕታቱን አስከሬን ልብስ አውልቆ አውሬ እንዲበላው ማድረግ፤ ጨፍጫፊው የፋሽስት ሀይል የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከፈጸመው የከፋ ነው፡፡ ወያኔ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ሕዝባዊ አመለካከት ያልተላበሰ ከኢትዮጵያ ምድር ያልበቀለ የእርኩሶች ስብስብ መሆኑን በሥራው አስመስክሩዋል፡፡ የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ግዳጁን ሲወጣ የነበረን የአገር አለኝታ በሬሳው ላይ ሲሳለቁና ከበው ሲጨፍሩ ማየት ይህ ድርጂታቸው ቀይ መሥመር ያለፈ መሆኑን አስመስክሩዋል፡፡ የደፈረውም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ሕዝብን መሆኑን ያላገናዘበ የደንቆሮዎች ስብስብ መሆኑን አስመስክሩዋል፡፡

      ስለሆነም በጀምላ ጭፍጨፋ ሕውሐትና መሪዎቹ ለዘላለም ውግዝ እንዲሆኑና አመራሩ ደግሞ በሕግ እንዲጠየቅ ማድረግ የሚገባ ነው እንላለን፡፡

      ልዑላዊነታችንን  ለማስጠበቅ በጦር ሜዳ የሚሰለፈው ሠራዊታችን ቢሆንም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጦርነት ነው፡፡ ይህም ፍትሓዊ ነው፡፡

      አባቶቻችን ብሄር ሳይለዩ ሁሉም ለአገሩ ልዑላዊነት በአንድነትና በትብብር የጠላትን ሀይል ሰባብረው ነጻነታችንን አስጠብቀዋል፡፡ ዛሬም እንደ ትናትናውና እንደጥንቱ በአንድነት በዘር የተለያየች አገርን ተሸክመን ወንዝ መሻገር ስለማያስችል ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር እንድንቀሳቀስ የሚያስችልበትን ሥርዓት ልንመሠርት ይገባል፡፡

        የኢትዮጵያ ሠራዊት ለሚከፍለው መስዋዕትነት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አጋዥ ይሆን ዘንድአእንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር እርዳታ በዚህ አጋጣሚ መስጠቱን በትህትኛ እንገልጣለን፡፡

          ኢትዮጵያ በለጆቹዋ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች፤

          እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ፤

 

Ambassador Alemayehu Abebe Shenkut,
Vice President of Association of Ethiopian Patriots
Filed in: Amharic